ነዋሪዎችን ያሰጋው በሰሜን ኢትዮጵያ ያጠላው የጦርነት ዳመና
ቅዳሜ፣ የካቲት 14 2018
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የመቀለ ከተማ ነዋሪ ከባለፈው ሰኞ የካቲት 09 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በነዋሪዎች ዘንድ መረጋጋት አይታይም ይላሉ፡፡ ከሳምንታት በፊት ትግራይ ክልልን በሚያዋስኑ የአማራ እና አፋር ክልሎች ውስን ቦታ ላይ ግጭት በመከሰቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል የሚያደርገውንም በረራ ባቋረጠበት ወቅት የተስተዋለው አለመረጋጋት ከፍተኛ እንደነበር ሁሉ ያነ የነገሮች መርገብ ተከትሎ መልሶ የተስተዋለው መረጋጋት አሁን ላይ በዚህ ሳምንት እንደገና ውጥረት ውስጥ ገብቷልም ነው ያሉት፡፡ “አሁን ከባድ ጭንቀት ነው የሚታየው” የሚሉት አስተያየት ሰጪው የመቀለ ነዋሪ፤ “በተለይም በህወሓት አመራሮች ተዘጋጁ የሚሉ መልእክቱች ጦርነትን ፈጽሞ የማይፈልገውን ህዝብ ረብሾታልም” ብለዋል፡፡ እናም በርካታ የክልሉ ህዝብ ክልሉን ጥለው ለመውታት እየተሰለፈ ነው ብለዋል፡፡
በተፈጠረው አለመረጋጋት የታየው የኑሮ መናጋት
ማህበረሰቡ ውስጥ እየታየ ባለው አለመረጋጋት የሸቀጦችም ዋጋ መናሩን የገለጹት አስተያየት ሰጪው እየታየ ያለውን ሁኔታ መጥፎ ሲሉ ገልጸውታል፡፡ “አለመረጋጋቱ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲታይ አድርጎታልም” ያሉት ነዋሪው፤ ያለውን ሁኔታ ከስራ እጦት ጋር ተጨምሮ መትፎ ሁኔታ ነው ሲሉም ገልጸውታል፡፡ሌላም አስተያየት ሰጪ የክልሉ ነዋሪ ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው በሰጡን አስተያየት፤ “ሰው እየወጣ ነው፤ ብርም ደግሞ በተለይም ካሽ ከባድ እትረት አለ” ብለዋል፡፡ሌላም አስተያየት ሰጪ አከሉ፤ “እኔ አሁን መውጣት እፈልጋለሁ ግን ደግሞ ሁሉም ሰው ወደ አዲስ አበባ ስለሆነ እየወጡ ያሉት ስራም እንዳላጣ ብዬ እየታገስኩ ነው፡፡ የከፋ ከመጣ ግን እኔም መውጣቴ የማይቀር ነው” ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
እየወጡ ያሉ የማህበረሰብ አካላት የትኞቹ ናቸው
በክልሉሊቀሰቀስ ይችላል ተብሎ የተሰጋውን ጦርነትተከትሎ ወጣቶችን ጨምሮ ሌላ አከባቢ ሄደው ህይወትን የመምራት አቅም ያለው ሁሉ ሊመጣ የሚችለውን በመስጋት እየወጡ እንደሉም አስተያየት ሰጪዎቹ ነዋሪዎች አክለው ተናግረዋል፡፡ “አማራጭ ያው ሰው፤ በተለይም አዲስ አበባወይም በሌላ የአገሪቱ አከባቢዎች አንዳንዴም ወደ አረብ አገርም የሚሄዱ ብዙ ናቸው” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ ሌላ ቦታ ስራ የመስራት አቅም ያላቸው ሰዎችም ከክልሉ ለመውጣት እያመነቱ አይደለም ብለዋል፡፡
የተስተዋለው የትራንስፖርት መጨናነቅ
በርካታ ነዋሪዎችበተለይም ከባለፈው ሰኞ ወዲህ የመውጣት ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ የትራንስፖርት ወረፋው ተጨናንቆ ታይቷልም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፤ “አዲስ አበባ ያሉ ሁሉም አይነት የባስ ኩባንያዎች በዚህ ቢሮ ከፍተው ሰው እያጋዙ ነው” በማለት የየብስ እና የአየር ትራንስፖርቱን የሚጠቀሙ በርካታ የክልሉ ማህበረሰብ በእየለቱ ወጥተው ስሰለፉ ነው የሚታየው ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው እሮብ የካቲት 11 ቀን 2018 ዓ.ም. የህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትራይ (ህወሓት) 51ኛ የምስታ በዓል ላይ ንግግር ያደረገጉት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ አሁን ላይ የታየውን ውጥረት ወደ ሰላም ለመቀየር ጠባብ እድል ብቻ ቀርተውታል ብለዋል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ደግሞ በክልሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ወደ ቀደመው ይዞታዎች የመመለስ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨውን መረጃ አስተባብሏል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በኤርትራ እና ኢትዮጵያ መንግስታት መካከል የነገሰውን ውጥረት ተከትሎ አገራቱ ጦራቸውን ወደ ድንበር እያስጠጉ ነው በሚል በሳምንቱ በስፋት ተዘግቧል፡፡
ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ውጥረት በሚሰማበት ባሁን ወቅት ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ስብሰባ ተቀምጧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባውን የተቀመጠው “በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት” እንደሆነ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ፀሐይ ጫኔ