1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ከ80 በመቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው መባሉ

ሰኞ፣ ሐምሌ 10 2015

በአማራ ክልል ከ85 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ከአጸደ ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች ከሚፈለገው ደረጃ በታች መሆናቸው ተገለፀ። በአማራ ክልል በአጠቃላይ ከ10, 730 በላይ ከአጸደ ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳል።

Educational conference in Ethiopia Bahir
ምስል Alemnew Mekonen/DW

«የሚያነጋግረው የትምህርት ጥራት ጉዳይ»

This browser does not support the audio element.

 

በአማራ ክልል ከ85 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ከአጸደ ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች ከሚፈለገው ደረጃ በታች መሆናቸው ተገለፀ።  የትምህርት ጥራት በዘላቂነት መረጋገጥ የሚችለው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና በማዘጋጀት ሳይሆን በታችኞቹ የትምህርት ክፍሎችደረጃ በብቃት ሲሰራ ብቻ መሆኑን ደግሞ አንድ የሥርዓተ ትምህርት ምሁር አመልክተዋል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መተባበር እንዳለባቸው ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ አስታውቋል። ዓለምነው መኮንን ከባሕር ዳር ዘገባ ልኮልናል።

የትምህርት ጥራት በብዙ ምክንያቶች እየተጓደለ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጧል። ለትምህርት ጥራት መውደቅ ከሚጠቀሱ ምክንቶች መካከል ባለፉት 30 ዓመታት የነበረው የትምህርት ሥርዓት አንዱ ሲሆን የትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹ አለመሆንና የትምህርት መረጃ ቁሳቁሶች እጥረትም በስፋት ይጠቀሳል። ሰሞኑን «ትምህርት ለትውልድ» በሚል በባሕር ዳር በተዘጋጀ የትምህርት ንቅናቄ ላይ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ኢየሩስ መንግሥቴ ዘገባ ያቀረቡት በአማራ ክልል አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን ያሳያል።

«በ2014/5 ዓ ም 434 አፀደ ሕጻናት ትምህርት ቤቶችን ለመመልከ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፣ 90 ከመቶ የሚሆኑት የአፀደ ሕጻናት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው፣ የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ስንመለከት፣ 5,552 ትምህርት ቤቶች ታይተዋል፣ 86 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው፣ 409 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የታዩ ሲሆን 80 ከመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች ናቸው፡፡»

ምስል Alemnew Mekonen/DW

በክልሉ በሚገኙ 9,510 የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከልም ቤተሙከራ፣ ቤተ መጽሐፍትና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ ግብዓቶች ያሏቸው ትምህርት ቤቶች ከግማሽ እንደማይበልጡ ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ የተናገሩት። ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም እጥረት፣ ከመምህራንና ከመማር ማስተማሩ ጋር ያሉ ሌሎች ችግሮችም ለትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ተጠቃሶች  መሆናቸውን ደግሞ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማተብ ታፈረ አመልክተዋል።

በዕለቱ በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለመምህራን ተገቢው የክህሎት ስልጠናና ተገቢው ክብር እስካልተሰጠ ድረስ ተፈላጊው ውጤት አይገኝም ነው ያሉት፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር ከ42 ከመቶ እንደማይበልጥ አሳውቋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት  ዶ/ር ዳዊት መኮንን ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል የሚስተካከለው በዩኒቨርሲቲ በሚሰጥ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ፣ ይልቁንም በታችኛው የትምህርት እርከን ትኩረት ሰጥቶት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። ግብዓት አንዱ መሰረታዊ ጉዳይ ቢሆንም የመምህራን ተነሳሽነት ከሌለ ግን የታሰበው የትምህርት ጥራት አይመጣምም ብለዋል ዶ/ር ዳዊት።

«የትምህርት ቤቶችን ብቃት ማሳደግ አለብን፣ ይህ ማለት ግብዓት መኖር አለበት፣ ወንበር ጠረጴዛ መኖር አለበት፣ ከዚያ ደግሞ መምህሩ ክፍል ውስጥ ሆኖ ማስተማር የሚያስችለውን መነሳሳት መፍጠር ያስፈልጋል፣ መምህሩ ካልተነሳሳና ክፍል ውስጥ ገብቶ ሥርዓተ ትምህርቱን ከተማሪዎች ጋር እየተቀናጀ ካልተገበረ፣ የትምህርት ጥራትን የምታረጋግጠው አይደለም፣ ስለዚህ ትምህርት ቤት ስትል መምህራንስ ምንድን ነው የሚሉ? የማስተማር ብቃታቸው ምንድን ነው? ትምህርት ቤት ለመቆየት ፍላጎት አላቸው ወይ? ሌላ የሥራ አማራጭ እያሰቡ ነው ወይ? የትምህርት ቤት አመራሩ ምንድን ነው የሚመስለው? እነዚህን ነገሮች ባገናዘበ መልኩ በሂደት እየሠራን የምናሻሽለው መሆን ነው ያለበት።»

የትምህርት ሚኒስቴር ሕንጻ አዲስ አበባምስል Solomon MUCHIE/DW

የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለመመለስ ሁሉም በጋራ ሊንቀሳቀስ ይገባል ባይ ናቸው። በአማራ ክልል በአጠቃላይ ከ10, 730 በላይ ከአጸደ ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW