1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

በቻግኒ የሁለት ወጣቶች ግድያ

ረቡዕ፣ የካቲት 19 2017

ሰሞኑን በአማራ ክልል አዊ ብሔረስብ አስተዳደር ቻግኒ ከተማ በጥይት ተደብድበው የተገደሉ የሁለት ወጣቶች ሞት የከተማዋን ነዋሪዎች አስቆጥቷል። መንግሥት አንድ የቀበሌ አሰተዳዳሪን ጭምሮ ስድስት ተጠርጣሪዎችን መያዙን አስታውቋል።

የፍትህ ተምሳሉት
«አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ከስጡን የቻግኒ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ እንደሚሉት በጥይት የተገደሉት ወጣቶቹ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩና የፖለቲካ ንክኪ የሌላቸው ናቸው።» ፎቶ ከማኅደር፤ የፍትህ ተምሳሉት ምስል፦ Christoph Hardt/picture-alliance/Geisler-Fotopress

ድርጊቱ ኅብረተሰቡን አስቆጥቷል

This browser does not support the audio element.

 

«ወጣቶቹ የፖለቲካ ንክኪ የላቸውምአስተያየት ሰጪዎች

ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር መሠረት ሃይማኖትና ምናለ ዋሌ የተባሉና በንግድ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ ወጣቶች «የምሽት የፀጥታ ጥበቃ ተረኞች ነበሩ» በተባሉ ተጠርጣሪዎች በጥይት ተመትተው መገደላቸው በከተማዋ ነዋሪ ዘንድ ቁጣን ፈጥሯል ነው የተባለው። ወጣቶቹ በግል ጥረታቸው የተሻለ ሥራ ይሰሩ እንደነበረም ያነጋገርናቸው የቻግኒ ከተማ ነዋሪዎች ገልጠዋል። አስተያየታቸውን ከስጡን የቻግኒ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ እንደሚሉት ወጣቶቹ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩና የፖለቲካ ንክኪ የሌላቸው ናቸው። ከከተማ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በምሽት በዓታ ቤተክርስቲያን አካባቢ በዕለቱ ተረኛ በነበሩ የጥበቃ አባላት በተተኮሰ ጥይት እንደተገደሉ ጥርጣሬ እንዳለ ገልጠዋል። «ተካታታይ እገታና ዘረፋ በከተማዋ በመኖሩ ምናልባትም ሟቾቹ ቁሙ ተብለው ከሆነ ታጣቂዎቹ መንግሥት ያሰማራቸው የጥበቃ አካላት ስላልመሰሏቸው እንዘረፋለን የሚል ሀሳብ ውስጥ ገብተው የያዙትን ተሽከርካሪ ባለማቆማቸው ግድያው ሳይፈጸምባቸው አይቀርም» በማለትም ግምታቸውን ገልጸዋል።

«ሟቾቹ ታታሪ ሠራተኞች ነበሩ» ስለመባላቸው

«አንደኛው ከዚህ በፊት በቤኒሽንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ሠራተኛ የነበር፣ ሌለኛው ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት አገልግሎ የተመለሰና አሁን በግል ሥራ የተሰማሩ ታታሪ ወጣቶች ነበሩ» ይላሉ አስተያየት ሰጪዎቹ።

የአንደኛው ሟች ታላቅ ወንድም እንደሆኑ የገለጡልን አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ወንድማቸውና ጓደኛው በባጃጅ በመሄድ ላይ እንዳሉ በጥይት ተመትተው መገደላቸውን፣ ስለግድያው ግን የተጣራ መረጃ እንደሌላቸው ነው የነገሩን።

ወጣቶቹ በጥረታቸው እስከ ኤክስካቫተርና ሎደር፣ ሲኖ ትራክ የሥራ መኪና የነበራቸው ባለ ራዕይ ወጣቶች እንደነበሩ አስተያየት ሰጪዎቹ ነግረውናል።

«ድርጊቱ ትዕግሥት ከማጣት የተፈፀመ ሳይሆን አይቀርም» የቻግኒ ከተማ አስተዳደር

የቻግኒ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ መኩሪያ ግድያው ትዕግስት ከማጣትና ካለማስተዋል የተፈፀመ ሳይሆን እንደማይቀር ጥርጣሪያቸውን ገልፀዋል። በዕለቱ የከተማ አስተዳደሩ ቀበሌ 01 ሊቀመንበርና ሌሎች የግል ታጣቂዎች የምሽት የጥበቃ ተረኛ እንደነበሩ አስታውሰው፣ በዓታ በተባለው ምንነቱ ያልታወቀና ጥርጣሬ የፈጠረ ቆሞ የዋለ ተሽከርካሪሲንቀሳቀስ ከአካባቢው በደረሰ ጥቆማ መሰረት ወደ ቦታው የተንቀሳቀሱት ተረኛ የጠበቃ አባላት የባጃጅ ተሽከርካሪዎችን ሲያገኙ እየፈተሹ በነበረበት ወቅት ሟቾቹ የነበረችባቸው ተሽከርካሪ (ባጃጅ) እንድትቆም ተጠይቃ አሽከርካሪዎቹ ሳይሰሙ ቀርተው ይሁን ወይም አይሁን ሳትቆም መንገድ በመቀጠሏ ተኩስ ተከፍቶባት የወጣቶቹ ሕይወት አልፏል ነው ያሉት።

ጉዳዩ አሁን በመጣራት ላይ በመሆኑ ግድያውን በትክክል ማን ፈፀመው፣ ለምንንና እንዴት ተፈፀመ የሚለው ወደፊት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ኃላፊው ቃል ገብተዋል። ኃላፊው ወጣቶቹ ለከተማ አስተዳደሩ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በመንግሥት እውቅና ተሰጥቷቸው በግል ታጣቂነት የአካባቢያቸውን ሰላም እያስጠበቁ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል

በዕለቱ የምሽት ተረኛ የፀጥታ ጥበቃ የነበሩ የአንድ የቻግኒ ከተማ የቀበሌ ሊቀምንበርን ጨምሮ አምስት የግል ታጣቂ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ እየተጣራ እንደሆነም አቶ በቀለ አመልክተዋል።

በቻግኒ ከተማ የባጃጅ ተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ብቻ እንደሆነ የተናገሩት የቻግኒ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ፣ ባለፈው ረቡዕ ጥቃቱ ሲፈፀም ሰዓቱ ከአንድ ሰዓት አልፎ የነበረ ቢሆንም፣ ነገሮችን በትዕግስት ማለፍ ይቻል ነበር ባይናቸው።

ዓለምነው መኮንን 

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW