1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

በአማራ ክልል ለትምህርት የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ነው ተባለ

ማክሰኞ፣ መስከረም 14 2017

እንደ ኃላፊው እድሜያቸው ከ4 እስከ 6 ዓመት የሆናቸውን አንድ ሚሊዮን 760 ህፃናትን ለመመዝገብ ታቅዶ የተመዘገቡት 324 ሺህ ያክሉ ናቸው፡፡ ከ1ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል 4 ሚሊዮን 800ሺህ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ቢባልም ባለፉት 20 ቀናት የተመዘገቡት ግን ከ1 ሚሊዮን 300ሺህ እንደማበልጡ ተናግረዋል፡

በአማራ ክልል ዘንድሮ ለመማር የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር ለማነሱ አንዱ ምክንያት በክልሉ ያለዉ ግጭት ነዉ
አቶ ጌታቸው ቢያዝን የአማራ ክልል የትምሕርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ።«ለተማሪዎች ቁጥር መቀነስ የፀጥታ ችግር አንዱ ምክንያት ነዉ» ብለዋልምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ለትምህርት የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ነው ተባለ

This browser does not support the audio element.


የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ ም  7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት ቢያቅድም እስካሁን የተመዘገቡት ከ2 ሚሊዮን እንደማይበልጡ አስታወቀ።ከታሰበዉ በእጅጉ ያነሰ ተማሪ ለመመዝገቡ በክልሉ ያለውን የፀጥታ ችግርና ሌሎች ምክንያቶች እንሚጠቀሱ ቢሮዉ አስታዉቋል።ወላጆች በበኩላቸው የልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት አለመሄድ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት መማር ከነበረባቸው ተማሪዎች ግማሽ ያክሉ አልተማሩም

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ወደ ትምህርት ቤት መግባት ከነበረባቸው 6 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል ግማሽ ያክሉ በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት እንዳልተከታተሉ በወቅቱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አመልክቷል፡፡ በተለይም በጎጃም ቀጠና የሚገኙ አብዛኛዎቹ የ6ኛ፣ የ8ኛና የ12 ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና መውሰድ እንዳልቻሉም የሚታወስ ነው፡፡
በ2017 ወደ ትምህርት ቤት የመጡ ጠማሪዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው
ችግሩ ሳይቃለል በዚህ ዓመትም ቢሮው 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር ቢያቅድም ከነሐሴ 20/2016 ዓ ም ጀምሮ ባደረገው ምዝገባ ግን እስካሁን የተመዘገቡት 2 ሚሊዮን እንደማይሞሉ ነው የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ለዶቼ ቬሌ የገለፁት፣

እንደ ኃላፊው እድሜያቸው ከ4 እስከ 6 ዓመት የሆናቸውን አንድ ሚሊዮን 760 ህፃናትን ለመመዝገብ ታቅዶ የተመዘገቡት 324 ሺህ ያክሉ ናቸው፡፡ ከ1ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል 4 ሚሊዮን 800ሺህ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ቢባልም ባለፉት 20 ቀናት የተመዘገቡት ግን ከ1 ሚሊዮን 300ሺህ እንደማበልጡ ተናግረዋል፡፡ በሁለተኛ ደራጅ ትምህርት ቤት 1 ሚሊዮን 200 ሺህ ተማሪዎች ይነዘገባሉ ተብሎ የታቀደ ሲሆን ወደ ትምህርት ቤት የመጡት ግን 300ሺህ ክሉ እንደሆኑ ነው አቶ ጌታቸው ያመለከቱት፡፡
ተማሪዎች ለምን ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም?

ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን በክልሉያለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ ተማሪዎች ዘግይቶ የመመዝገብ ልማድ፣ ፖለቲካን ከትምህርት ጋር የማያያዝ ጉዳዮችና ሌሎች ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ነዋሪ የዚህን ዓመት ትምህርት አጀማመር በተመለከተ እንደነገሩን በከተማው ውስጥ የሚገኙ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ትምህርት ጀምረዋል ብለዋል፣ እርሳቸው ተወልደው ባደጉበት የገጠር አካባቢዎች ግን በአንፃሩ ተማሪዎች ትምህርት እንዳልጀመሩ አመልክተዋል፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ “ትምህርት ቅንጦት ሆኗል” ብለዋል፡፡ ሁኔታው በአካባቢያቸው እንዲያውም ካለፈው ዓመት የከፋ ሊሆን እንደሚችል ያለውን ተጨባጭ የፀጥታ ሁኔታ ተመልከተው ገልጠዋል፡፡
በሰሜን ጎጃም ዞን የአዴት ከተማ ነዋሪ ምንም ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት አልሄደም፣ ትምህርት ቤቶችም ተማሪም ሆነ መምህራን አይታይባቸውም ነው ያሉት፡፡ “ጉዳዩ ከባድ ነው” ሲሉ ነው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የተናገሩት፡፡
ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ምን ይደረግ?

የኣማራ ክልላዊ መስተዳድር የትምሕርት ቢሮምስል Alemnew Mekonnen/DW

የትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጌታቸው ህፃናቱ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መንግስትና ኃላፊው “በጫካ ያሉ ወንድሞች” ያሏቸው ኃይሎች  ጭምር እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡
በአማራ ክልል ከ10ሺህ በላይ የአንደኛ፣ የመካከለኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW