በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው የኮሌራ ወረርሽኝ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 22 2016በተለይም ከጦርነቱ በኋላ የጤና ስርዓቱ ተዳክሞ ባለበት ትግራይ፥ ኮሌራን ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎች በወረርሽኝ ደረጃ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ነው። ከአንድ ወር በፊት በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ ከተገኘው የመጀመርያ የኮሌራ በሽተኛ በኋላ፥ በቀናት ጊዜ ውስጥ ወደ ተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተሰራጨ ሲሆን፥ አሁን ላይ በትግራይ 25 ወረዳዎች በሽታው አደጋ ፈጥሮ እንዳለ ተገልጿል። እንደ የትግራይ ጤና ቢሮ መረጃ አሁን ላይ በክልሉ በየቀኑ ከአስር በላይ የኮሌራ በሽተኞች በምርመራ የሚለዩ ሲሆን፥ ወረርሺኙ ከታየበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ ሰባት ሰዎች በኮሌራ ምክንያት መሞታቸውን አስታውቋል። በኮሌራ ምክንያት ከሞቱት በተጨማሪ በትግራይ 326 ሰዎች በአንድ ወር ውስጥ በበሽታው የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህ መካከል 250 የሚሆኑት ሕክምና ተደርጎላቸው መዳናቸውን በትግራይ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል እና ጤና ማበልፀግ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሚኪኤለ ሓጎስ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ 63 የኮሌራ በሽተኞች በሆስፒታሎች ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑም ተነግሯል። የክልሉ አስተዳደር የተፈጠረውንየኮሌራ ወረርሽን ለመከላከልእየሠራ መሆኑ የሚገልፅ ሲሆን በስፋት በሽታው በተሰራጨባቸው ሰሜን ምዕራብ እና ማእከላዊ ዞኖች ባለሙያዎች መሰማራታቸውንም አስታውቋል። በኮሌራ መከላከል ዘመቻ ከተሰማሩት የሕክምና ባለሙያዎች መካከል አቶ ሐጎስ ደጋፊ «በእኛ ካርታ ወይም ከፍተኛ ተጠቂ ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ልየታ አድርገን፥ እነዚህ አካባቢዎች ላይ ነው እየሠራን ያለነው። በእነዚህ አካባቢዎች ነው ቅድሚያ ሰጥተን የመከላከል ሥራዎቻችን እየሠራን ያለነው» ይላሉ።
በትግራይ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል እና ጤና ማበልፀግ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሚኪኤለ ሓጎስ እንደሚሉት በነበረው ሁኔታ የጤና ስርዓቱ በመፍረሱ ኮሌራን ለመከላከል አስቸጋሪ እንዳደረገው ያነሳሉ። ወረርሽኙን ለመግታት የክልሉ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ እንደሚጠብቅ ይገልፃል።
ሚሊየን ኃይለሥላሴ
ሸዋየ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ