በአማራ ክልል ከ600 ሺ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸው ተገለጸ
ሰኞ፣ ጥቅምት 11 2017በአማራ ክልል ከ600 ሺ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸው ተገለጸ።
የወባ በሽታ በአማራ ክልል ከምንጊዜውም በላይ መስፋፋቱን የጤና ባለሙያዎችና ነዋሪዎች ተናገሩ። በሩብ ዓመቱ የወባ በሽታ ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች ውስጥ ክ600 ሺህ በላይ የሚሆኑት በበሽታው መያዛቸው መረጋገጡን የክልሉ ህብረተስብ ጤና ተቋም አመልክቷል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ 3 ወራት ሲነፃጸር በ250 ሺህ ያክል ብልጫ እንዳለው ነው ተቋሙ ያስታወቀው ።
በአማራ ክልል የወባ በሽታ በስፋት መስፋፋቱን ነዋሪዎቹ እየገለጹ ነው፣ ወረርሽኙ በእጀጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል፣ በቀን በበሽታው የሚያዘው ሠው ቁጥር በሚያስፈራ ሁኔታ መጨመሩን በስጋት ተናግረዋል።
አማራ ክልል በ1ዓመት ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ ተጠቅተዋል
የወባ ስርጭት መስፋፋት
አስተያየት ከሰጡን ነዋሪዎች መካከል በሰሜን ወሎ ዞን የጃራ የተፈናቃዮች ጣቢያ ነዋሪ አንዱ ናቸው።
እንደ አስተያየት ሰጪው፣ ቤተሰቦቻቸው በሙሉ በበሽታው ታመው ህክምና ማግኘታቸውን አመልክተዋል። በመጠለያ ጣቢያው በሚደረገው ምርመራ በአንድ ቀን ውስጥ እስክ 120 ሰዎች የወባ በሽታ እንደሚገኝባቸው አስረድተዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን የተሁለደሬ ወረዳ ነዋሪም ህብረተሰቡ የአልጋ አጎበር ቢጠቀምም አብዛኝው ሠው በወባ መታመሙን ነው የነገሩን።
ሠው የአልጋ አጎበር ቢጠቀምም ከወባ ህመም ሊያመልጥ አልቻለም የሚሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ፣ እንደወረርሽኝ ሆኖ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎችን ወባ አጥቅቷል ነው ያሉት። ሠው በእርግጥ የአልጋ አጎበር አጠቃቀም ችግር አለበት ያሉት አስተያየት ሰጪ “ከአጠቃላይ የወረዳው ነዋሪ 80 ከመቶ የሚሆነው በበሽታው ሳይያዝ አይቀርም” ብለዋል።
በተፈጥሮ አደጋዎችና ወረርሽኞች የታጀበው 2016
የጤና ባለሙያዎች አስተያየት
የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪይ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መርሻ ዞኑ ከፍተኛ የቀን ሠራተኛ የሚበዛበት አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ምክንያት የወባ በሽታ በቀላሉ ሠዎችን እያጠቃ ነው ብለዋል። ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በመንግዶች ተደጋጋሚ መዘዘጋጋት መድኃኒቶች ወደ አካባቢው መድረስ አለመቻል፣ በምዕራብ አርማጭሆ፣ መተማና ቋራን በመሳሰሉ ወባማ ወረዳዎች የኬሚካል እርጭት ባለመካሄዱ በዞኑ ከፍተኛ የወባ ስርጭት መኖሩን ተናግረዋል። በሶስቱ ወር ብቻ 47 ሺህ ሠዎች በወባ መያዛቸውንም አስረድተዋል።
ሆኖም የኬሚካል እጥረቱ ቢኖርም 6 ያክል ቀበሌዎችን የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት ማካሄድ መቻሉን ገልጠዋል። ሠፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት ወዳለባቸው አካባቢዎች 40 ያከል የጤና ባለሙያዎቸ ወደ ቦታው ሄደው የክትትል ሥራ እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ደመቁ መኮንን በበኩላቸው የወባ ህሙማን ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል ነው ያሉት፣ ካለፈው ዓመት ጋር የነበርውን አኃዝ በማነፃፀር።
“ ከምን ጊዜውም በላይ አይተነው በማናውቀው ሁኔታ የወባ ስርጭት ጨምሯል፣ ሌላ ጊዜ በሩብ ዓመት ሪፖርት ይደረግ የነበር የወባ ታማሚ ቁጥር አሁን በአንድ ወር ውስጥ እየታየ ነው” በልዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት በቻ 603 ሺህ ሠዎች በወባ መያዛቸው
የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ የወባ ስርጭት በሚያስፈራ ሁኔታ መጭመሩን ገልጠዋል። ባለፉት 3 ወራት ብቻ አንድ ሚሊዮን 112 ሺህ ሠዎች የወባ ምርመራ አድርገው 603 ሺህ ሠዎች የወባ በሽታ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል፣ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ250 ሺህ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል። ወደ ጤና ተቋማት ከመጡ ታማሚዎች መካከል 50 ያክል ህሙማን ህይዎታቸው ማለፉንም አመልክተዋል።
ለወባ መጨመር ምክንያቶቹ “ የአየር ለውጥ ተፅዕኖ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ነው።” ነው ያሉት። መድኃኒቶችን በቀላሉ ወደ ወረዳዎች ማድረስ አልተቻልም፣ ባለሙያዎችም በሚፈለገው መንገድ ተንቀሳቅሰው መስራት እንዳለቻሉ በመጥቀስ።
በክልሉ የጤና ሥራ አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑ
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ በበኩላቸው በክልሉ እጅግ ወባማ የተባሉ 34 ወረዳዎች መለየታቸውን ተናግረዋል። በተለይ በምዕራብ አማራ ችግሩ መስፋፋቱን ጠቅሰው፣ የመከላከልና የህክምና ሥራዎች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ በጤናው ዘርፍ በማህበረሰብ አቀፍ ደረጃ የሚሰሩ ሥራዎችን ለማከናወን የጤና ኤክስቴንሽን ባልሙያዎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈለገውን ያክል መጓዝ ባለመቻላቸው አፈጻፅሙ ዝቅተኛ እነደሆነ ጠቁመዋል።
በኬሚካልና በአልጋ አጎበር አቅርቦት በኩል እጥረቶች መኖራቸውን ያልካዱተ ኃላፊው፣ ህብረተሰቡ ያለውን በአግባቡ እንዲጠቀም አሳስበዋል።
በአማራ ክልል የሚገኑ የጤና ተቋማት ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በክልሉ ስላሉ የጤና ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ሰሞኑን በባሕር ዳር ውይይት አድርገዋል።
ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል አንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ሠዎች የወባ ህክምና ማግኝታቸውን ከክልሉ ህብረተሰብ ጤና ተቋም ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ዓለምነው መኮንን
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ