1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በትግራይ ክልል ድርቅ የሰዎችን እንስሳትን ሕይወት መቅጠፉ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 29 2017

በድርቅ በተጠቃችው የትግራይ ቆላ ተምቤን ወረዳ 22 ሰዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ። በተጨማሪም በድርቁ ምክንያት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ከብቶች እና ሌሎች እንስሳት ማለቃቸው ተገልጿል።

በትግራይ ክልል ድርቅ የተከሰተበት አካባቢ
በትግራይ ክልል ድርቅ የተከሰተበት አካባቢ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Mariel Mueller/ Haileselassie Million/DW

በትግራይ ክልል ድርቅ የሰዎችን እንስሳትን ሕይወት መቅጠፉ

This browser does not support the audio element.

 

በድርቅ በተጠቃችው የትግራይ ቆላ ተምቤን ወረዳ 22 ሰዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ። በተጨማሪም በድርቁ ምክንያት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ከብቶች እና ሌሎች እንስሳት ማለቃቸው ተገልጿል። እስካሁን ወደ አካባቢው የደረሰ ድጋፍ አለመኖሩ ተነግሯል።

ከጦርነት በኋላ በከፋ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ውስጥ በሚገኘው የትግራይ ክልል ተፈጥሮአዊ ክስተቶች ተጨማሪ ጫና እየፈጠሩ ነው። እንደ ክልሉ አስተዳደር ቁጥራዊ መረጃዎች በትግራይ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 2.4 ሚልዮን ሕዝብ የምግብ እርዳታ የሚፈልግ ሲሆን በአንዳንድ የክልሉ ወረዳዎች በተከሰተ ድርቅ ደግሞ በሰዎችና እንስሳት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ ሆኖ እንደሚገኝ ተገልጿል። 

በማዕከላዊ ትግራይ ዞን ቆላ ተምቤን ወረዳ በሚገኘው ያቄር የተባለ አካባቢ ለረዥምጊዜ ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ እንዳለ ለዶቼቬለ የገለፁት የወረዳው የኢኮኖሚ እና ገጠር ልማት ዘርፍ ሐላፊ አቶ ጎይትኦም ገብረ ሐዋርያ፤ በቆላማ ያቄር ቀበሌ ብቻ ካለፈው ግንቦት ወር ወዲህ በረሃብ ምክንያት ሰባት ሕጻናትን ጨምሮ 22 ሰዎች መሞታቸው መረጋገጡን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶች እና ሌሎች እንስሳት በመኖ እጦት ምክንያት መሞታቸውንም አክለው ገልፀዋል። 

በአካባቢው ከተከሰተው ድርቅ በተጨማሪ መሠረተ ልማት አለመኖሩ ደግሞ ሁኔታውን የከፋ እንዳደረገው አቶ ጎይትኦሞ ገብረ ሐዋርያ ጨምረው ገልፀዋል።

ዛሬ ጨምሮ ሰሞኑን ከረሃብ ጋር በተያያዘ በሰዎች እና እንስሳት የሚደርስ ጉዳት መቀጠሉ የሚያነሱት ሐላፊው፥ እስካሁን በመንግሥት ይሁን በእርዳታ ድርጅቶች የተደረገ ተጨባጭ ድጋፍ አለመኖሩንም ጠቁመዋል። 

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ዓለም አቀፍ ተቋማት ያደርጉት የነበረ የምግብ እርዳታ መጠን መቀነሱ እንዲሁም እንዳንዶች እርዳታ ሰጪ ተቋማት አቅርቦት ማቋረጣቸውን ተከትሎ በትግራይ ካለውም የከፋ ሰብአዊ ቀውስ እንዳይከሰት ስጋት መኖሩን የክልሉ ባለሥልጣናት ሲገልፁ ቆይተዋል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW