1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በነቀምቴ ተፈጸመ የተባለው ጥቃት

ሰኞ፣ ጥቅምት 28 2015

በምዕራብ ኦሮሚያ ትልቅ ከተማ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችሉ እንደ ነቀምት ባሉ ከተሞች ታጣቂዎቹ ገብተው ተኩስ ሲከፍቱ እምብዛም ተሰምቶ አይታወቅም ነበር፡፡ ትናንት ግን ውጥረት ውስጥ በዋለችው ነቀምት ታጣቂዎቹ በከተማዋ ሶስት አቅጣጫ ዘልቀው በመግባት ከማለዳ አንስቶ የጀመሩት የተኩስ ልውውጥ እስከ እኩለ ቀን መቀጠሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Straße in Nekemt

በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ትናንት እሁድ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ከማለዳው ጀምሮ እስከ እኩለ ቀን የቆዬ ከባድ የተኩስ ድምጾች ይሰማ እንደነበረ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ዶይቼ ቬሌ (DW) በስልክ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት በአከባቢው በስፋት የሚንቀሳቀሰው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ሰራዊት ወደ ከተማው ዘልቆ ከመንግስት ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርጓል፡፡መንግስት ‘ሸነ’ ያለውና በኢትዮጵያ ፓርላማ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ራሱን «የኦሮሞ ነጻነት ጦር»ሲል የሚጠራው ቡድን ባለፉት ሶስት ዓመታት በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ በሰፊው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም በተለይም በምእራብ ኦሮሚያ ጦሩ የተለያዩ የወረዳ ከተሞችን ይዞ እንደነበርም ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ተዘግቧል። በምእራብ ኦሮሚያ ትልቅ ከተማ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችሉ እንደ ነቀምት ባሉ ከተሞች ታጣቂዎቹ ገብተው ተኩስ ሲከፍቱ ግን እምብዛም ተሰምቶ አይታወቅም ነበር፡፡ ትናንት ግን ውጥረት ውስጥ በዋለችው ነቀምት  ታጣቂዎቹ በከተማዋ ሶስት አቅጣጫ ዘልቀው በመግባት ከማለዳ አንስቶ የጀመሩት የተኩስ ልውውጥ እስከ እኩለ ቀን መቀጠሉን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
“ጠዋት ምንም እንቅስቃሴ ሳይጀመር 12 ሰኣት ገደማ ነው ወደ ከተማዋ የገቡት፡፡ እኛ ከቤትም አልወጣንም ከተማው በሙሉ በተለያዩ አቅጣጫዎች ግን በከፍተኛ የተውክስ ድምጽ ሲናጥ ነው የዋለው፡፡’’ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ የተናገሩት ነው፡፡“ይህ ነው ብለን የምንለው ነገር የለም፡፡ ተኩሱ በጠዋት ነው የተጀመረው፡፡ አሁንም ችግሩ እልባት ያገኘ ስላልመሰለን ከቤትም ለመውጣት አዳጋች ነው፡፡ ስለዚህ በዚህች ከተማ እየተካሄደ ያለው ይህ ነው ያ ነው ለማለት እንቸገራለን፡፡ ትናንት ጠዋት ከያቅጣጫው ግን ተኩስ ይሰማ ነበር፡፡” 

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት “ጠዋት ማለዳ ስንነሳ ተኩስ መከፈቱን ነው የሰማነው፡፡ በከተማዋ ሶስት አቅጣጫ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ይሰማ ጀመር፡፡ አንደኛው በዚህ ሶሰርጋ በሚባል በኩል በከተማዋ በስተምዕራብ ነው፡፡ 04 በሚባለው ወደ ቡሬ መሄጃ በኩልም ከፍተኛ ተኩስ ነበር፡፡ ሌላኛው በከተማዋ ደቡባዊ አቅጣጫም ተኩሱ ወደ መሃል ከተማ መሄዱን ቀጠለ፡፡ በከተማዋ መሃል ማዞሪያ በሚባልና ካምፖች አከባቢ ከባድ ተኩስ ሲካሄድ አይተናል፡፡ ትልቅ ጦርነት ነው በከተማ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው” ብለዋል፡፡
ነዋሪው በአስተያየታቸው በሰዓቱ የመንግስት ጦርም በከተማው ውስጥ እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡ ነዋሪው ከማለዳ ጀምሮ እስከ እኩለ ቀን የተኩስ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ነው እማኝነታቸውን የሰጡት፡፡ “በከተማዋ መብራት ወዲያው ነበር የጠፋው፡፡ አሁንም ከስጋት ነጻ አይደለንም፡፡ እስከ ትናንት ማታ ከከተማዋ ውጪም ቅርብ ቦታዎች ላይ የጥይት ድምጽ ስንሰማ ነበር፡፡ አሁን እኔ መሃል ከተማ ቆሜ ነው ማወራህ፡፡ ታጣቂዎች ከተማ ውስጥ አይታዩኝም፡፡ የመንግስት ጦር ግን በየካምቡ አለ፡፡ በተለይም ትናንት ሰው ዝር የማይልባት ፀጥ ያለች ከተማ ሆና ነው የዋለችው ነቀምት፡፡”
አስቸጋሪ በሆነ እና በሚቆራረጥ ኔትዎርክ ያነጋገርናቸው እኚው ነዋሪ፤ የከተማዋን አሁናዊ ሁኔታ ከባድ ሲሉ ገልጸውታል፡፡ በትናንቱ የታጣቂዎች የተኩስ ልውውጥ ከዞን ማረሚያ ውጪ ያሉ ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ እስረኞች መለቀቃቸውንም ገልጸዋል፡፡“በ05 ፖሊስ ጣቢያ እና ኩምሳ ሞረዳ በሚባል ትልቅ ካምብ ውስጥ የነበሩ እስረኞች በተደረገው የተኩስ ልውውጥ መለቀቃቸውን በተጨባጭ ነው የማውቀው፡፡”አስተያየት ሰጪው ከርቸሌ በሚል የሚታወቀው የዞኑ ማረሚያ ቤት ላይ ግን ታጣቂዎቹ እንዳልደረሱ ነው አየሁ ያሉትን ያስረዱት፡፡
በተኩስ ልውውጡ ሰለባ የሆኑት በርካታ ንጹሃን ሳይኖሩ እዳልቀረ ያነሱት እኚው ነዋሪ እስካሁን በሚኖሩበት አከባቢ የአንድ ሰላማዊ ሰው አስከሬን እንዲሁም በዛሬው እለት በከተማዋ መንገዶች ላይ አምስት የታጣቂዎች አስከሬን መመልከቱንም አብራርቶልናል፡፡ የትናንቱን የነቀምቴ ከተማን ክስተት በማስመልከት መንግስት እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም፡፡ ዶቼ ቬለ የነቀምቴ ከተማ ከንቲባን ትናንት በስልክ ቢያነጋግራቸውም መረጃ እያሰባሰብን ነው የሚል ምላሽ ብቻ ሰጥተዋል፡፡ “መረጃውን ከውስን ደቂቃዎች በኋ አጣርቼ እሰጣሃለሁ፡፡” ከንቲባው አቶ ቶሌራ ይህን ብሉም ከትናንት ጀምሮ ዛሬ ድረስ በተደጋጋሚ ብንደወልላቸውም ስልክ አይመልሱም፡፡
የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር፣ የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር እንዲሁም ኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናት ጋርም ደውለን አልተሳካልንም፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ጦር ዓለማቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በቲዊተር እንደጻፉት ግን ‘እያካሄድን ነው’ ያሉትን ኦፕሬሽን “የመንግስት የፀጥታ መዋቅር እና የመንግስት ጦር ካምፖችን ለማጥቃት” እንደሚጠቀሙበት ጽፈዋል፡፡ በትናንቱ የነቀምት ጥቃትም 120 “የፖለቲካ እስረኞች” ያሏቸውን ከኩምሳ ሞረዳ ካምፕ ጦራቸው እንዳስለቀቃቸው አመልክተዋል፡፡
መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ኦነግ ሸነ የሚለው ቡድን ላይ ጠንካራ ያለውን እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ አሳውቋል፡፡ በቅርቡ እንኳ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ ጠንካራ ያሉት ኦፕሬሽን በምዕራብ ኦሮሚያ በመንግስት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት  መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW