በአማራ ክልል የመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ
ቅዳሜ፣ መስከረም 17 2018
በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በክረምቱ ወቅት ያስከተለው የተፈጥሮ አደጋ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰባቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ፣ ሰሞኑንም በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ በረዶ ቀላቅሎ የጣለ ከባድ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል፣ የአማራ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በክረምቱ ወቅት በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰበት ሰብል ግምገማ ህዳር ላይ ይፋ እንደሚሆን አመልክቶ እርዳታም ከዚያ በኋላ ይሰራጫል ብሏል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ መስከረም መጀመሪያ ሳምንት ላይበረዶ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብበሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፣ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለዶይቼ ቬሌ በስልክ እንደተናገሩት ዝናቡ በማሳ ላይ የነበረን ሰብል በሙሉ አውድሟል፣ የእንስሳት መኖና የግጦሽ መሬትም ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ አቶ ሲሳይ ጫኔ በወረዳው የ033 “ቅምቅም” ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ናቸው፡፡
“... መላው ጥፍቶን ከብቶች የሚበሉት አጥተው ተጨንቀን ነው ያለነው፣ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ነገር ነው የገጠመን፣ የእኔ ባቄላ፣ ጤፍ፣ ስንዴ ማሽላ ነው የወደመው፣ ምንም የተደረገልን ነገር የለም እያለቀስን ነው መሄጃው ጠፍቶናል፣ ብዙው ሠው አካባቢውን ለቅቆ ወደሌላ ቦታ እየተሰደደ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ከባድ ዝናብ በሰብል ላይ ያስከተለው አደጋ
ሌላው በከባድ ዝናብ ሰብላቸው የተጎዳባቸው አርሶ አደር አቶ ደሴ ታደሰ ጤፍ፣ ባቄላ፣ ማሽላና ሌሎች ሰብሎች አንዳች ጥቅም ሊሰጡ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ናቸው ነው ያሉት፡፡ 5 ጥማድ ጤፍ፣ ማሽላና ባቄላ እንደወደመባቸው ተናግረዋል፡፡የመቄት ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ወንዴ በወረዳው 34 የገጠር ቀበሌዎች መኖራቸውን ጠቁመው ባለፈው ክረምት በወረዳው በበረዶ፣ በጎርፍና በመሬት መንሽራተት በ6ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብል መውደሙንና ከ45ሺህ በላይ ቤተሰቦች ለችግር መዳረጋቸውን ገልጠዋል፡፡ እስካሁን ለተጎጂዎች የደረሰ እርዳታ እንደሌለም አመልክተዋል፡፡የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላክልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት አደጋ ክትትልና የሰብል ልማት ባለሙያ ወ/ሮ ደስታ ለገሰ በበኩላቸው በዞኑ በተለያዩ ወርዳዎች ከባድ ዝናብ፣ የመሬት መንሸራተትና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግረዋል፣ እርዳታ እስካሁን ለተጎጂዎች አልደረሰም ብለዋል፡፡እንደባለሙያዋ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶአደሮች በከባድ ዝናብ፣ በመሬት መንሽራተትና በከባድ ነፋስ ሰብላቸው ወድሟል ነው ያሉት፡፡
በመብረቅ እንስሳት ሞተዋል.“ በቡግናና ዋልዳ ወረዳዎች ከባድ ነፋስ የ20 መኖሪያ ቤቶችን ጣራ የወሰደ ሲሆን በቡግና፣ በጉባላፍቶና ዋድላ ወረዳዎች ከዝናብ ጋር የወረደ መብረቅ 73 የተለያዩ እንስሳትን ሲገድል፣ በ11 ቀፎ የነበረን የንብ መንጋ ገድሏል፡፡” በለዋል፡፡
የክልልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምላሽ
የአማራ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በዚህ ዓመት በክልሉ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ማዕካላዊ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጥሮ አደጋዎች ቢከሰቱም ከተጠበቀው በታች እንደነበሩ ገልጠዋል፡፡
በተፈጥሮ አደጋ በሰብልና በእንስሳት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ቢሯቸው ከሌሎች አጋር አካላት ጋር አጥንቶ ህዳር ላይ ይፋ እንደሚያደርግና እርዳታ ከዚያ በኋላ እንደሚያቀርብ አመልክተዋል፡፡
በአማራ ክልል በሠው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች 2 ሚሊዮን ያክል ተረጂዎች እንደሚገኙ ከክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለከታል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ፀሐይ ጫኔ