1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ክልል ዕርዳታ ከሚፈልገዉ ሕዝብ 1.5 ሚሊዮኑ ርዳታ አያገኝም-ኮሚሽን

ረቡዕ፣ ግንቦት 21 2016

የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን እንደሚለው ጦርነቱ ያስከተለው ውድመት፣ ከጦርነቱ በኃላ ደግሞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በሚፈለገው ሁኔታ አለመለመመስ፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አሁንም በመጠልያዎች መኖራቸው እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከፍተኛ አድርጎታል

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ለሚገኙ ርዳታ ፈላጊዎች ደግሞ እርዳታ መታገዱን ዞኑ አስታዉቋል።
ትግራይ ዉስጥ ዕርዳታ ከሚፈልገዉ ከ4.5ሚሊዮን ሕዝብ 1.5 ሚሊዮኑ እስካሁን ርዳታ አይደርሰዉምምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

በትግራይ ክልል ዕርዳታ ከሚፈልገዉ ሕዝብ 1.5 ሚሊዮኑ ርዳታ አያገኝም-ኮሚሽን

This browser does not support the audio element.

በትግራይ ክልል 4 ነጥብ 5 ሚልዮን ሕዝብ  የምግብ እርዳታ እንደሚሻ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን አስታወቀ።ከዕርዳታ ፈላጊው ለ3 ሚልዮን ዜጎች ዓለምአቀፍ ተቋማትና ሌሎች አጋዦች እርዳታ እየቀረበ ቢሆንም የተቀሩት 1 ነጥብ 5 ሚልዮን ግን አሁንም ያለ ምንም ድጋፍ ችግር ላይ መሆናቸው ተገልጿል። በሌላ በኩል ወደ ትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ኦፍላ እና ዛታ አካባቢዎች መድረስ ይገባው የነበረ እርዳታ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት እንዳይጓጓዝ መከልከሉ የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

ከጦርነቱ በኃላ በተባባሰ ሰብአዊ ቀውስ የምትገኘው ትግራይ፥ ከአጠቃላይ ህዝቡ 4 ነጥብ 5 ሚልዮን የሚሆነው የምግብ እርዳታ ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑ የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ቁጥራዊ መረጃ ያመለክታል። የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን እንደሚለው ጦርነቱ ያስከተለው ውድመት፣ ከጦርነቱ በኃላ ደግሞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በሚፈለገው ሁኔታ አለመለመመስ፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አሁንም በመጠልያዎች መኖራቸው እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከፍተኛ አድርጎት እንዳለ ይገልፃል። ለዶቼቬለ የተናገሩት የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር ዶክተር ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር ከአጠቃላይ በትግራይ ያሉ 4 ነጥብ 5 ሚልዮን እርዳታ ፈላጊዎች በዓለምአቀፍ ተቋማት እና ሌሎች አጋዥ ድርጅቶች የምግብ እርዳታ እያገኙ ያሉት 3 ሚልዮን ብቻ ናቸው። 

ዶክተር ገብረህይወት "ከነበረው የተሻለ ሁኔታ ቢኖርም፥ ሁሉም ድጋፍ የሚሻ ግን እርዳታ እያገኘ አይደለም። ሶስት ሚልዮን የሚሆን ህዝብ በየወሩ ድጋፍ እያገኘ ነው። ከእነዚህ መካከል ቢሆንም አንድ ነጥብ አንድ ሚልዮን የሚሆነው እርዳታ ፈላጊ 'ፉል ፓኬጅ' እርዳታ አይደለም እያገኘ ያለው"

እንደ የትግራይ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ገለፃ፥ አሁንም በትግራይ ሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ ሊሆንላቸው ያልቻሉ አካባቢዎች አሉ። በሌላ በኩል እርዳታ ሊቀርብላቸው እየተገባ በበላይ አካል ውሳኔ መሰረት በተባለ፥ ወደ ትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ኦፍላ እና ዛታ አካባቢዎች የምግብ እርዳታ አቅርቦት ከቅርብ ግዜ ወዲህ እንዲቋረጥ መደረጉ የዞኑ አስተዳደር ይገልፃል። በዚህም በኦፍላ እና ዛታ አካባቢዎች የሚገኝ ከ130 ሺህ በላይ እርዳታ ጠባቂ ላለፉት ሁለት ወራት ተፈላጊ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንዳላገኘ የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር አስታውቋል። የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር ሳይኖር እና ግለፅ ምክንያት ሳይቀመጥ ወደ አካባቢዎች የምግብ እርዳታ አቅርቦት ተቋርጧል ይላሉ። 

በትግራይ ክልል የተደረገዉ ጦርነት ከቤት ንብረታቸዉ ያፈናቀላቸዉ ሰዎች ከሰፈሩበት መጠለያ ጣቢያ አንዱምስል Million Haileselassie/DW

አስተዳዳሪው "ወደዚህ አካባቢ እርዳታ የቆመው ከሁለት ወር በፊት ነው። ጉዳቱ ለማንም ግልፅ ነው።  . . . መጣራት አለበት ግን ክልከላው ከአደጋ መከላከል ኮምሽን ይመስለናል" ይላሉ። 

እንደ የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ ገለፃ፥ የእርዳታ አቅርቦት ወደ ኦፍላ እና ዛታ አካባቢዎች እንዲቋረጥ መደረጉ ፖለቲካ ይዘት ያለው ብለውታል። አቶ ሀፍቱ ኪሮስ "የእርዳታ አቅርቦቱ ለምን እንደቆመ፥ አስቋሚው ነው በትክክል የሚያውቀው። በርግጠኝነት ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው የሚሆነው። እርዳታን ለፖለቲካ የመጠቀም አባዜ ነው። በጣም ግልፅ ነው ይሄ" ብለዋል።

በዚህ በአካባቢው አስተዳደር የቀረበ ክስ ዙርያ ከሀገራዊው የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ማብራሪያ ለማግኘት በስልክ፣ በአጭር የፅሑፍ መልእክት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ለመፍታት እንዲሁም የተረጂ መጠን ለመቀነስ በዘላቂ መፍትሔ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት የሚያነሱት የትግራይ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር ዶክተር ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው መመለስ፣ ኢኮኖሚው የሚያነቃቁ እርምጃዎች መውሰድ እንዲሁም የስራ ዕድሎች መፍጠር ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW