በትግራይ ክልል የቀጠለው የተፈናቃዮች ችግር
ረቡዕ፣ መስከረም 14 2018
በኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች መካከል በ2013 ዓመተ ምሕረት የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ከቀዬአየው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ ዜጎች ከባድ ሕይወት እየገፉ እንዳለ ይገልፃሉ። ከየቀዬየው ተፈናቅለው በድንኳኖች መኖር ከጀመሩ አምስት ዓመት የሞላቸው እነዚህ ወገኖች በእርዳታ እጦት፣ በክረምት ዝናብ እና በበጋ ፀሓይ ከመፈተን በዘለለ ትናንት በመቐለ ሰብዓ ካሬ የተፈናቃዮች መጠለያ ያጋጠመው ክስተት በርካቶችን አሳዝኗል።
በጅብ የተጠቃ ሕጻን
በመጠለያው የሚኖሩ ተፈናቃዮች በአካባቢው በርካታ ጅቦች መኖራቸውን የሚናገሩ ሲሆን ትናንት ጠዋት ናኡድ የተባለ ሁለት ዓመት ያልሞላው ሕጻን በጅብ ተጠቅቶ መሞቱን ሰምተናል። በመቐለ ሰብዓ ካሬ መጠለያ ውስጥ የሚኖሩት ተፈናቃይ አቶ ግደይ ንጉሥ፥ ሰዎች ደርሰው ሕጻኑን ከጅብ ለማዳን ቢሞክሩም መሞቱ ንይናገራሉ።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ተፈናቃዩ ወገን ከባድ ሕይወት እየገፋ ስለመሆኑ ይናገራሉ። አንድ ተፈናቃይ በበኩላቸው «በተቀደደ የመጠለያ ድንኳን ነው እየኖርን ያለነው። ሕጻኑ ልጅ ድንገት ወደ ውጭ ሲወጣ ጅቡ አንጠልጥሎት ሮጠ። ደርሰን ለማስጣል ሞከርን፣ ሕጻኑ ልጅ ግን በሕይወት አልተረም። በበርካታ መከራ ላይ እየኖረ ያለ ሕዝብ አሁንም በችግር እየተፈተነ ነው። ከቀዬአችን ተፈናቅለን፥ አሁን ደሞ በአራዊት እየተጠቃን ነው» በማለት ያሉበት ሁኔታ ገልጸዋል።
ዘጠኝ መቶ ሺህ ተፈናቃዮች
በተለይም ከምዕራብ ትግራይ ዞን የተፈናቀሉ የሚበዙበት በአጠቃላይ ከዘጠኝ መቶ ሺህ በላይ የሚደርሱ ተፈናቃዮች በክልሉ የተለያዩ መጠለያዎች ተጠግተው ይኖራሉ። መንግሥት ወደ ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው በተደጋጋሚ የሚጠይቁት እነዚህ ተፈናቃዮች፥ ለዚህ ጥያቄ የሚጠበቀው ምላሽ ሳይገኝ ዓመታት መቆጠሩን ይናገራሉ። ከሰቲት ሑመራ ከአምስት ዓመት በፊት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉት አቶ ግደይ ንጉሥ፥ ለተፈናቃዩ ይቀርብ የነበረ እርዳታም መቀየሱን ያነሳሉ።
የህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ውዝግብ
በተፈናቃዮች ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ክልል አስተዳደር የሚወዛገቡ ሲሆን፥ የፌደራሉ መንግሥት ህወሓት የተፈናቃዮችን አጀንዳ ለፖለቲካ እየተጠቀመበት ነው በማለት ሲከስ ይሰማል። በሌላ በኩል ከህወሓት ጀምሮ የትግራይ አስተዳደር የትግራይ ሕገመንግሥታዊ ግዛት እንዲመለስ እና ተፈናቃዮች ደኅንነታቸው ተጠብቆ ወደቀዬአቸው እንዲገቡ በማድረግ በኩል ኢትዮጵያ መንግሥት ሚናው አልተወጣም ይላሉ። በዚህ ውዝግብ መሐል ተፈናቃዮች በአስከፊ ሁኔታ እየኖሩ መሆኑን ይገልጻሉ።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ