1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችኢትዮጵያ

በምዕራብ ጎንደር ዞን መቃ ከተማ 17 አርሶ አደሮች መገደላቸውን የአካባቢው ተወላጆች ተናገሩ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 24 2017

በምዕራብ ጎንደር ዞን መቃ በተባለች ትንሽ ከተማ በጸጥታ አስከባሪዎች እና በታጣቂዎች መካከል ከተፈጠረ ግጭት በኋላ 17 አርሶ አደሮች መገደላቸውን የአካባቢው ተወላጆች ተናገሩ። ባለፈው ሣምንት ሰኞ ታጣቂዎች በአጀብ በሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት 16 ሾፌሮች መገደላቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ አስታውቆ ነበር።

Äthiopien l Metema in der Amhara Region
ምስል፦ Alemnew Mekonnen

በምዕራብ ጎንደር ዞን መቃ ከተማ 17 አርሶ አደሮች መገደላቸውን የአካባቢው ተወላጆች ተናገሩ

This browser does not support the audio element.

ከሣምንት በፊት ወንድማቸው መቃ በተባለች አነስተኛ ከተማ በጸጥታ አስከባሪዎች እንደተገደሉባቸው የሚናገሩት ግለሰብ ዛሬም “መሪር ሐዘን ላይ” ናቸው። ወንድማቸው “የማይዋሽ ንጹሕ ገበሬ” እንደነበሩ ያስታውሳሉ። እምባ እየተናነቃቸው ስለ ወንድማቸው ሲናገሩ “ለወገን ደራሽ የነበረ፤ ቤተሰብ የነበረው፤ ሞተ በቃ ገደሉት” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

ለደሕንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የሚፈልጉት ግለሰብ የአራት ልጆች አባት የሆኑት ወንድማቸው ሥርዓተ-ቀብር ላይ አልተገኙም። ነገር ግን ወድማቸዉ መቃ መድሐኒዓለም ቤተ-ክርስቲያን ከሌሎች አስር ጓደኞቻቸው ጋር መቀበራቸውን ሰምተዋል።

ጎንደር ወደ መተማ በሚያመራው አውራ ጎዳና ላይ በምትገኘው መቃ ይኖሩ የነበሩት ገበሬ የተገደሉት ሰኔ 16 ቀን 2017 ከተፈጸመ ጥቃት በኋላ እንደሆነ ዶይቼ ቬለ ተንዝቧል። ጥቃቱ የተፈጸመው የአፈር ማዳበሪያ ጭነው በጸጥታ አስከባሪዎች አጀብ ይጓዙ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ እንደሆነ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ አስታውቋል።

ሰኔ 19 ቀን 2017 በዞኑ ከምትገኘው ገንዳውኃ ከተማ በወጣው መግለጫ መሠረት ተሽከርካሪዎች አጅበው ይጓዙ የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የአድማ መከላከል አባላት ናቸው። የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ “የቅማንት ነጻ አዉጭ” የተባለ ቡድን ጥቃቱን “አቅዶ፣ ሆን ብሎ ተዘጋጅቶ እና አስቦበት ማሀል ከተማ ላይ ሲደርሱ በየቤቱ እና ኪስ ቦታዎች  ላይ ዘግቶ መኪና ላይ በሠፈሩ የሠራዊታችን አባላት እና ተሣፋሪዎች ላይ ተኩስ” እንደከፈተ ወንጅሏል።

በጥቃቱ ማዳበሪያ ጭነው ሲያጓጉዙ ከነበሩ አሽከርካሪዎች መካከል “16 ሹፌሮችን ከመኪና  እያስወረደ ዘግናኝ በሆነ ጭካኔ ጨፍጭፏቸዋል” ያለው የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ “የተወሠኑትንም አግቶ”  እንደወሰደ በመግለጫው ጠቁሟል።

ዶይቼ ቬለ ከምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ፣ ከዞኑ ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ፣ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጽህፈት ቤት እንዲሁም ከመተማ ወረዳ አስተዳደር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የአማራ እና የቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የጸጥታ ቀውስ ውስጥ ቆይተዋል። የግጭት መነሾ ለነበረው የቅማንት ማኅበረሰብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መልስ ለመስጠት መስከረም 7 ቀን 2010 ሕዝበ-ውሳኔ ቢካሔድም በውጤቱ መሠረት አስተዳደር ባለመመሥረቱ ቀውሱ እንደቀጠለ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት አቶ አበባው ማሙዬ ይናገራሉ።

ችግሩ ምላሽ ባለማግኘቱ “አኩርፈው የወጡ እና ወገናቸውን የተከላከሉ ወጣቶች” መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ አበባው በ2015 “ትጥቃቸውን አስወርደው መልሰው ለቀቋቸው። አስተባባሪ ኮሚቴውን ግን ብዙውን አሰሩት” ሲሉ ተናግረዋል። “ከታኅሳስ 2015 በኋላ ሁለት ጊዜ ምኅረት ብለው አስገብተው በአካባቢው ይንቀሳቀሱ ነበር። ከመከላከያ ሠራዊት ጋርም ከአድማ ብተና ጋርም ተነጋገሩ እየተባለ ነበር” የሚሉት አበባው ታጣቂዎቹ “ኬላ ጥለው ከሕብረተሰቡ እና ከሚንቀሳቀሱ መኪኖች ብር ይሰበስባሉ ነው የሚባለው” ሲሉ ያስረዳሉ።

ሰኔ 16 ቀን 2017 “ብር ሲቀበሉ አነሰ በዛ በሚል ጭቅጭቅ” ተፈጥሮ የአድማ ብተና አባል ከታጣቂዎቹ መካከል አንዱን በጥይት ተኩሶ በመግደሉ ግጭት እንደተቀሰቀሰ ማስማታቸውን አስረድተዋል።

“ከፋኝ ብለው የወጡ ሽፍቶች” “ከመከላከያ ጋር ተግባብተው ቀረጥ እየቀረጡ ተስማምተው” ይኖሩ እንደነበር የሚናገሩት ወንድማቸው የተገደለባቸው የአካባቢው ተወላጅ በበኩላቸው የጸጥታ አስከባሪዎች በርካታ ተሽከርካሪዎች አጅበው ሲሔዱ “አንድ አድማ ብተና አንዱን ሽፍታ መታው። ከዚያ በኋላ ተኩስ ተከፈተ። ተጋደሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

በመተማ ወረዳ ሥር በምትገኘው የመቃ ከተማ እና አካባቢው የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ከነዋሪዎች ዶይቼ ቬለ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ከጎንደር ወደ መተማ በተደጋጋሚ የሚመላለሱ አንድ አሽከርካሪ ሰኔ 16 ቀን 2017 እስከ 5,000 ብር ድረስ ለታጣቂዎቹ ከፍለው ግጭት የተከሰተበትን ኬላ ያለፉ መኖራቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

የመጀመሪያዎቹ ተሽከርካሪዎች ካለፉ በኋላ ታጣቂዎች በጀብ በሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ ከተገደሉት መካከል ሁለቱን እንደሚያቁ እኚሁ ሾፌር ገልጸዋል። አብዛኞቹ በምዕራብ ጎንደር ዞን ውስጥ ወደ ምትገኘው ሸኸዲ ማዳበሪያ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ሾፌሮች እንደነበሩ የገለጹት ግለሰብ ከሟቾቹ መካከል አስከሬናቸው ወደ ደሴ ተጓጉዞ የተቀበሩ መኖራቸውንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዘውዱ የተገደሉትን ሾፌሮች ማንነት “ከነስማቸው፣ ከነ አድራሻቸው እያጣራን ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። “እዚያ አካባቢ የደረሰውን አደጋ በእርግጥ እኛ የሰማንው ዘግይተን ነው” የሚሉት አቶ ሰለሞን “በጅቡቲም በዛም ያሉ የእኛ ተወካዮች ስለነበሩ ከጓደኞቻቸው በመረዳት ወደ 16 የሚጠጉ አሽከርካሪዎች ማዳበሪያ ጭነው በዚያ ሲሔዱ እንደተገደሉ ሰምተናል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሰኔ 19 ቀን 2017 ከገንዳውኃ ከተማ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ባወጣው መግለጫ መሠረት ተሽከርካሪዎች አጅበው ይጓዙ የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የአድማ መከላከል አባላት ናቸው። ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

እስካሁን ምን ያክል የጸጥታ አስከባሪዎች እንደተገደሉ ወይም ጉዳት እንደደረሰባቸው ከክልሉም ይሁን ከፌድራል መንግሥት በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። ነገር ግን የአሽከርካሪዎቹን አስከሬኖች ያነሱ የአካባቢው ነዋሪዎች የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ከፈጸሙ በኋላ በጸጥታ አስከባሪዎች መገደላቸውን እንደሰሙ ወንድማቸውን ያጡት ግለሰብ አስረድተዋል።

ተጨማሪ የአድማ ብተና እና የመከላከያ አባላት ወደ አካባቢውን አቅንተው “ኑ አስከሬን አንሱ ብሎ ሲያስነሳቸው ቆየና መጨረሻ ላይ አስከሬን አንስተው ሲጨርሱ ረሽኗቸው ሔደ” የሚሉት የአካባቢው ተወላጅ “ከተረሸኑት አንዱ የእኔው ወንድም አራሽ፤ አንደፋራሽ ትጉህ ገበሬ ነበረ። እሱ ነው የተበላብኝ” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ግጭቱ ሰኔ 16 ቀን 2017 ቢጀመርም ከሁለት ቀናት በኋላ መቀጠሉን ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ሰኔ 18 ቀን 2017 ታጣቂ ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት ላይ “አቅዶ እና ተዘጋጅቶ” “ግጭት አድርጓል” ብሎ ነበር። ይሁንና የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም።

ዶይቼ ቬለ በሁለቱ ቀናት በጸጥታ አስከባሪዎች ተገድለዋል የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥም ዝርዝር ደርሶታል። ትክክለኛነቱን ግን በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም። ከሟቾች መካከል የአንዱ ወንድም የሆኑት ግለሰብ ግን ሰኞ 11 ረቡዕ 6 “በአጠቃላይ 17 ንጹህ ገበሬ እንደተገደሉ ነው የነገሩኝ። የእኔ የወንድሜ እና አብረው የነበሩትን እና ዘጠኙን አውቃቸዋለሁ” በማለት አስረድተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም የበቀል እርምጃ ይፈጸማል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ዶይቼ ቬለ ካነጋገራቸው የሟቾች ቤተሰቦች ለመገንዘብ ችሏል። አሽከርካሪዎች በፊናቸው ተደጋጋሚ ግድያ፣ እገታ እና ዘረፋ በበረታበት ከጎንደር ወደ መተማ በሚያመራው አውራ መንገድ መኪኖቻቸውን መንዳት አይፈልጉም።

አርታዒ ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW