በአማራ ክልል ዋግኸምራ ዞን በርካታ ተማሪዎች አሁንም በዳስ ትምህርት ቤቶች እንደሚማሩ ተገለጸ
ሰኞ፣ መስከረም 26 2018
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ ሲሆን ከጦርነቱ ቀደም ብሎም የነበረው የትምህርት መሰረተ ልማት የተጎዳ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ መንግሥትና ረጂ ድርጅቶ በተወሰነ ደረጃ የአካባቢዎቹን የትምህርት መሰረተ ልማቶች ለማሻሻል ጥረት ቢያደርጉም አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ህፃናት በዳስና በዛፎች ስር ለመማር ተግድደዋል፡፡
በሰቆጣ ወረዳ የእከመፅረዋና የአብዛ ማሪያም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ለዶይቼ ቬሌ በስልክ እንደተናገሩት ህፃናቱ በዳስና በዛፍ ስር ባልተመቻቼ መቀመጫ ጭምር እየተማሩ ናቸው፡፡ አስተያየት ከሰጡን መምህራን መካከል የአብዛ ማሪያም ትምህርት ቤት መምህር እንዲህ ብለዋል፡፡
“ ...ቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ናቸው፣ ገና ክፍሎች አልተገነቡላቸውም፣ በዳስ ነው የሚማሩት፣ መምህራንም አለተመደበላቸውም፣ አንዳንዴ ክፍል ባማይኖራቸው ጊዜ ሌሎች መምህራን ናቸው ግብተው የሚያስተምሯቸው፣ የዳስ ክፍሉ አንድ ብቻ ነው የቅድመ 1ኛ ደረጃው 5ኛና 6ኛ ክፍሎችን አንድ ላይ አድርገን ነው የምናስተምረው፡፡” ብለዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በዳስና በዛፍ ስር እየተማሩ ነው
በብሔረሰብ አስተዳደሩ የዝቋላ ወረዳ የትምህርት እቅድ ዝግጅትና ሀብት ማፈላልግ ቡድን መሪ አቶ መኩሪያ ረዳ “በወረዳው ካሉ ትምህርት ቤቶች መካክል 5ቱ የዳስ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ 139 መማሪያ ክፍሎችን ያካተቱ ናቸው” ብለዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችም በዛፍ ስርና በዳስ እየተማሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በወረዳው 28 አንደኛ ደረጃና 3 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ መኩሪያ፣ በክረምቱ በዝናብና በነፋስ በርካታ ክፍሎችም መፍረሳቸውን አስታውሰው፣ ይህም ለዳስ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ማደግ አንዱ ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የሳህላ ሰየምት ወረዳ የአጠቃላይ ትምህርት ክፍል ቡድን መሪ አቶ መንግሥቱ አድማሱ በበኩላቸው በወርዳው 25 ትምህርት ቤቶች መካክል 7 ትምህርት ቤቶ የዳስ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ገልጠው፣ ከ2ሺ500 በላይ ተማሪዎች በእኚሁ በዳስ በተሰሩ 110 “ክፍሎች” ትምህርት እንደሚከታትሉ አስረድተዋል፡፡
የፃግብጂ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይሌ ወንድሙ በወረዳው የፃድቃ፣ የኮሎኮ፣ የሰንኮና የአሪ አንደኛ ትምህርት ቤቶች በሙሉ የዳስ ትምህርት ቤቶች ቢሆኑም ሌሎች ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ የመማሪያ ክፍሎች የሌሏቸው ትምህርት ቤቶች በወረዳው እንደሚገኙ አብራርተዋል፣ በዚህም በርካታ መማሪያ ክፍሎች የዳስ ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ በዛፍ ስር ደንጋይ ላይ ተቀምጠው እየተማሩ ነው ብለዋል፡፡
በብሔረብ አስተዳደሩ 11ዱ የዳስ ትምህርት ቤቶች ናቸው
የዋግኽምራ ብሔረስብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይፉ ሞገስ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ለመቀየር በስፋት እየተሰራ እንደሆነ ገልተዋል፡፡
“...የዳስ ትምህርት ቤቶች በብሔረሰብ አስተዳደሩ ወደ 11 የሚድርሱ ናቸው፣ እንርሱም በዝቋላ፣ በፃግብጂና በሳህላ ሰየምት ወረዳዎች የሚገኙ ናቸው” ነው ያሉት፡፡ ከነበሩት የዳስ ትምህርት ቤቶች 5ቱ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው አድጓል ያሉት አቶ ሰይፉ፣ የቀሪ 11ዱን የዳስ ትምህርት ቤቶች ደረጃ ላማሳደግም በሰፊው እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ተማሪዎቹ ባልተማቻቼ ሁኔታ መማራቸው ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እንደሚያደርጋቸውና ለተለያዩ ችግሮች እንድሚያጋልጣቸው መምህራኑ ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል እየተካሄድ ባለው የሠላም እጥረት ወደ 3ሺህ 700 ትምህርት ቤቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ጉዳት የደረሰባቸውና ከሥራ ውጪ መሆናቸው ቀደም ሲል ቢሮው በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
እንደዚሁም በክልሉ ከ10ሺህ በላይ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ትምህርት ቤቶች ሲገኙ ብዙዎቹ ከደረጃ በታች መሆናቸው ይገለፃል፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ በዚህ ዓመት 7.4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመምዝግብ ቢያቅድም እስካሁን የተመዘገቡት ከ3.5 ሚሊዮን እንደማይበልጥ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ ባለፈው ሳምንት ከብዙሐን መገናኛ ባለሙያዎች ጋር በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ፀሀይ ጫኔ