በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ
ዓርብ፣ መጋቢት 5 2017
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከፀጥታ ችግር ጋር ና ተፈጥሯዊ በሆነ ድርቅ ምክንያት አንድ ሚልየን የሚደርሱ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በዞኑ እንደ አይና ቡግና ባሉ ወረዳዎች በታህሳስ ወር ተከስቶ የነበረዉ የምግብ እጥረት 10 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን ለጉዳት ዳርጎ ነበር። ዛሬም እለታዊ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ሠዎች በርካታ መሆናቸዉንና ባለፉት ሁለት ወራት ድጋፍ አለመደረጉን የአካባቢዉ ማህበረሰብ አባላት ይናገራሉ።
“አሁን እለታዊ ምግብ የሚፈልጉ ሰዎች በርካታ ናቸው። 68 ሺህ ህዝብ ዕለታዊ ድጋፍ ይፈልጋል ተብሎ ከዚህ 68 ሺህ ሰዎች 38 ሺህ 908 ተፈቅዶላቸዉ ለአንድ ወር ብቻ እረድተዉ አቁመዋል” ሲሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል። «ከእርዳታ አውጡን» የአማራ ክልል ተፈናቃዮች
በተደጋጋሚ ወደ ዞኑ የእርዳታ ምግብ ይዞ ለመሄድ ቃል የገቡ መንግስትም ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት “በቃላቸዉ መሰረት ድጋፍ ማድረግ አልቻሉም” የሚሉት አስተያየት ሰጭዎች የአሜሪካ መንግስት ተራድኦ ድርጅት ስራ ማቆም ችግሩን አጉልቶታል ይላሉ።
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪ “አካባቢዉ በአብዘሀኛዉ በአመልድ ነዉ የሚረዳዉ። ሌላ ድርጅት የለም። እሱ አሁን ሲዘጋ በድርቅ ላይ ሌላ ድርቅ እየሆነብን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሚሊዮኖችን አደጋ ላይ የጣለው የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ
ሌላ አንድ የዞኑ ነዋሪ “የክልሉ ምግብ ዋስትናም 4000 ኩንታል እህል ሰጥቶ የለኝም አለ። ሌላም ስድስት ሽህ ኩንታል አስገባለሁ ብሎ 38 ተሳቢ ከኮምቦልቻ እየወጣ ነዉ ተብሎ በሚድያ ተነግሮ ነበር። ለሚድያ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ምንም የመጣ የለም“ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ ይመር አሁን በዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ለክልሉ ማሳወቃቸዉን ገልፀዉ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ከዞኑ መዉጣታቸዉ ድጋፍ ለሚሹ እርዳታ ለማቅረብ አስቸጋሪ ሆኖብናል ሲሉ ይናገራሉ።
“በተለይ ደግሞ የመንግስት አቅም ሲያንስ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ገብተዉ ድጋፍ ያደርጉ ነበር። አሁን ባለዉ ሁኔታ ግን ከዞናችን ሙሉ በሙሉ ወጥተዋል ማለት ይቻላል“ ሲሉ አቶ አለሙ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። “የድጋፍ ሁኔታም እዚህ ግባ የሚባል በመንግስትም መንግስታዊ ባልሆነ ድርጂቶች አሁን እየተደረገልን አይደለም“ የሚሉት የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ “ጠይቀናል በቅርብ በመንግስት ይቀርባል ተብለናል። ባለፈዉ 400 ሺህ ሰው እርዳታ ያስፈልገዋል ብለን ነበር። አጠቃላይ የነበረዉ ሁኔታ ጥሩ ስለነበረ አሁን ግን ከ800 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ እርዳታ ያስፈልገዋል“ ሲሉ አስረድተዋል። የእርዳታ መታገድ አሉታዊ እና አዎንታዊ ፋይዳ
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ወይዘሮ ሰርክአዲስ አታሌ የአሜሪካ መንግስት የተራድኦ ድርጂት ስራ ማቆም በረድኤት ተግባሩ ላይ ተፅኖ ቢያሳድርም በሌሎች መንገዶች ክፍተቱን እየሞላን ነዉ ይላሉ። “የዝግጁነት ጊዜ ባልተሰጠበት አንዳንድ ነገሮች በዛ ይሸፈናሉ ብለህ ያሰብካቸዉ ጉዳዮች እያሉ ሊኖረዉ የሚችለዉ ተፅኖ ቀላል ላይባል ይችላል“ ያሉት ወይዘሮ ሰርክአዲስ አታሌ “የቅድመ ዝግጅት ላይ ስለነበር መንግስትም እንደ ክልልም ስነልቦናዊ ጉዳት አልደረሰም። በስራ ዉስጥ ቢሆን ተጨማሪ እገዛ ቢያደርግ ግን ለሌሎች ጉዳት ተጋላጮች ልናደርገዉ በምንችለዉ ሁኔታ ሰፊ ማዕቀፍ እንዲኖረን ያደርግ ነበር“ ሲሉ ተናግረዋል። በሰሜን ወሎ ያሉ የዕለት ምግብ የሚሹትንም ሆነ ሌሎች ተረጂዎች አስፈላጊዉ ምግብ እንዲደርሳቸዉ በፌደራል መንግስትና ከክልሉ መጠባበቂያ ወጭ በማድረግ በአካባቢዉ እንዲደርስ የማድረግ ተግባር እየሰራን ነዉ ብለዋል።
ወይዘሮ ሰርክአዲስ አታሌ “የአሜሪካ መንግስት የተራድኦ ድርጂት ስራ ማቋረጥ ምክንያት ድጋፉ መቋረጥ ነበረዉ ነገር ግን እሱኑ ለመተካት ፌደራል አሁን ጀምሯል። አሳዉቀን ፌደራል ለነዚህ አካባቢዎች በልዮ ሁኔታ CRS በኩል ነበር ፌደራል የሚያደርሰዉ ነገር ግን አሁን ባለዉ ሁኔታ CRS ማድረስ ስላልቻለ የነዚህን ወረዳዎች ችግር ፅፈን እነሱ እያስገቡ ነዉ በተጨማሪም ከክልሉ መጠባበቂያ እንዲገባም ትእዛዝ አስተላልፈናል“ ብለዋል።
ኢሳያስ ገላዉ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ