በትግራይ የሚገኝ የተመድ መጋዘን ዘረፋ እንደተፈፀመበት ድርጅቱ አስታወቀ
ማክሰኞ፣ መስከረም 26 2019
ትግራይ ክልል የሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መጋዘን ሰሞኑን መዘረፉን ድርጅቱ አስታውቀ።ይሁንና ድርጅቱ ጦርነት በተደረገና በሚደረግባቸዉ በትግራይና በአፋር ክልሎች የዕርዳታ ለማቅረብ እየጣረ መኾኑን፣ የድርጅቱ ዋና ፀኃፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ ትናንት በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።የአውሮጳ ኀብረትና ዩናይትድ ስቴትስ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተባባሰው ውጥረት እንዲረግብ ጠይቀዋል።
(ተመድ) ዋና ፀኃፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሀክ ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ነው። ተፈናቃዮችን ጨምሮ የሲቪሎችን መሞትና መቁሰል በተመለከተ እየወጡ ያሉ ረፖርቶች በእጅጉ ያሳስቡናል ብለዋል።
የተመድ መጋዘን መዘረፍ
በትግራይ ክልል ከትናንት ወዲያ ተፈፀመ ያሉትን ዘረፋም ጠቅሰዋል።እሳቸው እንዳሉት፣ በክልሉ የሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጋዘን እንደዚሁም መንግሥታዊ ያልኾኑ አለምአቀፍና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች መጋዘኖችና ሌሎች ተቋማት ተዘርፈዋል። በዚህም ምክንያት፣ ምግብን፣ ዘርን፣ ማዳበሪያንና የውሃ መሳቢያዎችን ጨምሮ፣ ሰብአዊ አቅርቦቶች መወሰዳቸውን አመልክተዋል- ዘረፋው በማንና እንዴት እንደፈፀመ ግን አላብራሩም። የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኛች፣ መስሪያ ቦታዎችና ንብረቶች በፍጹም ኢላማ መኾን እንደሌለባቸውና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ሀክ ተናግረዋል። የስልክና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ከአንድ ሳምንት መቋረጥ በኋላ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ እንደገና በመጀመሩ ተበረታተናል ያሉት ምክትል ቃል አቀባዩ፣ ሁኔታው ለሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች አመች ሁኔታ እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
"ይህ ሰዎች ለመሰረታዊ አገልግሎቶች ይበልጥ ተደራሽ እንዲኾኑ ያግዛል፣ የሰብአዊ ድጋፍ እንቅስቃሴዎችንም አመች ያደርጋል። ምግብና የጤና ድጋፍን ጨምሮ የእርዳታ አቅርቦት ስራዎችን በትግራይ እንደዚሁም በአፋር ለመቀጠል ዝግጅቶች በመካሄድ ላይ ናቸው" ብለዋል።
የአወሮፓ ኀብረትና የዋሽንግተን ሰጋት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ስራውን በትግራይናበአፋር ክልሎች ለመቀጠል እየተዘጋጀ መኾኑን ያስታወቀው፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በተለይ ወደ ጎረቤት ኤርትራም እንዳይስፋፋ ስጋቶች በቀጠሉበት ወቀት ነው። የአውሮፓ ኀብረት ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት እንደዚሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተባባሳው ውጥረት እንዳሳሰበው አስታውቋል። በሁሉም ግንባሮች ያሉ ውጥረቶች እንዲረግቡም ጥሪ አቅርቧል። ሁሉም ወገኖች ውጥረትን ሊጨምሩ ከሚችሉ ተግባራትና ንግግሮች እንዲቆጠቡም ጠይቋል። የፕሪቶሪያውን ግጭት በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት የተፈራረሙ ወገኖችም፣ በአፍሪካ ኀብረት ማዕቀፍ መሰረት ለሙሉ ተግባራዊነቱ ራሳቸውን ማስገዛት እንዳለባቸው አሳስቧል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫደግሞ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እየጨመረ የመጣው ውጥረት፣ በቀጠናው በሙሉ ጉዳት የማድረስ አቅም እንዳለው አስታውቋል። የአፍሪካ ቀንድ ሌላ ግጭትና ሰብአዊ ቀውስ መቋቋም አይችልም ብሏል። ግጭት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከኹለቱም ሀገራት ጋር እየፈጠረች ያለውን በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር አደጋ ላይ የሚጥል መኾኑንም አመልክቷል። የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር እንጋላ ቾሜ እንደሚሉት፣ የዋሽንግተን መግለጫ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ጭምር መነሻ ያደረገ ነው።
"ለዚህ ውሳኔ ምክንያት የኾኑ ከንግድ ጋር የተገናኙ ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። የአሜረካ መንግሥት በተለይ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የማስፋፊያ ስራ ጋር በተያያዘ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነቶችን የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አለው። እየተነጋጋርን ያለነው በቢሊዮን ስለሚቆጠር ዶላር ነው" በማለት አብራርተዋል።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የቀጠለው ውጥረት
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት የተካረረውና ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ያቋረጡት፣ በቀይ ባሕር ያለው ሁኔታም አሳሳቢ ሆኖ በቀጠለበት ወቅት ነው። የሁቲ አማጺያን በየመን የቀይ ባሕር ዳርቻ በኩል ያደረጉትን ፈጣን ግስጋሴ ተከትሎ፣ አለምአቀፍ እውቅና ባለው የየመን መንግሥት እንደዚሁም በሳዑዲ አረቢያ በሚመራው ጥምረት እየተወሰደ ያለው የአፀፋ ጥቃት ተጠናክሮ ቀጥሏል። አማጺያኑም ጥቃታቸውን አላቋረጡም። የዋሸንግተን መግለጫ የቀይ ባሕሩን ሁኔታ ይበልጥ የሚያወሳስብ ግጭት እንዳይፈጠር ከመስጋት ጋር ጭምር የተያያ
የመነጨ መኾኑን ዶ/ር ቾሜ ያምናሉ። በአካባቢው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉም ጥቅማቸውን ከማስጠበቅ ጋር የተያያዘ መኾኑን አክለው በመጥቀስ አብራርተዋል።
"ይሄ ሁሉ፣ አሜሪካኖች በዚህ አስፈላጊ የውሃ መተላለፊያ ማለትም በቀይ ባሕርና በባብ ኤል መንደብ ለመገኘት መሻታቸውን መነሻ ያደረገ ነው- በዚህ ጠቃሚ የውሃ ላይ መተላለፊያ ያሉ ክስተቶችን ለመቆጣጠር እንዲያስችላቸው። እና፣ አዎ በርግጠኝት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት እየተመለከቱ ባሉበት ወቅት ሳይቀር በቀይ ባሕር ያለውን ሁኔታ ከግምት አስገብተዋል" በማለት አስረድተዋል።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት የተባባሰውባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነው። በአዲስ አበባ የሚገኙ አስር የኤርትራ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ ግዛቷን ለቅቀው እንዲወጡ ያዘዘችው ኢትዮጵያ፣ በአስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗንም አስታውቃለች።
ኤርትራ ተመሳሳይ እርምጃ ከመውሰድ ውጭ አማራጭ የላትም ያለው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም፣ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማቋረጧን ገልጿል።
እስክንድር ፍሬዉ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ