«እናትም ትከዳለች» ከአረብ አገር ተመላሽ
ሰኞ፣ መጋቢት 28 2018
የተሻለ ሕይወትና የተሻለ ኑሮን በመመኘት በአረብ ሀገራት ለአመታት በስደት ሰርተው ያጠራቀሙትን ጥሪት ወደ ሀገር ቤት ሲልኩ የቆዩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ በቤተሰቦቻቸውና በፍቅር አጋሮቻቸው ክህደት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ለ26 አመታት በሳውዲ አረቢያና የመን የሰራችው ራህመት አሊ ሞታለች ተብሎ በፍርድ ቤት ተመስክሮ የሰራችውን ቤትና ገንዘብ ቤተሰቦቿ እንደወረሷት ትናገራለች።
«እናትም ትከዳለች»
"እናት ከዳኝ ብለህ አታምንምግን እናት ይከዳል፤ እውነቴን ነው የምልህ። እየላኩኝ የቤት ፎቶ ይላክልኛል፤ ይህን ያህል ቆርቆሮ ያስፈልጋል፣ ይህን ያህል ሚስማር ያስፈልጋል፣ ይህንን በቃ ይህን ካላደረግሽ ዛሬ ይቋረጣል። ቤቱ ሲሰራ ክደው ቤቱን በስማቸው አድርገው እኔ ስመጣ እንደወጣሽ ትቀሪያለሽ ብለን ነው ያሉኝ። አንድ የእናቴም የአባቴም ልጅ አንድ ነው። ሙሉ የኔ ንብረት ነው። ሞታለችና ልጄ ለሱ በቁም ኑዛዜ እሰጣለሁ ብላ ሄዳ ፍርድ ቤት ፍርምርም አድርጋ የቁም ኑዛዜ ሶስት ጊዜ ተመስክሮ ፍርድ ቤት ላይ ተለጥፎ እኔ አልነበርኩም ወርሶ ጠበቀኝ።"
ሌላዋ ባለታሪክ በጆርዳን ለአመታት የሰራችው ፋጡማ ኢብራሂምም የወደፊት ዉሀ አጣጭሽ ይሆንሻል ተብዬ ኒካህ ያሰርኩለት ሰው የላኩትን ብርና የቤት እቃ ቀማኝ ትላለች።
"ሼህ ነዉ አዲስ አበባ ነው ጀሞ አንድ የሱን ወንድም ካላገባሽ አለኝና አላህን ፈሪ ነኝ አለኝ እሺ አልኩኝ። ያኔ ልቤን ከፈትኩና ሰጠሁት ። እሺ ብዬ ጆርዳን የሰራሁትን ብር ደግሞ ለሱ እየላኩ ነበር ገራዶ ቦታ ይገዛል ተብሎ። በዛ ምክንያት ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር የቤት እቃ በሙሉ ተወሰደ፤ ስመጣ አግብቶ ወልዷል።"
የስልክ ትውውቅ መዘዝ
በዱባይና ኩዌት ከስድስት አመት በላይ የሰራችው ሰአዳ መሀመድም ይህ በአረብ ሀገራት ያሉ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሴት ሰራተኞች ችግር ነው ስትል ትገልጻለች።
"ሌላ ያገባባታል ገንዘቡ ይጠፋል። ሁለተኛ ገና ሳይጋቡ እንዲሁ በስልክ በሚተዋወቁት ወንድ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩት በስልክ በሶሻል ሚዲያ ይተዋወቃሉ ብሩ ይላካል እዚያ ይጠፋል። ከዛ ትመጣለች እዚህ መጥታ አእምሮዋ ኖርማል አይሆንም ጤነኛም አትሆንም ቤተሰብ አያስታምማትም ያው ዋናው ገንዘቧ ነው፤ ገንዘቧ ሲያልቅ ማንም አይጠይቃትም፤ ይህ በጣም ብዙ አለ።"
ማህበረሰቡ በአረብ ሀገር ስለሚሰሩ ሴቶች ያለው የተሳሳተ አመለካከት በብዙ እንደጎዳቸውም ራህመት አሊ ትናገራለች።"ከትዳር እንኳን ጥሩ ትዳር ይዘዉ የምታየው እዚህ ያሉትን ነው። እኛ የተሰደድ ነዉ አይደለንም፤ እኛን እንደ እብድ እንደ ቀውስ ነው የሚያዩን። ለምሳሌ ጓደኛዬ አባቷን ገድላለች፤ አባቷን የላኩትን ብር የሰራሁትን ብር እፈልጋለሁ ስትል የለም የምን ብር ነው የለሽም ብር የሚባል ነገር የለሽም ሲሏት አናታቸውን ብላ ገደለቻቸው። ሰርታ ልካ ነው 16 አመት እዛ ሰርታለች ግን ስትመጣ ምንም ያገኘችው የለም የታክሲ እንኳን አላገኘችም። በቃ እዛም እብደት ነው እዚህም እብደት ነው።"
ሴቶችን አረብ ሀገር በመላክ እያሰሩ ጉልበትን መበዝበዝ ሆን ተብሎ የሚከናወን ስራ ነው የሚሉት አቶ ዑመር ብርቁ ያልተሰራ ስራ እንደተሰራ በማሳመን ሕይወታቸውን የሚያጨልሙ በርካቶች ናቸው ይላሉ።
"በልጅነታቸዉ ትምህርት ሳይማሩ ትዳር ይጀምራሉ የሚያገባቸውም ሰው ለጋብቻ ሳይደርስበስነ ልቦናም በኢኮኖሚም በምንም ለማግባት ሳይደርስ አረብ ሀገር ለመላክ ብቻ ያገባል። ሌላ ሴት አግብቶ ይቀመጣል እሷ እየሰራች ትልካለች ስትመጣ ባዶዋን ናት። ቤት እየሰራሁልሽ ነው እያለ የሰው ቤት ፎቶ እያነሳ ይልካል። ስትመጣ ቤቱም የለም የተላከው ገንዘብም የለም መልሳ ጤናዋ ተቃዉሶ በባህር ትሄዳለች።"
የባለሙያ አስተያየት
በጎንደር መምህራን ኮሌጅ የስነ ልቦና ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ስለአባት ታከለም በስራ ሕይወታቸው በርካታ ተመሳሳይ ጉዳዮች እንዳጋጠሟቸው ገልጸው በዚህ ችግር ያለፉ ሴቶች ራስን ማረጋጋትና ነገ የተሻለ እንደሆነ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
"እኔም አንዳንድ ጊዜ ባለን የሰራ ግንኙነት የወደቁ እህቶችን አያለሁኝ።ስሜታቸውን ማረጋጋትስሜታቸውን መግታት አላስፈላጊ ውሳኔ በመወሰን ሕይወታቸውን የሚያጠፋም ጤናቸውንም ሊያቃውስ የሚችል ውሳኔዎች ውስጥ ላለመግባት ሕይወት በዚህ የሚያበቃ ስላልሆነ ነገ ሌላ ቀን ስለሆነ ራስን አረጋግቶ ደግሞ ሌላ ስራዎችን መስራትና ከዚህ ትምህርት ወስዶ እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ድጋሚ ላለመግባት ለራስ ቃል መግባት የተሻለ ይሆናል።"
ኢሳያስ ገላው
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ፀሐይ ጫኔ