1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ወደ ደምበጫ እና አማኑኤል ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት አባላት መግባታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13 2015

ከሐሙስ ጀምሮ ውጊያ ወደነበረባቸው ደምበጫ እና አማኑኤል ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት አባላት መግባታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። የአማኑኤል ከተማ ነዋሪ አርብ በነበረ ውጊያ አንድ አሽከርካሪ እና አንድ በሥራ ላይ የነበሩ የባንክ የጥበቃ ሠራተኛ መገደላቸውን ገልጸዋል። ዶይቼ ቬለ ከባለሥልጣናት ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም

የጸጥታ አስከባሪዎች በአማራ ክልል ሐይቅ ከተማ
በአማራ ክልል ደምበጫ እና አማኑኤል ከተሞች ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ውጊያ እንደነበር ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል፦ Minasse Wondimu Hailu/Anadolu Agency/picture alliance

ወደ ደምበጫ እና አማኑኤል ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት አባላት መግባታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

This browser does not support the audio element.

ሰሞኑን ከባድ ውጊያ ሲደረግባቸው የነበሩት በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን የምትገኘው የአማኑኤል ከተማ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን የምትገኘው የደምበጫ ከተማ ይሰማ የነበረው የተኩስ ድምጽ መቀነሱን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ወደ ክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር ከሚወስዱ አውራ ጎዳናዎች አንዱ በሚያቋርጣቸው ሁለቱ ከተሞች ትላንት ነሐሴ 12 ቀን 2015 በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ውጊያ ነበር። ትላንት በደምበጫ ከባድ ውጊያ እንደነበር ያረጋገጡ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ዛሬ የመከላከያ ሠራዊት መግባቱን ገልጸዋል። አርብ "በጣም ከባድ ውጊያ ነበር፤ ሰፈር ለሰፈር ሁሉ ነበር" የሚሉት ነዋሪ "ዛሬ ምንም ነገር የለም" ሲሉ በደምበጫ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።

የጦርነት ቀናት ውጥረት እና ሥጋት ፣ የዓይን ምስክር ከደብረ ታቦር

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የምትገኘው የአማኑኤል ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ትላንት በነበረው ውጊያ አንድ አሽከርካሪ እና አንድ በሥራ ላይ የነበሩ የባንክ የጥበቃ ሠራተኛ መገደላቸውን ተናግረዋል። ትላንት ማምሻ አስራ ሁለት ሰዓት ገደማ "ጸጥ" ማለቱን የጠቀሱት የአማኑኤል ከተማ ነዋሪ ዛሬ ቅዳሜ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ድምጽ መሰማቱን ገልጸዋል። እኚሁ የአማኑኤል ከተማ ነዋሪ የመከላከያ ሠራዊት አባላት "ወደ ከተማ እየገቡ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። በከተማው አርብ ዕለት "በጣም ኃይለኛ ውጊያ ነበረ" ሲሉ የተናገሩ ሌላ የአማኑኤል ነዋሪ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ገቡ መባሉን እንደሰሙ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ሁለተኛው የአማኑኤል ነዋሪ "ከተማ ውስጥ ሲዋጋ የነበረው ለቀውላቸው [የመከላከያ ሠራዊት አባላት] ገቡ" ብለዋል።

በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት አለመረጋጋት በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አሳውቋል።

በደምበጫ፣ አማኑኤል ከተሞች እና ሌሎች የክልሉ ክፍሎች ስላለው የጸጥታ ሁኔታ ከአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ተጨማሪ ማብራሪያ በስልክ ለመጠየቅ የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ሁለት ሣምንታት ተቆጥረዋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ የወሰነው ሐምሌ 28 ቀን 2015 ነበር። በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከባድ መሣሪያ ጭምር ጥቅም ላይ በዋለባቸው ውጊያዎች ሰዎች መገደላቸውን፣ መቁሰላቸውን እና ንብረት መውደሙን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW