በአሙሩ ወረዳ በታጣቂዎች በደረሰ ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ
ዓርብ፣ ግንቦት 30 2016በአሙሩ ወረዳ በታጣቂዎች በደረሰ ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ
በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ከትናንት በስቲያ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች በሞተር ሳይክል ወደ አጋምሳ ከተማ ሲጓዙ እንደነበር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በአሙሩ እና ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ሀሮ በሚባል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲያደርሱ እንደነበር ነዋሪዎች ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወረው የታጣቂዎች ጥቃት ቀንሶ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ በወረዳው ከ40 ሺ በላይ የተፈናቀሉ ሰዎች በቅርቡ ወደ ቤታቸው መመለሳቸው የተነገረው በዚሁ ሳምንት ነው፡፡
በአሙሩ ወረዳ በታጣቂዎች ጥቃት የ3 ሰዎች ህይወት አለፈ
በአሙሩ ወረዳ ለ3 ዓመታት በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ከ40ሺ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው መቆየታቸውን እና በአሁኑ ወቅት ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን የወረዳው አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በወረዳው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እና ድንበር ተሻግሮ ጥቃት የሚያደርሱ ታጣቂዎች ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ ከአሙሩ ወረዳ አጎራባች ከሆነው የምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ አጋምሳ ከተማ ሲያቀኑ የነበሩ ሶስት ሰዎች ላይ ሀሮ ተብሎ በሚታወቅ ቦታ ታጥቆ ይንቀሳቀሳሉ የተባሉና ጽንፈኛ ብሎ የጠሯአቸው ሀይሎች ጥቃቱን ማድረሳቸውን ነዋሪው አመልክተዋል፡፡
‹‹ አንድ ሞተር አጋምሳ ከተማ እየተመለሰች ባለችበት ሰዓት ነው ሀሮ የሚባል ቦታ እንዳለፉ ጎንኬ የሚባል ቦታ ላይ ታጣቂዎቹ ባደረሱት ጥቃት ህይወታቸው ያለፈው፡፡ ከሞቱት መካከል አንድ መምህር ይገኝበታል፡፡ ባጠቃላይ የሶስት ሰዎች ህይወት አልፈዋል፡፡ »
ከምስራቅ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች እየተመለሱ ነው
በአሙሩ ወረዳ ነዋሪና ባለፈው ሳምንት አሙስ ከቆዩበት መጠለያ ጣቢያ ወደ ቀድሞ ቤታቸው መመለሳቸውን የነገሩን ሌላው ነዋሪም በወረዳው ለረጅም ጊዜ የታጣቂዎች ጥቃት ቀንሶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ በታጣቂዎች ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎችም ያልታጠቁና ሠላማዊ ሰዎች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች ስርዓተ ቀብራቸው ትናንት መፈጸሙን ነዋሪው አክለዋል፡፡
በአሙሩ ወረዳ በሰላማዎ ሰዎች ላይ ደርሰዋል የተባለውን ጥቃት አስመልክቶ ማብራር የሰጡን የአሙሩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቂጠሳ በአሙሩወረዳና ኪረሙ ወረዳ መካከል በሚገኘው ጎንካ በሚባል ቦታ በደረሰው ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ በሶስት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሰዋል፡፡ ጎንካ ጫካ ውስጥ ጥቃት አድርሰው ሞተሩንም እዛው ጥለው የሄዱት፡፡ በአዋሳኝ አካባቢዎች እየገቡ ነው ጥቃት አድርሰው የሚመለሱት፣በጸጥታ ጉዳይ ኦፕሬሽን የሚፈልጉ ቦታዎች አሉ፡፡ እንደ አሙሩ በዚህ ጉዳ ላይ እየተሰራ ነው፡፡»
በአካባቢው በተለያዩ ስም የምንቀሰቀሱ ታጣቂዎች ጥቃት እንደሚያደርሱ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ የአሙሩ ወረዳ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት ሰሞኑን በሰጡን ማብራሪያ በወረዳው አንጻራዊ ሠላም በመስፈኑ 45ሺ 915 የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያአቸው መመለሱን ገልጸዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሰ