1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በናይጀሪያ የተስፋፉት የሀሰት የዩኒቨርስቲ ዲግሪዎች

ቅዳሜ፣ መስከረም 4 2017

የፌደራሉ መንግሥት ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ የሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ ፌደሬሽን ሃላፊ ማናቸውንም የሀሰት ሰርተፊኬት የያዘ ሰው እንዲያባርሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል ። ፕሬዝዳንቱ በዚህ እርምጃ የናይጄሪያን ቀጣሪዎች ከዚህ ዓይነቱ የሀሰት የትምህርት መረጃ መጠበቅና በአገሪቱ ውስጥ የብቃት ማረጋገጫዎች ትክክለኛነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ
የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡምስል Sodiq Adelakun/AFP

በናይጀሪያ የተስፋፉት የሀሰት የዩኒቨርስቲ ዲግሪዎች

This browser does not support the audio element.

ናይጀሪያ በሀሰት የዩኒቨርስቲ ዲግሪዎችን ለማስቀረት የምታደርገው ትግል 

ናይጀሪያ ባለፈው ዓመት በጥር ወር ቤኒንና ቶጎ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ናይጀርያውያን ያገኟቸው የሀሰት ዲግሪዎች አግዳለች። ሆኖም ባለፈው ወር እገዳው ተስፋፍቶ በኬንያ በዩጋንዳና በጋና ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የተወሰዱ ዲግሪዎችንም አካቷል። 

መቀመጫውን አቡጃ ያደረገው የናይጀሪያ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲዎች ዋና ጸሐፊ ክሪስ ማያኪ መንግሥት ለሀሰት ዲግሪዎች ምንም ትዕግእስት የለውም ብለዋል።

«ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታውን የቀየረና በትልቅ ደረጃ በዚህ መንግሥት የተላለፈ ውሳኔ ነው። የሀሰት ዲግሪዎችን በፍጹም አይታገስም።»

የናይጀሪያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት የሀገሪቱን የትምሕርት ስርዓት ተዓማኒነት ማስጠበቅና አሠሪዎችንም ሊፈጸሙ ከሚችሉ የማጭበርበር ድርጊቶች ለመጠበቅ ይፈልጋሉ።ከአፍሪቃ በህዝብ ብዛት አንደኛውን ደረጃ የምትይዘው የናይጀሪያ መንግሥት የቅርብ ጊዜው ውሳኔ ላይ የደረሰው ለአንድ የሀገር ውስጥ ጋዜጣ የሚሰራ ጋዜጠኛ በድብቅ ባካሄደው ምርመራ ቤኒን ከሚገኝ አንድ ዩኒቨርስቲ የሀሰት ዲግሪ ማግኘት ከቻለ በኋላ ነበር። ጋዜጠኛው ኡማር አውዱ ባለፈው ጥር ወር አራት ዓመት የሚወስደውን በአንድ የቤኒን ዩኒቨርስቲ የሚሰጥ የዲግሪ መርሃ ግብር ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ እንዴት መጨረስ እንደቻለ በዝርዝር አሳውቆ ነበር።

ማያኪ በድብቅ ለመማር የተመዘገበው ጋዜጠኛ በስድስት ሳምንት ውስጥ ከኒዠር ድንበር ተሻግሮ ሰርተፊኬቱን ማግኘቱ የማይታሰብ፤ የማይታመንም ነው ብለዋል።

በናይጀርያ የማይዱግሪ ዩኒቨርስቲምስል Alamin Muhammed/DW

 

ለአካዳሚ ትምህርት መረጃዎች እውቅና የሚሰጡ የመንግሥት ድርጅቶችና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው። የናይጀሪያ የትምሕርት ሚኒስትር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የፌደራሉ መንግሥት ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ የሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ ፌደሬሽን ሃላፊ ማናቸውንም የሀሰት ሰርተፊኬት የያዘ ሰው እንዲያባርሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል ። ፕሬዝዳንቱ በዚህ እርምጃ የናይጄሪያን ቀጣሪዎች ከዚህ ዓይነቱ የሀሰት የትምህርት መረጃ መጠበቅና በአገሪቱ ውስጥ የብቃት ማረጋገጫዎች ትክክለኛነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲ ዲግሪዎችን ትክክለኛነት መጠበቅ

ሪችመንድ አቼያምፖንግ በጋናው የክርስቲያን ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የኮምኒኬሽን መምህር ናቸው።በጉዳዩ ላይ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት ናይጀሪያ ችግሩን ለመከላከል ትክክለኛ እርምጃ እየወሰደች ነው ብለዋል።

«አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች መታገዳቸው ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚወስድ እርምጃ ነው። ይህም የሀሰተኛ ምስክር ወረቀቶችን ደረጃ ለማጣራት ይረዳል።»

በናይጀሪያ የዩኒቨርስቲ የሀሰት የምስክር ወረቀቶች አዲስ አይደሉም። ባለፈው ጥር መንግሥት ባለፉት 15 ዓመታት በሀገሪቱ አገልግሎት መስጠት በጀመሩ 107 የግል ዩኒቨርስቲዎች ላይ ምርመራ በማካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቋል። ይህም የሀሰት ዲግሪዎችን መስፋፋት ለመከላከል ተጨማሪ ጥረት ነው።

«እዚህም እዚያም የሕገ ወጥነት ኪሶች አሉ።ሆኖም ይህ በምንም ዓይነት ባለጸጋውን የናይጀሪያን የአካዳሚ ልምድ እና የናይጀሪያ ዩኒቨርስቲ መለያ በሆኑት የተከበሩ ዓመታት ላይ ጥላ እንዳያጠላ ነው የምንመኘው።»

እንደ አቼምፖንግ ገለጻ፣ የውሸት የዩኒቨርሲቲ ዲግሪዎች መስፋፋት ብዙውን ጊዜ ከተቆጣጣሪ አካላት “ትክክለኛ ቁጥጥር” መላላት ጋር ይያያዛል። የሀሰት ዲግሪዎች እንዳሉ በተዘገበባት በጋና አቼምፖንግ እንዳሉት ችግሩን በጠንካራ የክትትል ሂደት መቆጣጠር ተችሏል።

«ይህ ነው የነዚህን ምስክር ወረቀቶች ጉዳይ ለመፍታት ጋና ባለፉት ዓመታት ስታደርግ የቆየችው ይህን ነበር። የጋና ባለሥልጣናት ፣ ህዝቡን እውቅና ከሌላቸው ተቋማት እንዲጠበቅ በየጊዜው እውቅና ያላቸውን ተቋማት ዝርዝር ያሳውቃል።

በጋና የአክራ ዩኒቨርስቲምስል Imago Images/D. Delimont

ናይጀሪያ ከጎረቤቶቿ ትማራለች

አቼምፖንግ እንዳሉት ቀጣሪዎች ሁሌም የሠራተኞቻቸውን ሰርተፊኬቶች ሲያጣሩ ናይጀሪያ ከጋና መማር ትችላለች። ጋና ቀጣሪዎች የወደፊት ሠራተኞቻቸውን ሰርተፊኬቶች እንዲያጣሩ ታበረታታለች።የናይጀሪያ ባለሥልጣናት ለዜጎችና ለዓለም ናይጀሪያ ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርርስቲዎች የሚሰጡ ዲግሪዎች አሁንም የቁጥጥር ደረጃዎችን ያሟሉ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ይሰጣሉ።

«የአካዳሚ ብቃቱ አያጠራጥርም።ሆኖም ምንም ያህል ትንሽ ይሁን ክፍልፋዩ በሰርተፊኬቶቻችንና በዩኒቨርስቲዎቻችን ስም ላይ ተጽእኖ ሊያደርጉ መቻላቸው ያሳስበናል። ይህ ወደፊትም የምንታገለው አንድ ጉዳይ ነው። »

አቼምፖንግ እንደሚሉት ናይጀሪያ ትግሉን ለማሸነፍ ከዚህም በላይ መስራት አለባት።

«ናይጀሪያ በተጭበረበረ የትምሕርት መረጃ ለተያዙ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት በመስጠት ለሌሎች ትምሕርት እንዲሆኑ በማረጋገጥ አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ ትችላለች።»

የናይጀሪያ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ቢያንስ 21,600 ምሩቃን የሚባሉ ናይጀሪያውያን ከቤኒን ቶጎ እና ሌሎች አገራት የተጭበረበረ ዲግሪ ያገኙ ናቸው። ባለፈው ጥር ጋዜጠኛ አውዱ የምርመራ ዘገባው ይፋ እንደሆነ ችግሩ በናይጀሪያ የትምሕርት ስርዓት ላይ የሚያስከትለew ጫና ቀላል እንዳልሆነ ተናግሮ ነበር።

« ሰርተፊኬቶች ማግኘት የሚፈልጉ ተስፋ የቆረጡ በርካታ ወጣት ናይጀሪያውያን አሉ።ይህ ደግሞ በትምሕርት ዘርፋችን ላይ ከፍተኛ ክፍተት እየፈጠረ ነው።»

እናም አቼምፖንግ በዚህ ጉዳይ ላይ ናይጀሪያ ችግሩን የማሳወቅ ከፍተኛ ዘመቻ ማካሄድ አለባት ብሏል። የሀሰት የትምሕርት ማስረጃዎች ለአደጋ እንደሚያጋልጡ እና እንዴት ሕጋዊውን ተቋም እንዴት ማወቅ እንደሚችሉ ህዝቡን ማስተማር እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። የናይጀሪያ ባለሥልጣናት ደግሞ የተጭበረበረ ዲግሪ እንደሚሰጡ የደረሱባቸው የትምሕርት ተቋማት ከሚገኙባቸው ሀገራት ጋር ድንበር ተሻጋሪ ትብብር እንዲያደርግ ተማጽኗል።

 

ክርስፒን ምዋኪዱ / ኅሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW