1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በትግራይ የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች ዕግድ “ትልቅ ጥሰት ነው” ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ መስከረም 20 2019

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የትግራይ ክልል ቅርንጫፎች የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች ዕግድ “ትልቅ ጥሰት ነው” የሚል አቋም እንዳላቸው የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል። እርምጃው በትግራይ እና ከክልሉ ውጪ የሚገኙ ደንበኞች ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እንዳይችሉ አድርጓል። ይህ የዕለት ተዕለት ወጪዎችን ለመሸፈን ችግር ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በአዲስ አበባ የሚገኙ ስድስት ሰዎች በትግራይ ክልል በሚገኙ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦቻቸውን ማንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ለዶቸ ቬለ ተናግረዋል። ምስል፦ Marco Simoncelli

በትግራይ የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች ዕግድ “ትልቅ ጥሰት ነው” ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ ክልል እየተደረገ የሚገኘው ውጊያ የቀድሞው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ከራሳቸው ችግር ይልቅ ስለ ቤተሰቦቻቸው ደሕንነት እንዲጨነቁ አድርጓቸዋል። “ወላጅ እናቴ መቐለ ነው ያለችው፤ ቤተሰቦቼም መቐለ ነው ያሉት። እስካሁን ምንም ነገር እየሰማን አይደለም” የሚሉት የቀድሞው የዩኒቨርሲቲ መምህር አዲስ አበባ ከገቡ አንድ ዓመት ገደማ ሆኗቸዋል።

ባሉበት ሆነው ከትግራይ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች የሚያረጋጋቸው መረጃ እያገኙ አይደለም። ዘላለም እንደ ቀድሞው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ሁሉ በትግራይ ክልል ዋና ከተማ ስለሚኖሩ ቤተሰቦቹ ዕጣ ፈንታ እየተጨነቀ ነው።

ከመቐለ ርቆ አዲስ አበባ ሲከትም የዕለት ተዕለት ሕይወቱን የሚፈታተን ችግር ቢገጥመውም የልጆቹ ነገር አብዝቶ ያሳስበዋል። ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆነው ዘላለም “በአየር እየተደበደቡ እንደሆኑ” ይሰማዋል።

ዘላለም የልጆቹን ድምጽ ከሰማ አምስት ቀናት ገደማ ሆኖታል። ቤተሰቦቹ ስላሉበት ሁኔታ የሚያውቀው ነገር የለም። ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ የሚሰማቸው መረጃዎች ሁሉ ዘላለም ከ2013 እስከ 2015 የተደረገው ጦርነት ያሳደረበትን የሥነ-ልቦና ጠባሳ መልሰው የሚቀሰቅሱ ናቸው።

ከጦርነት ወደ ጦርነት?

የትግራይ ኃይሎች ከፌድራል መንግሥት እና አጋሮቹ ጋር ለሁለት ዓመታት ባደረጉት ጦርነት በውጊያ፣ በረሐብ እና የጤና አገልግሎት እጦት ቢያንስ 600,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል ተብሎ ይገመታል። ጦርነቱ ካስከተለው ሰብአዊ ቀውስ ባሻገር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የፌድራል መንግሥት የጦርነት ወጪ በአራት እጥፍ አድጎ ከአገሪቱ በጀት ያለው ድርሻ 15 በመቶ ገደማ ደርሶ ነበር። በጦርነቱ መዋዕለ-ንዋይ ከኢትዮጵያ ሸሽቷል፤ መሠረተ-ልማቶች ወድመዋል።

የልማት አጋሮች ለመንግሥት ይሰጡ የነበረውን ድጋፍ ሲያቆሙ፤ አገሪቱ በአጎዋ በኩል ሸቀጦቿን በአሜሪካ ገበያ የመሸጥ ዕድሏን ተነጥቃለች። ጦርነት ከቆመ ከጥቂት ወራት በኋላ ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው ግምት አገሪቱ ለመልሶ ግንባታ 20 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚያስፈልጋት አስታውቆ ነበር።

በትግራይ ክልል በተከሰተ የብር እጥረት ምክንያት ዲጂታል ገንዘብ ማዘዋወሪያዎች ዋንኛ መገበያያ ሆነዋል።ምስል፦ REUTERS

የቀደመው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰባቸው የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ዳግም ደም አፋሳሽ ውጊያ መስከረም 12 ቀን 2019 የተቀሰቀሰው በቅጡ ሳያገግሙ ነው። የትግራይ ክልል በተለይ ህወሓት እና ፌድራል መንግሥት ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈራረሙ በኋላም ቢሆን በመካከላቸው በዘለቀው ቅራኔ በኃይል ሲፈተን ነበር።

በትግራይ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡት ብር በማጣታቸው ገንዘብ ማዘዋወሪያዎች ዋንኛ መገበያያ ሆነዋል። ነዳጅን ጨምሮ የመሠረታዊ ሸቀጦች እጥረት የክልሉን ኢኮኖሚ እግር ተወርች ከጠፈነጉ መሠረታዊ ችግሮች መካከል የሚጠቀስ ነው።

ኢኮኖሚው የገባበት ቅርቃር በመቐለ በግል ሥራ ይተዳደር ለነበረው ዘላለም አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ዘላለም በመቐለ ከተማ የተሽከርካሪዎች መለዋወጫ ዕቃዎች መሸጫ መደብር ነበረው። ከዚያ ባሻገር መኪና ያከራያል፤ የትራንስፖርት አገልግሎትም ያቀርባል። 

ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ

“ቢዝነስ በጣም አሪፍ ነበር” የሚለው ዘላለም ከጦርነቱ ወዲህ ባሉት ስድስት ዓመታት “ግን ጥሩ” እንዳልነበረ አስረድቷል። ጦርነቱ ከቆመም በኋላ ቢሆን “ነዳጅም አልነበረም፣ ባንክም አንዴ ይከፈታል አንዴ ይዘጋል” የሚለው ዘላለም በተለይ ባለፉት አምስት ገደማ ወራት ችግሩ እንደተባባሰ ገልጿል።

በትግራይ ክልል “አፈሳ በጣም ሲጠነክር” ዘላለም ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ አቀና። ከቤተሰቦቹ እንዲርቅ ያስገደደው በግዳጅ የሚደረግ ወታደራዊ ምልመላ በዋናነት የተጠናከረው ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከተመለሰ በኋላ ነው። በመቐለ “አፈሳ” የሸሸው ዘላለም በአዲስ አበባ የጠበቀው ግን ከባድ ፈተና ነው።

“አሁን አዲስ አበባ ሥራ እያፈላለግን ነው። እዚህ ሁሉም ሰዉ ስለመጣ ሥራ ሊገኝ አልቻለም። ኢኮኖሚው ከባድ ሆነ” በማለት ይናገራል። አዲስ አበባ በቆየባቸው ጊዜያት የዕለት ተዕለት ወጪውን የሚሸፍነው ቁጠባውን እያሟጠጠ እና ዕቃዎቹን “በማይሆን ዋጋ” ሸጦ መሆኑን ተናግሯል።

በአዲስ አበባ ሥራ አጥነት የገጠመው ዘላለም በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ ድንገት በመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለው የባንክ ሒሳብ ታግዷል።

በትግራይ የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች ያሏቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ስለ ዕግዱ የሰሙት ውጊያ እንደተቀሰቀሰ ነበር። ምስል፦ AFP

የታክሲ ለመክፈል ገንዘብ “ከንግድ ባንክ ወደ ቴሌ ብር” ለማስተላለፍ ሲሞክር “Error Error” የሚል መልዕክት ደረሰው። ለጊዜው በኪሱ በነበረው ገንዘብ የታክሲ ወጪውን ቢሸፍንም በፌስቡክ “ከትግራይ የመጣ ጠቅላላ አካውንት ተዘግቷል” የሚል መረጃ አገኘ። “ዝግጁ ስላልነበርን አሁን ምንም መንቀሳቀሻ የለንም” ሲል ተናግሯል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ሌሎች ስድስት ሰዎች በትግራይ ክልል በሚገኙ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦቻቸውን ማንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ለዶቸ ቬለ ተናግረዋል። ሁሉም ለምን የባንክ ሒሳቦቻቸው እንደታገዱ በግልጽ የተሰጣቸው ማብራሪያ የለም። ዶቸ ቬለ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የባንክ ሒሳቦች ላይ የተጣለው ዕግድ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ደንበኞች ጭምር ገንዘባቸውን እንዳያንቀሳቅዱ ማድረጉን የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ዋና ዳይሬክተር ተስፋለም በርሔ ለዶቸ ቬለ ተናግረዋል። “ትግራይ ውስጥ አልፎ አልፎ አንዳንድ አካባቢዎች የስልክ ግንኙነት አለ። እዚያ አካባቢ ያሉትም ገንዘብ ማዘዋወር እንዳልቻሉ፤ መጠቀም እንዳልቻሉ፤ በጣም ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደወደቁ ነግረውናል” ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “በትግራይ ክልል የተከፈቱ ሒሳቦችን ለማስለቀቅ የተመረጡ ቅርንጫፎችን” ለደንበኞቹ እንዳሳወቀ ዶቸ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። የቀድሞው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ከተመረጡት ቅርንጫፎች ወደ አንዱ ሲያመሩ በትግራይ በሚገኙ ቅርንጫፎች የባንክ ሒሳብ የከፈቱ “በጣም በብዙ ተጠቃሚዎች” ተሰልፈው መመልከታቸውን ገልጸዋል። በተሰለፉ ሰዎች ብዛት ምክንያት ተራቸው ደርሶ ለችግራቸው መፍትሔ ማግኘት አልቻሉም።

በተመሳሳይ የታገደው የባንክ ሒሳብ እንዲለቀቅለት ጥያቄ ያቀረበው ዘላለም ከሦስት እስከ አስር ቀናት መጠበቅ እንዳለበት ምላሽ ተሰጥቶታል። ወጪውን ለመሸፈን “ያለው ሰዉ ትንሽ ይሰጥኻል፤ ወይ ትበደራለህ” የሚለው ዘላለም “በጣም ነው የሚያሳዝነው” በማለት ስሜቱን አጋርቷል።  

ቤተሰቦቹን የሚያስተዳድረው ዘላለም ብር ከባንኮች ማግኘት ከባድ በሆነባት መቐለ የዲጂታል የገንዘብ ማዘዋወሪያዎች አገልግሎት ሲቋረጥ የሚከሰተው ያሰጋዋል። ዘላለም እንደሚለው “ምን እንደሚያደርጉ እግዚዓብሔር ነው የሚያውቀው።”

“ትልቅ ጥሰት ነው ብለን ነው የምንወስደው”

የቀድሞው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ከቤተሰቦቻቸው ያላቸው ግንኙነት በመቋረጡ “በምን አይነት ችግር ውስጥ እያለፉ እንደሆነ” ማሰብ ሥጋታቸውን ከባድ አድርጎታል።  “እንዲህ አይነት ሁኔታ እንደሚመጣ” ባለመገመታቸው ራሳቸውን ይታዘባሉ።  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን በትግራይ በሚገኙ ቅርንጫፎቹ የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች ዕግድን በተመለከተ በይፋ ያለው ነገር የለምምስል፦ Eshete Bekele/DW

የባንክ ሒሳብ ለታገደባቸው ምግብ እና መጓጓዣን የመሳሰሉ መሠረታዊ ወጪዎች መሸፈን እንደማይችሉ የገለጹት የቀድሞው የዩኒቨርሲቲ መምህር “የቀን ተቀን ሕይወት ላይ ከባድ የሆነ ጫና” እንዳለው አስረድተዋል። በቅርብ ጊዜ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ ያመሩ እና ከማኅበረሰቡ ያልተቀላቀሉ የሚያበድራቸው ስለማያገኙ የከፋ ችግር እንደሚገጥማቸው ሥጋታቸውን አጋርተዋል።

በትግራይ ክልል በአብዛኛው የኢንተርኔት አገልግሎት ቢቋረጥም በሽረ እና አክሱም አካባቢዎች የአቢሲኒያ ባንክ እየሠራ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን አቶ ተስፋለም በርሔ ለዶቸ ቬለ ተናግረዋል። በባንክ ሒሳቦች ላይ የተጣለው ዕግድ በተራዘመ ቁጥር “ትልቅ ውድቀት” እንደሚያስከትል የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ያላቸውን ሥጋት እንደገለጹላቸው አስረድተዋል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ያገኘንው መረጃ የለም” የሚሉት አቶ ተስፋለም “የፋይናንስ ተቋማት የደሕንነት ሁኔታ እና ማጭበርበር ሊኖር ይችላል የሚል ሥጋት ካደረባቸው ማድረግ እንደሚችሉ የዓለም አቀፍ ሕጉም አንዳንዴ የሚፈቅድላቸው ነገር አለ” ሲሉ ተናግረዋል። ይሁንና ባንኮች እንዲህ አይነት እርምጃ መውሰድ የሚችሉት እንደ አቶ ተስፋለም ከሆነ “ከቅድመ ሁኔታ ጋር ነው።”

“ሕዝቡን በሙሉ፤ እዚያ አካባቢ የተከፈተውን በሙሉ መቅጣት የለባቸውም” የሚሉት የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ዋና ዳይሬክተር እርምጃው “ዒላማውን የለየ መሆን የነበረበት” ሲሉ ይሞግታሉ።

እርምጃው ሲወሰድ የባንክ ሒሳቦቹ ለምን እንደታገዱ እና እርምጃው እስከ መቼ እንደሚቆይ “ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ለሕብረተሰቡ መስጠት ነበረባቸው” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ተስፋለም “ትልቅ ጥሰት ነው ብለን ነው የምንወስደው” ሲሉ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ጉዳዩን እንዴት እንደሚመለከት ገልጸዋል።

አርታዒ አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW