1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በትግራይና አጎራባች ክልሎች ያለ ገደብ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ለማመቻቸት ሥምምነት ተደረሰ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 3 2015

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ለአራት ቀናት በናይሮቢ ካደረጉት ድርድር በኋላ በትግራይና አጎራባች ክልሎች ያለ ገደብ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ለማመቻቸት ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን የአፍሪካ ኅብረት ገልጿል።

Kenia I Friedensabkommen von Pretoria
ምስል፦ Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በትግራይ እና አጎራባች ክልሎች ለተቸገሩ ሁሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ያለ ገደብ ለማመቻቸት ከሥምምነት ደረሱ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ዛሬ ቅዳሜ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በተፈራረሙት ሰነድ ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች ያለ ገደብ እንቅስቃሴ ለማመቻቸት መስማማታቸውን የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል። 

ሁለቱ የጦር አዛዦች የተፈራረሙት ሰነድ በፕሪቶሪያ በተደረሰበት ግጭት የማቆም ሥምምነት መሠረት ለግብረ ሰናይ ሠራተኞች እና ለድርጅቶች የደህንነት ዋስትና መስጠት እንዲሁም ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ማድረግን ያካተተ ነው። 

በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በሁለቱ ኃይሎች አዛዦች መካከል ሲደረግ ከቆየ ድርድር በኋላ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙትን ግጭት የማቆም ሥምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ሥምምነት ላይ ደርሰዋል። 

በሁለቱ የጦር አዛዦች መካከል በናይሮቢ የተካሔደውን የአራት ቀናት ድርድር አፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ፐምዙሌ ምላቦ አማካኝነት የተመቻቸ ነው። ምስል፦ Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

በሁለቱ የጦር አዛዦች መካከል በናይሮቢ የተካሔደውን የአራት ቀናት ድርድር አፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ፐምዙሌ ምላቦ አማካኝነት የተመቻቸ ነው። 

የአፍሪካ ኅብረት ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው በትጥቅ አፈታት፣ አበታተን እና የመልሶ ማዋሃድን በተመለከተ በዝርዝር የሚያብራራ የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም ወስነዋል። 
የኢትዮጵያ መንግሥት "በሰላም ሥምምነቱ በተያዘው የጊዜ ገደብ ትጥቅ የሚፈታበትን እና መከላከያ ወደ መቐለ የሚገባበት ዕቅድ ላይ" ከሥምምነት መደረሱን ገልጿል። 

የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔተ ቬበር የትጥቅ አፈታትን በተመለከተ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰው ሥምምነት "ወደ ፊት የሚወስድ አስፈላጊ እርምጃ" እንደሆነ ገልጸዋል። 

የዛሬውን የናይሮቢ ሥምምነት የፈረሙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በተፈራረሙት ሥምምነት "ወታደራዊ ጉዳዮች" ላይ አተኩረው ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ውይይቱ "በጥሩ መንፈስ እና መግባባት" መከናወኑን የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ "ለሕዝባችን እና ለአገራችን ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ሙሉ ቁርጠኛ መሆናችንን መግለጽ እንፈልጋለን" ሲሉ ተደምጠዋል። የፕሪቶሪያውን ሥምምነት እና በኬንያ የተፈረመውን ሰነድ መግለጫ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገልጸዋል።  

የአፍሪካ ኅብረት ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ የሚፈቱበትን፣ የሚበተኑበትን እና መልሰው የሚዋሀዱበትን አኳኋን በዝርዝር የሚያብራራ የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም ወስነዋል። ምስል፦ Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

"ላለፉት ሁለት ዓመታት ሕዝባችንን ለመጠበቅ እና ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ስንዋጋ ቆይተናል" ያሉት የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው "የማይነገር መከራ ደርሶብናል፤ አሁንም እየተሰቃየን ነው" ሲሉ ተደምጠዋል። 

ጄኔራል ታደሰ ሥምምነቱን የሚፈርሙት "ሕዝባችን የሚደርስበት መከራ ያበቃል" በሚል ተስፋ እንደሆነ በንግግራቸው ጠቁመዋል። ይሁንና "ከውስጥም ከውጪም ከጦርነቱ የሚያተርፉ ኃይሎች" እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ መኖራቸውን ጠቅሰው ሥምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ "ከባድ ሥራ" እንደሚሆን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት "ግጭቱን ማቆም ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን በማመቻቸት እና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ በማስጀመር ሥምምነቱን ያከብራል" የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል።  

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW