በአማራ ክልል ከ200 በላይ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለዋል ተባለ
ሐሙስ፣ ጥር 8 2017
ከ200 በላይ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላም መጥተዋል ሲል በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ገልጿል። ወደ ሰላም የመጡት በዞኑ የኦሮሞ ነፃነት ታጣቂዎች መሆናቸውም የዞኑ ባለስጣናት ገልፀዋል።ታጣቂዎቹ ከሚሴ ከሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ከህብረተሰቡ ጋር ተወያይተዋል ተብሏል።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትየወሎ ክንፍ አመራር በትግል ስማቸዉ ፍሊታ ሮባ ከ30 ዓመት ትግል በኃላ መንግስት ያቀረበልኝን የሰላም ጥሪ ተቀብያለሁ ሲሉ ገልፀዋል።
« የትግል ስሜ ፍሊታ ሮባ ይባላል እኔ ከ30 ዓመታት በላይ በዚህ ትግል ዉስጥ ቆይቻለሁ አሁን ህዝቤ እየተጎዳ እየሞተ ያለዉ የኦሮሞ ህዝብ መሆኑን ተገንዝቤ የተደረገዉን ጥሪ ተቀብያለሁ»
አባ ቦኩ አደም መሀመድ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር የገዳ አመራር ናቸዉ ባለፉት አመታት ታጣቂ ቡድኑ በዛኑ በነበረዉ እንቅስቃሴ ልጃቸዉን በሞት አጥተዋል ነገር ግን ይቅርታ ሁሉን ያስረሳል ሲሉ ይናገራሉ ።
«አሁን ይሄ ትልቅ ተስፋ ነዉ የተጎዳ ጭምር እኮ ነዉ ትናንትና ወጥቶ የተቀበላቸዉ ኢትዮጵያዊ ያን ልባችን ሰፊ ነዉ የኛ ሰዉ ለይቅርታ በሩ ክፍት ነዉ እኛም በዚህ አንድ እረፍት እናገኛለን ብለን ነዉ የምናስበዉ ህዝቡ ለሰላሙ ትልቅ ጉጉት ስላለዉ በዚያ መልኩ ተቀብለናል እረፍትም ይሰጠናል» ይላሉ።
በአማራ ክልልየኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ሠላም ካዉንስል በዞኑ ያሉ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ የማግባባት ስራዉን እንደሰራ የሚገልፁት የካዉንስሉ ፀሃፊ አቶ አህመድ ጁሀር ሱልጣን ሌሎችም በቅርቡ ወደ ሠላም ይመጣሉ ሲሉ ይናገራሉ።
«መንገድም ላይ ያሉ ሰዎች አሉ እንመጣለን የሚሉ አሁን የመጡትም ከኛ ጋር ቃል ገብተዉ እነኛን ለመቀስቀስ ቃል አስጠብተናቸዋል ሰላም ካዉንስል ጥያቄ ካላችሁ ጥያቄያችሁን ይዛችሁ ቅረቡ ከመንግስት ጋር ተነጋገሩ ፊትለፊት የምትፈልጉት ነገር ካለም ጠይቁ ብለን ሀሳብ ሰጥተናል» ብለዋል።
በብሄረሰብ ዞኑ ያሉየሀገር ሽማግሌዎች ሠላሙ እንዲመጣ አካባቢዉ አካባቢዉ ወደ ቀደመ መረጋጋት እንዲመለስ ሰርተናል የሚሉት አባ ቦኩ አደም መሀመድ የንብረት መዉደምና የሠዉ ሞት ሊቆም ይገባል ይላሉ።
«እሳት ራሳችን ላይ ለኩሰን ያለንን ንብረት እያወደምን ያለንን ሀብት እያወደምን ሰዉ እየሞተ እስከመች ነዉ የምንቀጥለዉ ይህ ወደ ሰላም መምጣት አለበት ብለን የሚመጣዉ ይበልጣል ያለፈዉ አልፏልና አሁን ወደሰላም መምጣቱ እረፍት ይሰጠናል» ብለዋል።
ትናንት በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ወደ ሰላም የመጡት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራሮችና 200 የሚደርሱ የቡድኑ አባላት መሆናቸዉን የሚናገሩት የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ሰላምና ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱ ጀማል ናቸዉ።
«እስከዛሬ ባለን ከ200 በላይ ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል በህዝቡ ዉስጥ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድሩ የነበሩ ኃይሎች ናቸዉ አሁን መንግስት እንደ አገርም እደ ክልልም ያቀረበዉን የሰላም ጥሪ ተቀብለዉ እየገቡ ነዉ ያሉት»
ታጣቂ ኃይሎቹ ወደ ተሀድሶ ማዕከል የማስገባትና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ተግባርም ይሰራል ተብሏል።
ኢሳያስ ገላው
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ