የድሬዳዋ ጎርፍ ሰላባዎች ዝክር
ዓርብ፣ ሐምሌ 30 2013ከአስራ አምስት አመታት በፊት ሐምሌ 28 ቀን 1998 ዓ.ም ሌቱን የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የበርካታ ሰዎችን ህይወት የተነጠቀችው ድሬደዋ ዕለቱን በአንድ ቀን አምስት መቶ ሺህ ችግኞችን በመትከል አስባለች፡፡ ችግኞችን መትከል እና ተንከባክቦ እንዲፀድቁ ማድረግ ለድሬደዋ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡
በድሬደዋ ሐምሌ 28 ቀን 1998 ዓ.ም ሌቱን የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሀብት ንብረት ወድሟል፡፡ እጅጉን አሳዛኝ ትውስታን ትቶ ያለፈው ያ ክስተት አስራ አምስት ዓመት ሞላው፡፡ድሬደዋዎች ይህንን ዕለት አምስት መቶ ሺህ ችግኞችን በአንድ ቀን በመትከል ዘክረውታል፡፡ ነዋሪዎች ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ብቸናዋ ሴት አሰልጣኝ የነበረችው ኢንስትራክተር መሰረት ማኔ እና ከብሔራዊ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ወጣት ሰምበቶ አቡ ስለችግኝ ተከላው ለዶቼቬለ አስረድተዋል።
በድሬደዋ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሪፈራል ሆስፒታል ችግኝ ተከላ ላይ ያነጋገርናቸው ሻለቃ ራህመቶ ሂርጶ በበኩላቸው ሀገር የምትፈርሰው በጦርነት ብቻ ሳይሆን በሰው ሰራሽ አደጋዎች መሆኑን ጠቅሰው እሱን ለመከላከል ሰራዊቱ የበኩሉን ይወጣል ብለዋል፡፡
ባለፈው አመት በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በአስተዳደሩ ከተማና ገጠር ከተተከሉ ችግኞች 68% (ስልሳ ስምንት በመቶ) የሚሆኑት መፅደቃቸውን የአስተዳደሩ ግብርና ውሀ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ተናግረዋል፡፡
በከተማና በገጠር አምስት መቶ ሺህ ችግኝ የመትክል መርህ ግብርን ያስጀመሩት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ለድሬደዋ የተለየ ጥቅም አለው ባሉት የችግኝ ተከላ ላይ የተገኘው ህብረተሰብ ችግኞችን መንከባከብ አለበት ብለዋል፡፡
በያዝነው ክረምት ሁለት ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ጥረት በሚደረግባት ድሬደዋ በአንድ ቀን ከተተከለው አምስት መቶ ሺህ የዛፍ ችግኝ 70 በመቶው የደን ፣ 26 በመቶ የምርምር ደን እንዲሁም ቀሪው 4 በመቶ የውበት ዛፍ ያካተተ መሆኑ ተገልጧል፡፡
መሳይ መኮንን
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ