1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
የምግብ ዋስትናኢትዮጵያ

በአማራ ክልል በተከሰተው ድርቅ ከ1,8 ሚሊየን ሕዝብ በላይ ለችግር መዳረጉ፤

ሐሙስ፣ የካቲት 7 2016

በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መቸገሩ ተገለጸ። ከመካከላቸው ከ380 ሺህ በላይ ሕጻናትና እናቶች ለከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ክልሉ አስታውቋል።

የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በድርቅ የተፈናቀሉ ወገኖች «ተገቢ እርዳታ እያገኘን አይደለም»

This browser does not support the audio element.

በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅ በርካቶች ለችግር መዳረጋቸውና ሌሎች ደግሞ ለመፈናቀል ተገድደዋል። የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን እንደሚያመለክተው በአማራ ክልል በአጠቃላይ በ43 ወረዳዎችና 429 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ አንድ ሚሊዮን 800 ሺህ ህዝብ ጉዳት ደርሶበታል፣ ከ900 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቀያቸውን ለቅቀው ተፈናቅለዋል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በሰሜን ጎንደር ዞን ጃንአሞራ ወረዳ «ዋሰን» በተባለ ቀበሌ የሚገኙ አንድ ተፈናቃይ ያለውን የእርዳታ አቅርቦት በተመለከተ ሲናገሩ፤

«ስለ  ድርቁ ምን ብየ ላውራህ፣ የምትላስ የምትቀመስ፣ ምንም፣ ምንም፣ ምንም ነገር የለንም፣ ሌላው ቀርቶ “እግዚአብሔር የፈጠረውን ውሀ፣ እግዚአብሔር አነሳብን” ውሀ እንኳ ሳይቀር፣ እርዳታ የሚባል ነገር የለም፣ የለንም» ነው ያሉት።

ሌላው በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃይም በተመሳሳይ በቂ እርዳታ እንደማይደርሳቸው ነው የሚናገሩት።

«እርዳታ እየቀረበ አይደለም፣ ህዝባችን እዚህ መጥቷል፣ ከ16 እስከ 17 ሺህ እንሆናለን፣ ህዝቡ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ተበትኗል፣ ምንጮች ደርቋል፣ ተፈናቃዩ ሁለትና ሶስት ወራት እዚህ ተቀምጦ ምንም ነገር የለም፣ «ጎኑን የሚዳስስ»  እርዳታ እየመጣ አይደለም፣ መላ ቅጡ የጠፋው ጊዜ ነው።» ሲሉ ገልጠዋል።

የጃንአሞራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሸጋው ተሰማ የውሀ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። ምንም እንኳ ክልሉ የውሀ ቦቴ ቢያቀርብም የመንገድ ችግር እንደልብ አላሠራንም ብለዋል። የምግብ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ አሁን የተሻለ አቅርቦት እንዳለ ነው የተናገሩት።

በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ተቋም የድንገተኛ ስርዓተ ምግብ ቅኝትና ምላሽ ባለሙያ አቶ ኃይሉ አያሌው በድርቁ በዋናነት የተጠቁት ሕጻናትና አጥቢ እናቶች መሆናቸውን አመልክተዋል። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ተቋም የድንገተኛ ስርዓተ ምግብ ቅኝትና ምላሽ ባለሙያ አቶ ኃይሉ አያሌው በድርቁ በዋናነት የተጠቁት ሕጻናትና አጥቢ እናቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

«ድርቁ ያስከተለው ችግር በጤናና ስርዓተ ምግብ ላይ ስናስብ፣ ለምግብ እጥረት ከሚጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከ5 ዓመት በታች ሕጻናት፣ አጥቢና  ነፍሰ ጡር እናቶች ናቸው። ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች አጠቃላይ በተደረገ ልየታ 23,060 ሕጻናት ከፍተኛ አጣዳፊ የምግብ እጥረት ያለባቸው ሆነዋል፣ 230,314ቱ ደግም መካከለኛ አጣዳፊ የምግብ እጥረት ያለባቸው ሆነው ተገኝተዋል።»

አጣዳፊ የምግብ እጥረት ካለባቸው 23 ሺህ ሕጻናት መካከል ግማሹ ያክሉ ብቻ የአልሚ ምግብ እርዳታ ያገኙ ሲሆን መካከለኛ የምግብ እጥረት ካለባቸው 230,314 ሕጻናት መካከል ደግሞ እርዳታ ያገኙት 34 ሺህ ያክሉ ብቻ ናቸው ብለዋል።

መካከለኛ የአጣዳፊ ምግብ እርዳታ ያሻቸዋል ተብለው ከተለዩ 62,426 እናቶች መካከል ደግሞ እስካሁን 15 ሺህ እናቶች ድጋፍ እንደተደረገላቸው አመልክተዋል። ተረጂዎችን በተሟላ ሁኔታ ማገዝ ያልተቻለው በዋናነት የግብዓት እጥረት በመኖሩ ነው ያሉት አቶ ኃይሉ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ረጂ ድርጅቶችና ተቋማት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW