1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ "100 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሞብናል" -ዘኒት ገብስ እሸት

ረቡዕ፣ ጥር 5 2013

በትግራይ ሽሬ ከተማ ተገንብቶ ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ የነበረው የዘኒት ገብስ እሸት ፋብሪካ 100 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ጉዳት እንደደረሰበት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል። ሰማየታ የእምነ በረድ ፋብሪካ እና ጎዳ ጠርሙስና እና ብርጭቆ ፋብሪካ ጉዳት እንደገጠማቸው ዶይቼ ቬለ አዲስ አበባ የሚገኙ ኃላፊዎቻቸውን በማነጋገር ለማረጋገጥ ችሏል።

Äthiopien I Krieg in Tigray beschädigt die Fabrik von Zenith Gebs Eshet Ethiopia Ltd in Shire
ከፊል ጉዳት የደረሰበት የዘኒት ገብስ እሸት ፋብሪካ ምስል Biniam Gebrezgi/Zenith Gebs Eshet Ethiopia Ltd

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ በትግራይ ጦርነት የተጎዱት ፋብሪካዎች

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ታኅሳስ መገባደጃ በትግራይ ጦርነት ሲቀሰቀስ ዘኒት ገብስ እሸት ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሽሬ ከተማ ያስገነባውን ፋብሪካ ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት ላይ ነበር። ኩባንያው የንጽሕና መጠበቂያዎች፣ የሰውነት እና የጸጉር መታጠቢያዎች እና መዋቢያዎች በማምረት የሚታወቅ ሲሆን ነባሮቹ ፋብሪካዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ይገኛሉ።

ከአዲስ አበባ በ1000 ገደማ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሽሬ ከተማ የተገነባውን ፋብሪካ የኩባንያውን ምርቶች ወደ ኤርትራ እና ሱዳን ገበያዎች የሚላኩ ምርቶች የታቀደ ነበር። "የሱዳን ደንበኞች የሚጭኑት በአዲስ አበባ ቃሊቲ ካለው ነባር ፋብሪካ ነው። ስለዚህ ይኸን ወደ ውጪ የምንልከውን ምርት ለማሳደግ ብለን ሽሬ ከተማ ላይ ይኸን ፋብሪካ አቋቋምን። ጠቅላላ ፋብሪካው የፈጀው ወደ 500 ሚሊዮን ብር ነው" ሲሉ የዘኒት ገብስ እሸት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ገብረእዝጊ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከተመሠረተ 30 አመታት ገደማ ያስቆጠረው ኩባንያ ከዚህ ቀደምም ምርቶቹን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ዩጋንዳ ገበያዎች ጭምር እንደሚያቀርብ በድረ-ገጹ የሰፈረው መረጃ ይጠቁማል። አዲሱ ፋብሪካ ወደ ኤርትራ እና ሱዳን ቀረብ ማለቱ ዘኒት ገብስ እሸት ለሁለቱ አገሮች ገበያዎች ምርቶቹን ለማቅረብ የተሻለ ዕድል ይፈጥራል የሚል ዕምነት እንደነበራቸው የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ከዚህ ባሻገር ኩባንያው ለግብዓትነት የሚያሻውን የጉሎ ፍሬ ምርት ለማግኘት አቶ ቢኒያም እንደተናገሩት በሽሬ እና አክሱም አካባቢ የሚገኙ ገበሬዎች እንዲያመርቱ ዘር አከፋፍሎ ነበር።

ሥራ አስኪያጁ ይኸው በሽሬ ከተማ የተገነባ ፋብሪካ ለሱዳን እና ለኤርትራ በሚኖረው ቅርበት የመጓጓዣ ወጪ ይቀንሳል፤ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፤ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል የሚል ተስፋ ነበራቸው።

"በ30 ገጥመን በ8 ተቃጠለ"

"ከ500 እስከ 600 ሰራተኛ" በመቅጠር ፋብሪካውን ሥራ ለማስጀመር አቶ ቢኒያምን ጨምሮ 21 የቴክኒክ ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው አቅንተው ነበር። ነገር ግን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ ፋብሪካው ጉዳት ደርሶበታል። በወቅቱ እዚያው ይገኙ እንደነበር የተናገሩት አቶ ቢኒያም ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የማሽን ተከላ ተከናውኖ ከሳምንት ገደማ በኋላ ሕዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም በከባድ የጦር መሳሪያ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸዋል።  

በ500 ሚሊዮን ብር በሽሬ ከተማ የተገነባው ፋብሪካ ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ እንደነበር የዘኒት ገብስ እሸት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ገብረእዝጊ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል Biniam Gebrezgi/Zenith Gebs Eshet Ethiopia Ltd

የፋብሪካው የአንዱ ሕንፃ ግድግዳዎች በእሳት ተለብልበዋል። ጣሪያው ወድቋል። ዶይቼ ቬለ በተመለከታቸው እና ጉዳቱን በሚያሳዩ ቪዲዮዎች የተቃጠሉ እና የተጨረማመቱ ቆርቆሮዎች ከአንዱ ክፍል ወድቀው ይታያሉ። በዚሁ ክፍል የነበሩ የማምረቻ ቁሳቁሶች ጋይተዋል፤ መሬቱ በእሳት ተቃጥሎ ጠቁሯል።

"ወደ 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት የፋብሪካው ሕንፃ ነው የነደደው። በውስጡ አዲስ የተገዛ ማሽን ነበር። እሱ ገና እንደመጣ ነው የተቃጠለው። በ30 ገጥመን በ8 ተቃጠለ።" ሲሉ የጉዳቱን መጠን ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት አቶ ቢንያም "ወደ 100 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሞብናል" ብለዋል።

ምን ተፈጠረ?

ሥራ አስኪያጁ እንዴት ፋብሪካው እንደተጎዳ ተጠይቀው ሲመልሱ "ሜካናይዝዱ ከአዲ አገራይ እየመጣ ነበር። እዚያ ነበርኩኝ። በእኔ ግምት ሮኬት ነው ያቃጠለው ባይ ነኝ።  ምክንያቱም ጣራው ነው የወደቀው። ከላይ ጣራው ወደቀ። በውስጥ ደግሞ ኬሚካሎች ነበሩ፤ ፎርክሊፍቶች ነበሩ። አዲስ ሎደር ነበረ። እዚያ ውስጥ ተቀምጠው ነበር። ሁሉም ነደዱ" ሲሉ አስረድተዋል። የዘኒት ገብስ እሸት የሽሬ ፋብሪካን ለዚህ የዳረገውን ምክንያት ከመንግሥት ወገን ለማረጋገጥ ዶይቼ ቬለ በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።   

ከዘኒት ገብስ እሸት በተጨማሪ በትግራይ በርከት ያሉ ፋብሪካዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው ይሰማል። በክልሉ በሚገኙ ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት ማጣራት ግን በተለይ በቴሎኮም ግልጋሎት ምክንያት ፈታኝ ሆኗል። ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት በትግራይ ንብረት ከወደመባቸው ኩባንያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ የተገኙት የሳባና የእርሻ ድርጅት እና ኤጄጄ የወተት መቀነባበሪያ ባለቤት አቶ አበራ ጣሰው ኩባንያዎቻቸው ደርሶባቸዋል ያሏቸውን ጉዳቶች ለባለሥልጣናቱ ማስረዳታቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቧል።

አቶ አበራ "እርሻው ሙሉ በሙሉ ወድሟል። መኪኖቹ ተዘርፈዋል፤ የት እንደተወሰዱ አናውቅም። ትራክተሮቹ በሙሉ ተወስደዋል። ህንፃዎቹ፣ መኖሪያ ቤቶቹ፣ መጋዘኖቹ እና ቢሮዎቹ በሙሉ ፈርሰው ቆርቆሮው መወሰድ ብቻ ሳይሆን ግንቡም ጭምር እንዲፈርስ ተደርጓል" ሲሉ ተደምጠዋል።

"ወደ 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት የፋብሪካው ሕንፃ ነው የነደደው። በውስጡ አዲስ የተገዛ ማሽን ነበር። እሱ ገና እንደመጣ ነው የተቃጠለው። በ30 ገጥመን በ8 ተቃጠለ።" አቶ ቢኒያም ገብረእዝጊምስል Biniam Gebrezgi/Zenith Gebs Eshet Ethiopia Ltd

ከእነዚህ በተጨማሪ ሰማየታ የእምነ በረድ ፋብሪካ እንዲሁም ጎዳ ጠርሙስና እና ብርጭቆ ፋብሪካ ጉዳት እንደገጠማቸው ዶይቼ ቬለ አዲስ አበባ የሚገኙ ኃላፊዎቻቸውን በማነጋገር ለማረጋገጥ ችሏል። የሁለቱ ፋብሪካዎች የሥራ ኃላፊዎች እንዳሉት በትግራይ በሚገኙ ማምረቻዎቻቸው ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመመርመር ወደ ቦታው ማቅናት ያስፈልጋቸዋል።

የኢትዮጵያ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምኒስትር ድዔታ አቶ ዮሐንስ ድንቃየሁ በትግራይ ጉዳት ከደረሰባቸው ኩባንያዎች ጋር በተደረገው ውይይት "የእያንዳንዱን ፋብሪካ ችግር ለይተን፤ እያንዳንዱን ፋብሪካ ኢንስቲትዩቱ እንዲደግፍ እናደርጋለን። ለምሳሌ በኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ኢንስቲትዩት ስትደገፉ የነበራችሁ ፋብሪካዎች፤ ኢንስቲትዩቱ እያንዳንዱን ፋብሪካ በአካል ተገኝቶ ነው የሚደግፈው። በዚያ አኳኋን የማጥራት ሥራ እንጀምራለን። ስለዚህ ከእናንተ አንደኛ መረጃ እንፈልጋለን" ብለዋል።

የዘኒት ገብስ እሸት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም ገብረእዝጊ የደረሰውን ጉዳት ጠግኖ የጎደለውን ሞልቶ ወደ ሥራ ለመመለስ ያቅዳሉ። ነገር ግን ከመንግሥት እንፈልጋለን የሚሏቸው ጉዳዮች አሉ። "እኛ የውጭ ምንዛሪ ከተመደበልን በአስቸኳይ ወደ ሥራ ለመግባት እንፈልጋለን። በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብተን ሥራ ለማስጀመር እንፈልጋለን" ያሉት አቶ ቢኒያም የመንግሥት ባለሥልጣናት ቃል በገቡላቸው መሠረት ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችላቸውን ድጋፍ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ኩባንያዎቹ የደረሰባቸው ጉዳት ብቻ አይደለም። ውጊያውን ተከትሎ በተፈጠሩ ኩነቶች ሥራዎቻቸው ተስተጓጉለዋል። የጸጥታ መደፍረስ፣ የባንክ፣ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች መቆራረጥም ሌላው ፈተና ነው። የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምኒስትር ድዔታው አቶ ዮሐንስ ድንቃየሁ መንግሥታቸው ለችግሮቹ መፍትሔ እንደሚያፈላልግ በአዲስ አበባ በተካሔደው ውይይት ቃል ገብተዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW