1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ክልል የእርዳታ ስርቆትና የእርዳታ መቋረጥ ስጋት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 26 2015

በትግራይ ክልል ለሚገኙ ተረጂዎች ይቀርብ የነበረ የምግብ እርዳታ መቋረጡ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ይበልጥ የሚያባብስ ነው ተባለ። የዓለም ምግብ ድርጅት ለትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሙሉበሙሉ ካቆመ ከ20 ቀናት በላይ ማለፉን የክልሉ አስተዳደር አስታውቋል።

Äthiopien Tigray Konflikt Symbolbild
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

«የእርዳታ መቋረጥ ስጋት ማስከተሉ»

This browser does not support the audio element.

በትግራይ ክልል ለሚገኙ ተረጂዎች ይቀርብ የነበረ የምግብ እርዳታ መቋረጡ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ይበልጥ የሚያባብስ ነው ተባለ። የዓለም ምግብ ድርጅት ለትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሙሉበሙሉ ካቆመ ከ20 ቀናት በላይ ማለፉን የክልሉ አስተዳደር አስታውቋል።  ትናንት ከዓለም የምግብ ድርጅት በኩል የተሰማው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ተቋሙ ለትግራይ ክልል የሚሰጠው የምግብ እርዳታ ያቋረጠው ለችግረኞች መከፋፈል ይገባው የነበረ እህል በተደጋጋሚ በመዘረፉ እና በመሸጡ መሆኑን ይገልፃል። በዚህ ጉዳይ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት በትግራይ አደጋ መከላከል ኮሚሽን የአስቸኳይ ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረ እግዚአብሔር አረጋዊ፥ የዓለም የምግብ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት የሚያቀርቡትን የምግብ ድጋፍ ካቋረጡ 20 ቀናት እንዳለፈ ጠቁመዋል። በትግራይ ክልል የእርዳታ እህል በተደጋጋሚ ስለመዘረፉ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ክልሉ በተለያዩ ኃይሎች እየተዳደረ መሆኑን በማንሳት፣ በትግራይ ለተዘረፉ መጋዝኖች የውጭ ኃይሎች እጅ እንዳለበት አንስተዋል። የትግራይ ኃይሎች አልያም አስተዳደር ባሉባቸው ወይም በነበሩባቸው አካባቢዎች አንድም የተዘረፈ የምግብ እህል መጋዝን የለም ያሉት ኃላፊው፥ ይኽን በማስረጃ ጭምር ማረጋገጥ ይቻላል ብለውታል። ይህ እንዳለ ሆኖ የዓለም ምግብ ድርጅት ለትግራይ ሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ ማቋረጡን አስደንጋጭ ያሉት ሲሆን፣ ውሳኔው ከስድስት ሚልዮን በላይ የሚሆን በትግራይ ያለው እርዳታ ፈላጊ ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ሲሉ አክለዋል።

ምስል Million Hailesilassie/DW

ከእርዳታ ምግብ መሸጥ ጋር በተያያዘ ማብራርያ የሰጡት ዳይሬክተሩ፣ በመቐለ ገበያዎች በትግራይ የማይከፋፈል የዓለም ምግብ ድርጅት አርማ ያላቸው የምግብ አይነቶች ጭምር ሲሸጡ እንደሚስተዋል የጠቆሙ ሲሆን፥ በዓፋር ጨምሮ በተለያዩ አጎራባች ክልሎች የሚታደል እርዳታ በትግራይ የተሻለ ዋጋ ስለሚያወጣ በሕገወጥ ነጋዴዎች ወደ ትግራይ ክልል ገብቶ ሲሸጥ ታዝበናል፣ ይኽን ለማስቀረት የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ብለዋል።

ከዚህ ውጭ በትግራይ ክልል ያሉ ተረጂዎች ገንዘብ ለማግኘት የተሰጣቸውን እርዳታ የሚሸጡበት አጋጣሚ መኖሩም አንስተዋል። የእርዳታ ምግብ ሽያጭ ለማስቀረት የትግራይ ክልል አስተዳደር የዓለም ምግብ ድርጅት፣ USAID እና ሌሎች እርዳታ አቅራቢ ተቋማት አርማ ያላቸው የእርዳታ ምግቦችን ከነጋዴዎች እና ሸማቾች በመንጠቅ ለእርዳታ ድርጅቶቹ የመመለስ ሥራ እየከወነ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

በዚህ መሀልም በትግራይ ክልል የሚገኙ እርዳታ ፈላጊዎች፣ ለረዥም ግዜ እርዳታ ሳያገኙ መቀጠላቸው ገልፀውልናል። በዓብይ ዓዲ የሚገኙ ተፈናቃይ እና ተረጂ አቶ ብርሃነ እና ቤተሰቦቻቸው ለመጨረሻ ግዜ የምግብ እርዳታ የተሰጣቸው ከሦስት ወር በፊት እንደነበረ ይገልፃሉ። ብርሃነ «የካቲት ወር ነበር እርዳታ የተሰጠን፣ ከዛ በኋላ የለም። እዚህ ያለ ህዝብ ከፍተኛ ችግር ላይ ነው» ይላሉ። ተረጂዎቹ ያሉ ችግሮች በአፋጣኝ ተቀርፎ ሕይወት አድን እርዳታ ቶሎ እንዲሰጣቸው ይማፀናሉ።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW