በትግራይ 1.2 ሚሊዮን ተማሪዎች፣ ከ14,000 በላይ መምህራን ከትምህርት ቤት ርቀዋል
ሐሙስ፣ መስከረም 8 2018
በትግራይ ከጦርነቱ በኋላ 46 ከመቶ ተማሪዎች አሁንም ወደ ትምህርት ገበታ አለመመለሳቸው ተገለፀ። ህፃናት እና ወጣቶች ከትምህርት ርቀው ለጉልበት ብዝበዛ እየተጋለጡ እንዲሁም በሕገወጥ መንገዶች እየተሰደዱ መሆኑም የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 የተደረገው ጦርነት የተገታው የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በፕሪቶሪያ በተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት ነበር። ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ ስላለው የመማርና ማስተማር ስራዎች ጉዳይ ትላንት ለመገናኛ ቡዙሐን መግለጫ የሰጡት የትግራይ ትምህርት ቢሮ ሐላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ፥ በበርካታ ምክንያት አሁንም በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናት ከጦርነቱ በኃላ ወደ ትምህርት ገበታ አልተመለሱም ብለዋል።
የተማሪዎች ቁጥር ቀንሷል
በትግራይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመለሱ የሚያደርጉ በርካታ ፈተናዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን መፈናቀል እና ድርቅ ጨምሮ የተለያዩ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች፣ የትምህርት ግብአት እጦት፣ ስደት እንዲሁም ከዕድሜ በታች ጋብቻ ዋነኛ ምክንያቶች ሆነው እንዳለ ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ ገልፀዋል።
ዶክተር ጉዑሽ "በርካቶች ከዕድሜያቸው በታች የሚያገቡበት፣ ከዚህ በተጨማሪ ሕገወጥ ስደት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ሁኔታ ስላሉ ህፃናት እና ወጣቶች ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመለሱ ምክንያት ሆነዋል።
የማዕድን ማውጣት ስራዎች በተንሰራፉባቸው አካባቢ ደግሞ ህፃናት ከትምህርት ርቀው ወደ ማዕድን ማውጣት ስራ የሚገቡበት ሁኔታ ይስተዋላል። በሌላ በኩልም ትምህርት ቤቶች ምቹ ባለመሆናቸው የተማሪዎች የመማር ፍላጎት የወረደበት እንዲሁም ተፈናቃዮች ሌላ መጠልያ ስለሌላቸው በትምህርት ቤቶች የሚኖሩበት ሁኔታ አለ" ብለዋል።
ከጦርነቱ በኃላ በየአመቱ የተወሰኑ ለውጦች እንኳን ቢታዩም አሁንም ድረስ 1 ነጥብ 2 ሚልዮን በትግራይ የሚገኙ ለትምህርት የደረሱ ህፃናት እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ርቀው እንዳለ ሐላፊው ጨምረው ገልፅዋል። "ወደ ትምህርት ገበታ የመለስናቸው ተማሪዎች ቁጥር 1 ነጥብ 3 ሚልዮን ወይም ከሚጠበቀው 54 በመቶ ነው። የቀረው 46 በመቶ ወይም 1 ነጥብ 2 ሚልዮን የሚሆን የሚጠበቁ ተማሪዎች ግን ወደ ትምህርት ገበታ አልተመለሱም" ብለዋል።
የትምህርት ተቋማት ውድመት
በትምህርት ቤቶች የደረሰ ውድመት ለመጠገን እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የተገለፀ ሲሆን፥ ይሁንና ከግብአት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጉድለት አሁንም ስለመኖሩ የትግራይ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በትምህርት ዘርፉ የነበሩ ከ14 ሺህ በላይ አስተማሪዎች ከጦርነቱ በኃላ በተለያዩ ምክንያቶች በስራቸው እንደሌሉ የትምህርት ቢሮው ሐላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ ገልፀዋል።
የቢሮ ሐላፊው "ከጦርነቱ በፊት ከ46 ሺህ 958 በላይ የሚሆን አስተማሪ ነበሩን። ይሁንና በጦርነቱ ምክንያት ከ14 ሺህ በላይ አስተማሪዎች አሁን ላይ የሉም። ይህ ከነበረው አስተማሪ 30 በመቶ አካባቢ ነው። የአስተማሪዎች ቁጥር መቀነስ ብቻ አይደለም፣ በስራ ያለው አስተማሪም ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰበት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የጦርነቱ ወቅት የ17 ወራት ደሞዛችን ይከፈለን ያሉ በትግራይ የሚገኙ አስተማሪዎች፥ ቅሬታቸው በተለያየ መንገድ እየገለፁ እንዳለ መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ያሰራጨው መረጃ እንደሚያመልክተው በትግራይ የ12 ክፍል ሀገራዊ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 8 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ የማለፍያ ነጥብ ማምጣታቸው የሚያመለክት ሲሆን፥ በመቐለ የሚገኘው ቃላሚኖ ልዩ ትምህርት ቤት ሙሉበሙሉ ተማሪዎች ማሳለፉ ተነግሯል። በክልሉ የሚገኙ 49 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ዘንድሮ አንድም ተማሪ ወደ ዮኒቨርስቲ አላሳለፉም።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር