1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በትግራይ ክልል የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ረቡዕ፣ መስከረም 7 2018

ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን እና ሌሎች አካባቢዎች በዜጎች ላይ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን አስታወቀ። በሌላ በኩል ከትግራይ ኃይሎች ተለይተው በአፋር ክልል ሲደራጁ በነበሩ ታጣቂዎች መካከል ክፍፍል መፈጠሩን ተከትሎ በርካቶች ያለፍርድ ለረዥም ጊዜ ታስረው ይገኛሉ ብሏል።

የትግራይ ክልል ዋና መዲና መቀለ
የትግራይ ክልል ዋና መዲና መቀለ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ EDUARDO SOTERAS/AFP

በትግራይ ክልል የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች

This browser does not support the audio element.

 

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ያወጣው የምርመራ ዘገባ እንደሚያሳየው በትግራይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲሁም እሱን ተከትለው የተወሰዱ እርምጃዎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አስከትለዋል። ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች እንዳለው በሐምሌ ወር በዓዲጉደም ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጉ በነበሩት ላይ በተከፈተ ተኩስ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን፣ በነሐሴ ወር አጋማሽ ደግሞ በመኾኒ በተፈጠሩ ኹነቶች፥ የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ ከፍተው የከተማዋ ነዋሪዎች በሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክቷል። 

የታጣቂዎች እርምጃ

የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ዳይሬክተር ተስፋዓለም በርኸ፥ መኾኒን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች እየተፈፀሙ ላሉ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያሰማራቸው ታጣቂዎች መሆናቸውን ያነሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ከትግራይ ኃይሎች ተለይተው በአፋር እየተደራጁ ስላሉ ታጣቂዎች ጉዳይ በዘገባው ውስጥ ያካተተ ሲሆን፥ በመካከላቸው በተፈጠረ ልዩነት ምክንያትም በአፋር ክልል ዱብቲ ከተማ በሚገኝ እስርቤት 12 ሰዎች ፍርድቤት ሳይቀርቡ ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ እንደሚገኙ መረጃ ማሰባሰቡን አስታውቋል። 

በአፋር ያሉ የትግራይ ታጣቂዎች 

በቅርቡ ሸዊት ቢተውን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሰመራ ወደሚገኝ መደበኛ ፖሊስ ጣብያ ተወስደው መታሰራቸውን፥ ሌሎች የተቀሩት ደግሞ እዛው ዱብቲ እንዳሉ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች አመልክቷል። የድርጅቱ ዳይሬክተር ተስፋዓለም በርኸ የታሰሩት ፍርድቤት የመቅረብ መብታቸው መጠበቅ አለበት ብለዋል። 

በእነዚህ ኹነቶች በትግራይ እና አፋር ሰብአዊ፣ ሕገመንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጣሳቸውን የገለፀው ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የኃይል እርምጃ በወሰዱ ታጣቂዎች ላይ ምርመራ በማድረግ እርምጃ እንዲወስድ፣ የአፋር ክልል መንግሥትም በግዛቱ ውስጥ ያሉ ታሳሪዎችን ጉዳይ ተመልክቶ መፍትሔ እንዲያበጅ ጠይቋል። 

የመንግሥት እርምጃ 

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ሕገመንግሥታዊ እና ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች የመጠበቅ ሐላፊነቱን እንዲወጣ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ጥሪ አቅርቧል። በተለይም ከአፋር ክልል ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጉዳይ አስመልክቶ ከክልሉ ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW