1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በናዚ ጀርመን በግፍ የተጨፈጨፉት የሲንቲ ሮማዎች 80ኛ ዓመት መታሰቢያ በአውሮጳ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30 2016

ራሳቸውን ሲንቲ ሮማ ብለው የሚጠሩ ፣በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት የሚገኙ አናሳ ህዝቦች በናዚ ጀርመን የግፍ ግፍ የተፈጸመባቸውና አሁንም በየሀገሩ የተገፉ ህዝቦች ናቸው።ያኔ በአውስሽቪትዝ ማጎሪያ በሺዎች የሚቆጠሩት በናዚ ጀርመን ያለ ርህራሄ ተጨፍጭፈዋል። የያኔው ግፍ ሳያንስ በዚህ ዘመንም በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ልዩ ልዩ በደሎች ይደርሱባቸዋል።

Der 80. Jahrestag der Auflösung des Roma-Lagers in Auschwitz
ምስል Brunilda Kazani/DW

በናዚ ጀርመን በግፍ የተጨፈጨፉት የሲንቲ ሮማዎች 80ኛ ዓመት መታሰቢያ በአውሮጳ

This browser does not support the audio element.

በየሀገሩ የተለያየ መጠሪያ አላቸው ፤ ጂፕሲ ፣ሲንቲ ሮማ ፣ትሲጎይነር ፣ሲንጋሪ ይባላሉ ። ራሳቸውን ሲንቲ ሮማ ብለው የሚጠሩት እነዚህ ህዝቦች በአንድ ስፍራ ረግተው አይኖሩም ። ተንቀሳቃሽ ህዝቦች ናቸው ። ከአያት ቅደመ አያቶቻቸው ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው ከዚህ ልምዳቸው ዛሬም አልተላቀቁም ። በተለያዩ የአውጳ ሐገራት ውስጥ ለዘመናት ቢኖሩም ከዘመነው አውሮጳ ጋር የሚመሳሰል ህይወት ግን የላቸውም ። የአብዛኛዎቹ  ኑሮ ከ3ተኛው ዓለም ችግረኛ ህዝብ ጋር ይቀራረባል ። በየሚኖሩበት ሐገር የተገለለ ሕይወት የሚገፉት እነዚህ ህዝቦች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ከአንዳንድ የምዕራብ አውሮጳ ሐገራት በግዳጅ ይባረራሉ ፤ጥቃትም ይፈምባቸዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አይሁዶችን በግፍ የጨፈጨፈው ናዚ ጀርመን ያኔ ሲንቲ ሮማዎችንም ያለ ርህራሄ ገድሏል።  

ማርቲን ክሮክ ሴሬድ ስሎቫክያ የሚገኘው በናዚ ጀርመን የተጨፈጨፉ አይሁዶች መታሰቢያ ቤተመዘክር ሃላፊ ናቸው። ብዙም የማይወራለትን የዚህን ግድያ መነሻንና መታሰቢያውም በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2 የሆነበትንም ምክንያት ሲያስረዱ«በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብዙዎች ተገድለዋል። አይሁዶች የተገደሉት ዘረኛ ሕጎችን መነሻ በማድረግ ነው። ከነርሱ ጎን ለጎን ከፍተኛ ጭፍጨፋ ከተፈጸመባቸው መካከል ሮማዎች ይገኙበታል። ከ500 ሚሊዮን በላይ በላይ የሚሆኑት ተገድለዋል። ለምን በዚህ ቀን በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ ሁለት ሆነ ስንል ምክንያቱ በአውስሽቪትስ ቢርከናው የሰዎች ማጎሪያና መግደያ የጂፕሲዎች ካምፕ እንዳልነበረ እንዲሆን የተደረገበት ቀን ነው።ያም ማለት  በዚያ የነበሩት ሰዎች በሙሉ በዚያ ለሊት ተገድለዋል።የተገደሉትም በዋነኛነት አዛውንቶች ሴቶችና ህጻናት ናቸው።»


ናዚዎች ቀደም ሲል በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 1944 ነበር ስፍራውን ለማውደም የፈለጉት። ሆኖም በካምፑ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ ስለነበረ ያኔ ያሰቡትን ሳያደርጉ ቀርተው ፣ ለነሐሴ 1944 በገፉት መሠረት በዚሁ ወቅት ጭፍጨፋውን ፈጽመዋል። በዚያ ለሊት ቁጥራቸው ወደ 4300 እንደሚሆኑ የተገመቱ ሰዎች በግፍ መገደላቸው ተመዝግቧል። ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እናቶች፣ ትናንሽ ህጻናት ፣አዛውንቶችና በሽተኞች የነበሩ ሲንቲ ሮማዎች የዛሬ 80 ዓመት በፖላንዱ «በአውስሽቪትስ ቢርከናው» የሰዎች ማጎሪያና መግደያ የጂፕሲ ካፕም ውስጥ በመርዝ  ጢስ ታፍነው እንዲሞቱ ተደርጓል።  መስራት የሚችሉ ሌሎቹ ደግሞ አስቀድሞ ወደሌሎች ካምፖች ተወስደው ነበር። 

በአውስሽቪትዝ ቢርከናው በተካሄደው 80ኛ ዓመት የሮማ ሲንቲዎች የናዚ ጀርመን ጭፍጨፋ መታሰቢያ ላይ የተገኙ የአውሮጳ ሀገራት ባለሥልጣናት ምስል Keno Verseck/DW


በአውሮጳ አናሳ ከሆኑት ከእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአጠቃላይ ቁጥራቸው ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሰው በማጎሪያ ካምፖች ብቻ ሳይሆን በጎስቋላ የመኖሪያ መንደሮቻቸውም ፣በመርዝ ጢስ፣ በጥይት ፣በረሀብ፣ በግዳጅ ስራ እና በበሽታ እንዲሁም የሕክምና ሙከራ ሲደረግባቸው ሕይወታቸው ማለፉን ታሪክ መዝግቦታል። ያኔ የናዚ ጀርመን የሮማ ሲንቲዎች አያያዝ ምን ይመስል እንደነበር ያስረዱት ማርቲን ኮርኮክ እንዳሉት ሲንቲዎችን መግደል ከመጀመራቸው በፊት ናዚዎች ደንቦችን አውጥተው ነበር። «ፀረ አይሁድ ደንቦች እንደወጡ ፣አንዳንድ ፀረ-ሮማ ደንቦችም ይፋ ሆኑ።ለምሳሌ ከነዚህ በጣም ቀዳሚው የግዳጅ ስራ ነበር። ይህም ለምሳሌ 18 ዓመትና ከዚያ በላይ እድሜ ያላቸው ወንዶች ልጆች በግዳጅ የሚሰማሩበት ነበር። ቀስ በቀስ እስከ 1944 ስሎቫክያ ግዛት ውስጥ ጂፕሲዎች የሚታጎሩበት ካምፕ ሲመሰረት ግዳጁ እየተጠናከረ ሄደ ።ርግጥ ነው ከዚያ በፊትም ጂፕሲዎችን የሚያጉሩበት ካምፕ ነበረ። በ1944 ግን ሮማዎችን ብቻ ያጎሩበት ካምፕ በዱብኒካ ናድ ቫሆም ተቋቋመ። ስፍራው በርካታ ሰዎች የተያዙበት ነበር። ስፍራው አንዳንዶቹ የተገደሉበትም ቦታ ነበር። »የጀርመናዊ ጂፕሲ የአውስሽቪትዝ ትውስታ


የአውሮጳ ኅብረት ጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2 የሲንቲና ሮማዎች ጭፍጨፋ መታሰቢያ ቀን እንዲሆን በ2015 ዓም ነው የደነገገው ። የዘንድሮው የሲንቲና ሮማዎች ጭፍጨፋ 80ኛ ዓመት  ከያኔው ጭፍጨፋ የተረፉና ሌሎች የሲንቲ ማኅበረሰብ አባላት ፣ከመላው የአውሮጳ ሀገራትና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተወከሉ ባለስልጣናት በተገኙበት አብዛኛው ክፍል ፖላንድ ባለው የቀድሞው የአውስሽቪትስ ማጎሪያ ካምፕ በሚገኝበት ስፍራ ታስቧል። በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት  የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ባቤርብል ባስ ሲንቲና ሮማዎች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መጨፍጨፋቸውን ብዙ ሰው እንደማያውቅ ተናግረው ቀኑ መታሰቡ ሰለባዎች እንዳይረሱ ይረዳል ብለዋል። ኮርኮክ እለቱን በነዚህ ዝግጅቶች ማሰቡ ዘላቂ ጠቀሜታ አለው ብለው ያምናሉ።
«ባለፉት ጊዜያት ሮማዎች በመሠረቱ በአንዳንድ መንገድ የተገለሉ ነበሩ።በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ደግሞ የተገደሉበት ሁኔታ አለ። ይህ እውነታ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አልተገለጸም። በተቃራኒው አንዳንድ ማግለል ነበር። ግን ባለፉት ዓመታት ሮማዎች ስለደረሰባቸው ተናግረን አናውቅም ነበር።በመሠረቱ ይህም እስካሁን ድረስ የዘለቁ መዘዞች አሉት።  ስለዚህ ባለፉት ጊዜያት ይህ ጥላቻ ከየት ተነስቶ ወዴት እንዳመራ ፣ወደፊትም መሰል ነገሮች እንዳይፈጸሙ መናገር በጣም ጠቃሚ ነው።» 

በአውስሽቪትዝ ቢርከናው የዘንድሮው የሮማ ሲንቲዎች የናዚ ጀርመን ጭፍጨፋ መታሰቢያ ምስል Keno Verseck/DW

ይሁንና በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ሲንቲና ሮማዎች በአውሮጳ የሚደርስባቸው በደል አልቆመም ። በጀርመን ብቻ የሚደርሰውን ስንመለከት ፣የጀርመን ባለሥልጣናት ባለፈው ነሐሴ እንዳሳወቁት በሮማና ሲንቲዎች ላይ የሚፈጸሙትን ጥቃቶች የሚመዘግበው የመረጃ ማዕከል እንዳሳወቀው በጎርጎሮሳዊው 2023 ጀርመን ውስጥ በአናሳዎቹ ሲንቲና ሮማዎች ላይ 1200 ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ይህም በ2022 ከደረሰው ጥቃት ጋር ሲነጻጸር በ621 ከፍ ብሏል።ሪፖርቱ በርሊን ውስጥ በቀረበበት ወቅት በጀርመን የሲንቲና ሮማዎች ማዕከላዊ ምክር ቤት የበላይ ሮማኒ ሮዝ «ይህ ከታሪካችን ጋር በተገናኘ ትልቅ ስጋት ሆኖብናል ብለው ነበር። መኖሪያቸውን ጀርመን ያደረጉ ቁጥራቸው 150ሺህ የሚደርስ ሲንቲና ሮማዎች አሉ። ሌሎች 100 ሺህ የሮማ ስደተኞችም ጀርመን ይገኛሉ።ጂፕሲዎች ከአውሮፓ የተገለሉ ህዝቦች

የጀርመን ፌደራል መንግሥት የቤተሰብ ሚኒስትር ሊዛ ፖስ ፀረ- ሮማ አመለካከት የጀርመን የእለት ተዕለት ሕይወት አሳዛኝ አካል መሆኑን ተናግረው ነበር ። በዚሁ ወቅት በቀረበ ዘገባ ፖሊስ ሲንቲና ሮማዎችን የሚይዝበት መንገድ ተተችቶ ነበር። በዚህም  ስልታዊ የሚባለውን አድልዎ ለመዋጋት በፖሊስ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል። የሲንቲ ሮማዎች ተወካዮች ችግሩ የተሰባባሰው ፖለቲከኞች በሲንቲዎች ላይ የሚፈጸሙ ማግለሎችን አጉልተው ባለማሳወቃቸው ነው ብለዋል። ከዚህ ሌላ ኅብረተሰቡ በሮማዎች ላይ የሚደርሱ አድልዎችን በአደባባይ ድምጹን ከፍ አድርጎ አለማሰማቱንም አሳፋሪ ብለውታል። እስራኤል የሚገኘው ያድ ቫሼም የተባለው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚ ጀርመን ለጨፈጨፋቸው አይሁዶች መታሰቢያ የተቋቋመው ቤተ መዘክር ሊቀ መንበር ዳን ዳያን በሲንቲ ሮማዎችና በአይሁዶች ላይ አሁንም ድረስ በደሉ መቀጠሉን ተናግረዋል።
«በአሁኑ ወቅት ሁለቱም ህዝቦች አሳዛኝ የሆነ ዓለም አቀፍ ክህደትና ባለፉት ዘመናት የተፈጸሙ አስከፊ ወንጀሎችን፣የማዛባት ሁኔታ እየገጠማቸው ነው። እንዲህ ዓይነቱ ክህደት ደግሞ  ወደ ጥላቻ ግጭትና ሁከት አምርቷል። ዝም ከተባለ ኅብረተሰባችንን መመረዙን እና ህልውናችንንም መፈታተኑ ይቀጥላል። በሚያስደነግጥ ሁኔታ የገዛ ሀገሬ በቅርቡ የዘር ማጥፋት እንዲፈፀም የሚያነሳሱ የጥፋት ኃይሎች ከጥቂት ወራት በፊት የተፈጸሙና በአግባቡ የተሰነዱ ወንጀሎችን እንደሚክዱ ደርሳበታለች። »
ድያን ከወራት በፊት የተፈጸመ ወንጀል ያሉት እስራኤል ዩናይትድ ስቴትስ ፣ብሪታንያ ፣ጀርመንና ሌሎች ሀገራት አሸባሪ የሚሉት ሃማስ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓም በእስራኤል የፈጸመውን ጥቃት ነው። ወደ ጀርመን ስንመለስ ጀርመን በሲንቲዎች ላይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተፈጸመውን ግድያ እስከ ጎርጎሮሳዊው 1985 ድረስ የዘር ማጥፋት ብላ አልተቀበለችውም ነበር። በጎርጎሮሳዊው 2022  የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጎርጎሮሳዊው 1945 ካበቃ በኋላም በሲንቲና ሮማዎች ላይ ኢፍትሀዊነቱ መቀጠሉን ተናግረው ለዚህም ሲንቲና ሮማዎችን ይቅርታ ጠይቀዋል።  

በቀድሞው የአውስሽቪትዝ ቢርከናው ማጎሪያ በዛሬ ሁለት ዓመቱ መታሰቢያ ላይ የተገኙ ወጣት ጂፕሲዎች ምስል Wojciech Grabowski/ZUMAPRESS/picture alliance

ኂሩት መለሰ

ሸዋሼ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW