1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትኢትዮጵያ

በአማራ ክልል በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተሸለሙ

ዓለምነው መኮንን
ሰኞ፣ መስከረም 19 2018

የአማራ ክልል መንግሥት በ2017 ዓም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ከ 500 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅናና የገንዘብ ሽልማት ሰጠ፣ በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር የተፈታኝ ተማሪዎችን ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እንዲቀንስ ማድረጉን ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ሸልሟል።
ባለፈው ዓመት 94 ሺሕ 668 ተማሪዎች በአማራ ክልል የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ወስደው ያለፉት 12.5 በመቶ ብቻ ናቸው።ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተሸለሙ

This browser does not support the audio element.

የአማራ ክልል መንግሥት ባለፈው ዓመት ፈተናውን ወስደው 500 እና ከዚያ በላይ ላስመዘገቡ 452 ተማሪዎች ነው ዛሬ በባሕር ዳር እውቅናና የገንዝብ ሽልማት የሰጠው። ሽልማትና እውቅና ከተሰጣቸው ተማሪዎች መካክል በሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋ ሮቢት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በረከት ንጉሴ አንዱ ነው፡፡

በአካባቢው በተደጋጋሚ የፀጥታ ችግሮች ይከሰቱ እንደነበር ጠቁሞ ያን በምቋቋም ባደረገው ጥረት 507.75 በማስመዝገብ ለዚህ ውጤት መብቃቱን ለዶይቼ ቬሌ ገልጿል፡፡ የደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ ችግሮች ሲፈጠሩ ወደ ግቢው በመጥራት ለተማሪዎቹ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበረም አመልክቷል፡፡

መልካሙ ውድነህ ከምዕራብ ጎጃም ዞን የደንበጫ 2ኛ ደረጃ ተማሪ የመጣ ሲሆን ሲሆን እርሱም በአካባቢው በተከታታይ በሚከሰተው የሠላም መደፍረስ አንድ ዓመት ትምህርት እንዳቋረጠ ጠቁሞ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ድጋፍ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን በዩኒቨርሲቲው መማሩንና 543 ነጥብ በማስመዝገብ ለዛሬው እውቅናና ሽልማት መድረሱን ተናግሯል፡፡ “በፀጥታው መታወክ ሰበብ በርካታ እወቀት የሰነቁ ተማሪዎች ሳይማሩም፣ ሳይፈተኑም ቀርተዋል” ሲልም ፀፀቱን ገልጧል፡፡

የወላጅ ክትትል አስፈላጊ ስለመሆኑ

በባሕር ዳር “ሪስፔንስ” ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ልጃቸውን እንዳስተማሩ የገለፁልን የዳግማዊ ዘመነ አባት አቶ ዘመነ አይቼው፣ ልጃቸው በትምህርት ቤት ከፍተኛውን ውጤት እንዳስመዘገበ አስረድተዋል፣ ለውጤቱ መምጣትም የወላጆች ክትትልና ለትምህርቱ አጋዥየሆኑ ግብዓቶችን መጠቀም መቻሉ እንደሆነ ገልጠዋል፡፡ በተለይ ልጃቸው እንደ ዩቱብ፣ ቴሌግራምና ሌሎች የበይነመርብ አውታሮችን ጭምር እየተጠቀመ ጥናቱን ያካሂድ እንደነበርና ለዚህም ውጤታማ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ዶ/ር ነፃነት ጌጤ የተማሪ ኤፍራታ ምትኩ ወላጅ ናቸው፣ ሽልማቱና እውቅናው የዛሬዎችንም ሆነ ቀጣይ ለሚመጡ ተማሪዎች የሞራል ስንቅ ይሆናቸዋል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃ መሠረት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል 452ቱ ከ500 በላይ ውጤት አምጥተዋል። ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

“የፀጥታ ችግሩ ብዙዎቹን ከትምህርት አስቅርቷል” ወላጆች

በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር አብዛኛዎቹን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን የተናገሩት ወላጆች፣ የክልሉ ሠላም ወደነበረበት ተመልሶ ለሁለትና

ሶስት ዓመታት ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ወላጆች ጠይቀዋል፡፡ ዶ/ር ነፃነት በዚህ እርገድ የእርሳቸው የቅርብ ዘመድ ልጆች ከትምህርት ገበታ እርቀው እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡

“በተፈጠረው የሠላም መደፍረስ የወንድሜና የእህቴ ልጆች ትምህርት አቋርጠው ገጠር ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ በክልሉ በተፈጠርው የፀጥታ ችግር ምክንያት በ2014ዓ እና 2015 ዓም 247ሺህና 210ሺህ የነበረው የ12ና ክፍል ተፈታኞች ቁጥር በ2016 ዓም እና 2017 ዓም በግማሽ አንሶ ወደ 96ሺህና 95ሺህ ወርዷል ነው ያሉት፡፡

ዛሬ በተደረገው የእውቅናና ሽልማት ስነስርዓት 452 ተማሪዎች እንዳመጡት ውጤት ከ30ሺህ እስከ 40ሺህ ብርና የእውቅና ይምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ተማሪዎቹ ሽልማታቸውን ከተለያዩ የክልሉ ኃላፊዎች እጅ ተቀብለዋል፡፡

“የተፈታኞች ቁጥር ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ነው” ትምህርት ቢሮ

በክልሉ 7 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ሲያሳልፉ፣ 61 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ ማሳለፍ እንዳልቻሉ ቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ ከተፈተኑ 94ሺህ 668 ተማሪዎች መካከል ደግሞ 11ሺህ 830 ተማሪዎች ከ50 ከመቶ  በላይ ያስመዘገቡና ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በስንስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አብዱ ሁሴንን ጨምሮ ሌሎችም የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መካከል 8.4 በመቶው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ማግኘታቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። 

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW