1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ክልል የሚሞቱን ሕፃናትና እናቶች ቁጥር እየጨመረ ነዉ

ረቡዕ፣ ጥር 8 2016

ለሁለት ዓመት በትግራይ የተደረገው ጦርነት በጤና መሰረተ ልማቱ እና የጤና ስርዓቱ ላይ ያደረሰው ጥፋት የዳሰሰ የትግራይ ጤና ቢሮ፥ 80 በመቶ በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት በተለያየ መጠን የሚገለፅ ውድመት እንደደረሳቸው ይገልጻል።

የጤና ሚንስትር ሊያ ታደሰ በጎብኝታቸዉ ወቅት ከሐኪሞችና ታካሚዎች ጋር ተነጋግረዋል
የኢትዮጵያ የጤና ሚንስትር ሊያ ታደሰ መቀሌን በጎበኙበት ወቅትምስል Million Hailesilassie/DW

በትግራይ ክልል የሚሞቱን ሕፃናትና እናቶች ቁጥር እየጨመረ ነዉ

This browser does not support the audio element.

         

የትግራይ ክልል የጤና ስርዓት በመፍረሱ በሕክምና እጦትየሚሞቱትና በምግብ እጥረት የሚሰቃዩት እናቶች እና ህፃናት ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ ። የትግራይ ጤና ቢሮ እንደሚለው በክልሉ ከሚገኙ እርጉዝና የሚያጠቡ እናቶች መካከል 61 በመቶዎቹ ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል። የየህፃናት ሞትም ከጊዜ ወደጊዜ እጨመረ ነዉ።ቢሮዉ እንደሚለዉ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት በተደረገዉ ጦርነት በክልሉ ከሚገኙ የጤና ተቋማት 80 በመቶ ያክሉ ወድመዋል ወይም ተጎድተዋል።

ለሁለት ዓመት በትግራይ የተደረገው ጦርነት በጤና መሰረተ ልማቱ እና የጤና ስርዓቱ ላይ ያደረሰው ጥፋት የዳሰሰ የትግራይ ጤና ቢሮ፥ 80 በመቶ በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት በተለያየ መጠን የሚገለፅ ውድመት እንደደረሳቸው ይገልጻል። ከዚህ ውጭ ለዓመታት በተሰሩ ተግባራት ተቀይረው የነበሩ በተለይም ከእናቶች እና ጨቅላ ህፃናት ጤና ጋር የተያያዙ ተግባራት ወደኃላ መመለሳቸው፣ የጤና ስርዓቱ መፍረሱ ተከትሎም በተለይም በትግራይ የህፃናት ሞት በአራት እጥፍ ማደጉ የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀው እና ትላንት በመቐለ በተደረገው ሀገራዊ የእናቶች እና ህፃናት ጤና መድረክ ላይ የተናገሩት የትግራይ ጤና ቢሮ ሐላፊ ዶክተር አማኑኤል ሃይለ፥ በትግራይ የጤና አገልግሎት ፈላጊ ቁጥር እና የአገልግሎት አቅርቦቱ አለመመጣጠን አስቸጋሪ ሆኖ እንዳለ ገልፀዋል።

በትግራይ፣ በጦርነቱ ወቅት አብዛኞቹ የጤና ተቋማት በመዉደማቸዉና በክልልሉ በገባዉ ረሐብ ምክንያት የእናቶችና የህፃናትን ሞት ጨምሯልምስል Million Hailesilassie/DW

ረሃብ እና የጤና መታወክ በእናቶች እና ህፃናት ዘላቂ ህይወት ላይ የከፋ ጫና እየፈጠረ መሆኑ ጨምረው የሚያነሱት ሐላፊው በትግራይ ከሚገኙ እርጉዝ እና የሚያጠቡ እናቶች መካከል 61 በመቶዎቹ የምግብ እጥረት ወይም ማልኒዩትሪሽን የተጋለጡ መሆኑ አንስተዋል። 

አጠቃላይ በትግራይ ያለው ረሃብ፣ የሕክምና አገልግሎት አቅርቦት ውሱንነት እንዲሁም የተለያዩ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በተለይም የእናቶች እና ህፃናት ህይወት ለአደጋ ማጋለጣቸው ተመላክቷል። በጦርነቱ ምክንያት በደረሳቸው ውድመት እና የአቅርቦት እጦት ከስራ ውጭ ሆነው የቆዩ በትግራይ የሚገኙ ጤና ተቋማት በአብዛኛው ወደ ስራ እየተመለሱ ቢሆንም፥ በጤና መሳርያዎች እጦት እና የደረሳቸው ውድመት እየተፈተኑ ይገኛል ተብሏል። ይህ ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እየሰራ ስለመሆኑ ሚኒስቴርዋ ዶክተር ሊያ ታደሰ ይገልፃሉ። 

በትግራይ ትልቁ የሆነው እና ከመላው ትግራይ፣ ከአጎራባች የአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎች የሚመጡ ታካሚዎች የሚያስተናግደው ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታልም ቢሆን ፈተና ላይ ይገኛል። ሆስፒታሉ በበጀት እጦት ምክንያት የተለያዩ የጤና አገልግሎቶች ያቋረጠ ሲሆን በተደጋጋሚ የድጋፍ ጥሪም እያሰማ ይገኛል። ተቋሙ የጎበኙት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ዶክተር ሊያ ታደሰ "ሆስፒሉ ለመደገፍ እየተሰራ ነው" ይላሉ።

ከትግራይ እናቶች ከ60 ከመቶ የሚበልጡት በምግብ እጥረት ይሰቃያሉምስል Million Hailesilassie/DW

በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም በትግራይ የሚገኙ አብዛኞቹ ጤና ተቋማት ወደ ስራ መመለሳቸው የተገለፀ ሲሆን ተቋርጠው የነበሩ የህፃናት መደበኛ ክትባቶች እንዲሁም ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችም ተጀምረዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW