በትግራይ ክልል ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡትን ለማገዝ ያለመው ቴሌቶን
ሰኞ፣ ጥቅምት 11 2017በትግራይ ክልል ለረሃብና ለተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ዜጎች ለማገዝ ያለመ ገቢ ማሰባሰብ ዘመቻ ትናንት እሁድ ተጀመረ። በዚህ ዘመቻ አንድ ቢልዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትም 130 ሚልዮን ብር ለግሷል። በትግራይ 4 ነጥብ 5 ሚልዮን ዜጎች እርዳታ ፈላጊ መሆናቸው ተመላክቷል።
ጦርነቱ፣ ከጦርነቱ በኃላ ደግሞ በትግራይ የተከሰተው ድርቅ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት በትግራይ የእርዳታ ፈላጊ መጠን ከፍተኛ ሆኖ ቀጥሏል። እንደ የክልሉ አስተዳደር መረጃ በትግራይ አሁን ላይ 4 ነጥብ 5 ሚልዮን ህዝብ እርዳታ ፈላጊ ሆኖ እንዳለ የሚገልፅ ሲሆን፥ ከለጋሾም የሚሰጥ የእርዳታ መጠንም ለሁሉም እየደረሰ እንዳልሆነ ያመለክታል። በክልሉ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ያለው የህዝቡ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ጋርዶታል የሚለው ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የትግራይ አስቸኳይ ምላሽ ግብረሀይል፥ ይህ ከፍተኛ ማሕበራዊ ቀውስ ሳይባባስ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ይገልፃል። የግብረሀይሉ አባል እና የገቢ ማሰባሰብ አስተባባሪ አቶ ዶሪ አስገዶም ለዶቼቬለ እንዳሉት በትግራይ ያለው ቀውስ እየተባባሰ እንጂ መፍትሔ እያገኘ አይደለም ይላሉ።
የትግራይ ነጻነት ፓርቲ አባላቶቼ ግድያና እንግልት ተፈጸመባቸው አለ
በትግራይ ረሀብ ጨምሮ የተለያዩ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ያለመ ገቢ የማሰባስ ዘመቻም በትላንትናው ዕለት ተጀምሯል። በትላንትናው መድረክ የተናገሩት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም፥ ባለፊት ስድስት ወራት በትግራይ ለሚገኙ እርዳታ ፈላጊዎች ድጋፍ እያደረገ መቆየቱ የገለፁት ሲሆን በዚህ በተጀመረው ዘመቻ ደግሞ 130 ሚልዮን ብር ለመስጠት በኮምሽናቸው በኩል ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን አማራና ትግራይ ክልል «መስራት ተሳነኝ» አለ
የትግራይ ህዝብ ችግር በውስጥ አቅም መፍታት የሚቻልበት ዕድል ቢኖርም በአስተዳደር ክፍተት ያለው ሀብት ችግር እየፈታ ሳይሆን ችግር እየፈጠረ ነው ያሉት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ፥ የክልሉ አስተዳደር በቢልዮኖች የሚገመት የወርቅ ሀብት ከሚያወጡ አካላት እንኳን አንድም ገቢ እንዳላገኘ ጠቁመዋል።
የትግራይ ክልል ባለሃብቶች በባንኮች ላይ ያቀረቡት አቤቱታ
አቶ ጌታቸው ረዳ "በሶስት ወር ብቻ ከ17 ቢልየን ብር በላይ የሚያወጣ ወርቅ ከአንድ መንደር ብቻ የሚወጣባት ትግራይ ነች። እንደ መንግስት መሪ ከዚህ ሀብት ይህ የሚባል ሳንቲም አላገኘንም። ያላገኘንበት ምክንያት አስተዳደራችን ማሻሻል ባለመቻላችን፣ ፖለቲካዊ ጤንነት መፍጠር ባለመቻላችን ነው። ሀብታችን የትግራይ ችግር ከመፍታት ይልቅ የትግራይ ህዝብ ችግር ይበልጥ እንዲወሳሰብ እያደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው" ብለዋል።
የተከፋፈሉትን የሕወሓት ፖለቲከኞች ለማስታረቅ የተደረገዉ ጥረት አልተሳካም
በዚህ ትላንት በይፋ የተጀመረው ገቢ ማሰባሰብ አንድ ቢልዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱ ያነሱልን የአስቸኳይ ምላሽ ለትግራይ አባልና የቴሌቶኑ አስተባባሪ አቶ ዶሪ አስገዶም፥ ችግር ላይ ያሉት ለመታደግ ሁሉም አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ትግራይ ክልል የሕወሓትና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፍጥጫ ቀጥሏል
አስተባባሪዎቹ ይህ ገቢ ማሰባሰብ በቀጣይ ሳምንታት በአዲስአበባ ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ይቀጥላል ተብሏል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ