«በትግራይ ከመቶ 50 ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል» የትግራይ አስተዳደር
ሰኞ፣ ሰኔ 9 2017
«በትግራይ ከመቶ 50 ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል» የትግራይ አስተዳደር
በትግራይ 50 ከመቶ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው እንዳለ የክልሉ አስተዳደር ገለፀ። ድህነት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ሁኔታዎች ለዚህ ምክንያቶች ናቸው ተብለዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ህፃናት በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ በልመና ተሰማርተዋል፣ ለጉልበት ብዝበዛ እየተዳረጉ መሆኑንም ተገልጿል። ዛሬ የአፍሪካ ህፃናት ቀን እየተዘከረ ነው። ከ12ኛ ክፍል ተፈታኞች 1 ተማሪ ብቻ የወደቀበት ትምህርት ቤት
የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከጦርነቱ በፊት በክልሉ 95 በመቶ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት በትምህርት ገበታ እንደነበሩ የሚገልፅ ሲሆን ይህ አሁን በከፍተኛ መጠን ቀንሶ በክልሉ በትምህርት ገበታ ያሉ ህፃናት ከሚጠበቀው ከ50 በመቶ በታች መሆናቸው ያመለክታል። የድህነት መንሰራፋት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ሁኔታዎች ህፃናት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ ምክንያት መሆኑ ተመላክቷል። በተለይም ከጦርነቱ በኃላ በትግራይ ድህነት ይበልጥ መንሰራፋቱ የሚገለፅ ሲሆን፥ ይህ ሁኔታ ተከትሎ ህፃናት እና እናቶች ከቀዬአቸው ይፈናቀላሉ፣ ወደተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተሰደው በልመና ይሰማራሉ፣ ለጉልበት ብዝበዛ ይዳረጋሉ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሆነው የከፋ ህይወት የሚመሩበት ሁኔታ ይስተዋላል። በህፃናት ድጋፍ ዙርያ የሚሰሩት አቶ የማነ ወልደማርያም፥ በመቐለ የጎዳና ተዳዳሪዎች ህፃናት ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩ፣ እነዚህ ህፃናት ከትምህርት ውጭ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለዘላቂ ችግር እየተጋለጡ ስለመሆኑ ያነሳሉ።
ዛሬ እየተከበረ ያለው የአፍሪካ ህፃናት ቀን፥ ህፃናት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ታሳቢ ተደርጎ እንዲሰራ መልእክት ይተላለፍበታል። ቀኑ አስመልክቶ በትግራይ ስላለው የህፃናት ሁኔታ ዙርያ ማብራርያ የሰጡት የትግራይ ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሐላፊ አቶ ገብረስላሴ ታረቀ፥ ከግዜ ወደ ግዜ የህፃናት ተማሪዎች መጠን እየቀነሰ መሆኑ ይገልፃሉ። ባለስልጣኑ "የትግራይ ህፃናት በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠሩ ችግሮች 50 በመቶ የሚሆኑት በትምህርት ገበታ ላይ የሉም። ከመጀመርያውኑ 49 በመቶ የሚሆኑት አልተመዘገቡም። በሂደት በርካቶች አቋረጡ። አሁን ላይ ከ50 በመቶ በላይ በትምህርት ገበታ ላይ የሉም" ሲሉ አክለው ገልፀዋል።ወደ ትምህርት ገበታ ያልተመለሱት 1.2 ሚልዮን የትግራይ ሕጻናት እና አዳጊዎች
በትግራይ ያለው አጠቃላይ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት በተለይም በህፃናት ላይ የተጋለጠ ዘላቂ ችግር ለመቅረፍ ጥረቶች እንደሚያስፈልጉ የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣናት ጀነራል ዘውዱ ኪሮስ ይገልፃሉ።
ጀነራል ዘውዱ "ባለው ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ምክንያት ህፃናት የሚያስተምራቸው፣ የሚንከባከባቸው፣ የሚያሳድጋቸው ስላጡ እንዲሁም ከወላጅ እና አሳዳጊዎቻቸው ስለተለያዩ፣ ተፈናቅለው በመጠልያ እንዲሁም በየጎዳናው ስላሉ የሚታደጋቸው ይሻሉ። በተጨማሪም ህፃናት የስነልቦና ችግር ገጥሟቸዋል። እነዚህ ማዳን ይጠበቃል" ብለዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ