«በትግራይ ክልል 2 ሚልዮን ዜጎች ለረሃብ ተጋልጠው ይገኛሉ»
ማክሰኞ፣ ኅዳር 25 2016አስቀድመው በድርቅ ተመትተው የነበሩ የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች አሁን ላይ ከፍተኛ ረሃብ እየታየባቸው እንዲሁም ረሃብ የወለደው ሞት እየተከሰተባቸው ይገኛሉ። በተለይም ከመስከረም ወር ወዲህ በትግራይ ረሃብ ለበርካቶች ሞት ምክንያት እየሆነ እንዳለ የሚገልፀው የትግራይ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን፥ በአጠቃላይ በክልሉ የደረሰው ጉዳት ከፌደራል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን እየተጠና ቢሆንም፥ በአበርገለ የጭላ ወረዳ 83፣ በአፅቢ 66፣ በጉሎመኸዳ እና ኢሮብ አካባቢዎች 77፣ እንዳባ ፃሕማ በሚባል አካባቢ 25 ህፃናት ያሉበት 208 ሰዎች በረሃብ መሞታቸው መረጋገጡ አስታውቋል። በመላው ትግራይ እርዳታ ከሚፈልግ 5 ነጥብ 2 ሚልዮን ህዝብ መካከል 2 ሚልዮኑ አሁን ላይ ለረሃብ ተጋልጦ እንዳለም የኮምሽኑ መረጃ የሚያመላክት ሲሆን ይህ አፋጣኝ እርዳታ ካላገኘ ሁኔታው የከፋ እንደሚሆን ይገልፃል። የትግራይ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር ዶክተር ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር « የትግራይ 12 ወረዳዎች አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው» ይላሉ።
ዘንድሮ በትግራይ እየታየ ያለው ረሃብ ከሌላው ግዜ በስፋቱ እና መጠኑ የተለየ መሆኑ የሚገልፁት ኮምሽነሩ፥ ጦርነቱ ከፈጠረው ችግር በተጨማሪ የክረምት ዝናብ እጥረት እና አጠቃላይ እጦት፣ አንበጣ ጨምሮ የተለያዩ ተባዮች መንሰራፋት፣ ወቅቱ ያልጠበቀ ዝናብ እና በረዶ ምርት እና የእንስሳት ቀለብ እንዲጠፋ ምክንያት መሆናቸው ይገልፃሉ። ከዚህ በተጨማሪ የረሃብ አደጋው በሚቀጥሉት ወራት እየከፋ የሚመጣበት አጋጣሚ ስለመኖሩም ጠቁመዋል።
ረሃቡ በመከላከያ ዙርያ የክልሉ አስተዳደር ይሁን የፌደራል መንግስት በቂ ምላሽ አልሰጡም ተብለው በበርካቶች ይተቻሉ። ከመንግስት ምላሽ ይልቅም የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ሚና በጉልህ ይታያል። ብርክቲ ሃይለ በትግራይ ያሉ የተራቡ ዜጎች ለመርዳት ከጓደኞችዋ ጋር በማሕበራዊ ሚድያ በኩል እንቅስቃሴ ጀምረው ውጤታማ ስራ እየከወኑ ካሉት መካከል ናት። ብርክቲ እና ጓደኞችዋ ባሰባሰቡት ገንዘብ 12 ሺህ የሚሆኑ ረሃብ ላይ ያሉ የአበርገለ የጭላ ወረዳ ነዋሪዎች የተወሰነ ግዜም ቢሆን ሊያሻግራቸው የሚችል ምግብ አግኝተዋል።
ብርክቲ "በአጭር ግዜ ተጀምሮ፣ በአጭር ግዜ ወደ ተግባር የገባ እንቅስቃሴ ነው እየተካሄደ ያለው። ረሃብ ግዜ አይሰጥም። ለዛም ነው እየሰራን ያለነው። በተደረገው እንቅስቃሴ በ4 ቀን 10 ሚልዮን ብር ነው የሰበሰብነው። ከ1840 ኩንታል እህል ገዝተን፥ የጭላ አበርገለ ወዳሉ በረሃብ በከፋ ሁኔታ የተጎዱ ጣብያዎች አድርሰናል። ቀጥሎም ዘመቻችን በአጠቃላይ ወደ መላው ትግራይ እያሰፋን ነው። አደጋና ዝግጁነት ጋር ተነጋግረን፥ የትኛው አካባቢ የባሰ እንደሆነ ለይተን ወደዛ እንጓዛለን" ትላለች።
እንደ ብርክቲ ገለፃ በትግራይ ያለው ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የከፋ ነው። በረሃብ ምክንያት የሚፈጠረው ሞት ለመቀነስ መንግስት ይሁን በጎ ፍቃደኞች ፈጣን እርምጃ ሊመስዱ እንደሚገባም ትገልፃለች። በጎ ፍቃደኛዋ "እስካሁን ከ12 ሺህ በላይ ለማሆን ህዝብ እርዳታ አድርሰናል። ገቢ ማሰባሰብ ከጀመርን በኃላ በአምስተኛ ቀናችን ነው እርዳታ ለተጎዱት በቀጥታ ያደረስነው። እኛ ይህ ማድረጋችን ለሌላው አብነት እንሆን እንደሆነ እንጂ ሙሉበሙሉ ችግሩ ይፈታል ማለት አይደለም። የታደለችው እህል የየተወሰኑ ሰዎች ሕይወት ለተወሰኑ ቀናት ታቆይ ይሆናል። ከዚህ ውጭ ግን ዘላቂ ድጋፍ ነው መደረግ ያለበት። በዚህ ግዜ በረሃብ ምክንያት ሰዎች ሊሞቱ መፍቀድ የለብንም" ባይ ናት።
አሁን ላይ ለረሃብ ተጋልጠው ካሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች በተጨማሪ የእርዳታ ለጋሾች እጅ የሚጠብቁ 1 ነጥብ 1 ሚልዮን ተፈናቃዮች በትግራይ በከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይገለፃል። እርዳታ ማቅረብ አቋርጠው የቆዩ ዓለምአቀፍ ለጋሾች በቅርቡ በትግራይ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሰብአዊ ስራቸው እንደሚቀጥሉም ተስፋ ሰጥተው ነበር።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ