በተከዜ ወንዝ ላይ ጀልባ ተገልብጣ 12 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ
እሑድ፣ ሐምሌ 21 2016በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሳህላ ሰየምት ወረዳ ወደ ዝቋላ ወረዳ 26 ሰዎችን አሳፍራ በተከዜ ወንዝ ላይ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ተገልብጣ የ12 ሰዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው አስተዳደርና የአይን እማኞች ተናገሩ። ሌሎች 7 ሰዎች ተዳክመው ሳያልፍ የተገኙ ሲሆን ወደ ህክምና ጣቢያዎች መላካቸውም ተመልክቷል፡፡
በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የዝቋላንና ሳህላ ሰየምት ወረዳዎችን በሚያገኛኘው የተከዜ ወንዝ ላይ 26 ያክል ሰዎችን አሳፍራ ከሳህላ ሰየምት ወደ ዝቋላ ወረዳ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ተገልብጣ የሰዎች ህይወት ማለፉንና በሌሎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን የሳህላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።
ዝቋላን ከሳህላ ሰየምት የሚያገናኘው ድልድይ በወንዝ ተወሰደ
ወ/ሮ ሙሉ መኮንን የተባሉ ነዋሪ እንዳሉት በጀልባዋ ተሳፍረው ከነበሩ ሰዎች መካከል ብዙዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን የሁለቱ ሰዎች አስከሬን ተገኝቶ ተቀብሯል፡፡ የወረዳው ነዋሪ ወጥቶ በአስከሬን ፍለጋ ላይ መሆኑንም ለዶይቼ ቬሌ በስልክ አመልክተዋል፡፡
ሌላ ነዋሪም ልጃቸው በጀልባው ተሳፍረው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበር ጠቁመው እስካሁን የልጃቸውን እጣፋንታው ማወቅ እንዳልቻሉ ገልጠዋል፡፡
“ትናንትና አላገኙትም፣ ዛሬ ጠዋት አግኝተው ይሁን ገና የደረሰኝ መረጃ የለም፣ የተገኙ ሰዎች አሉ ይባላል፣ እሱ (ልጃቸውን ማለታቸው ነው) አለ የለም የሚለው አልታወቀም” ብለዋል፡፡
የሳህላ ሰየምት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ብሩ በበኩላቸው የ2 ሰዎች አስከሬን መገኘቱንና የሌሎች 10 ሰዎች አስከሬን እየተፈለገ ነው ብለዋል፣ 7 ሰዎች ብዙም ጉዳት ሳይደርስባቸው በዋና የወጡ ሲሆን ሌሎች 7 ሰዎች ደግሞ ተዳክመው ተገኝተው ወደ ህክምና ጣቢያዎች ተልከዋል ነው ያሉት።
በደቡብ ጎንደር ዞን 6 ቀበሌዎች በውኃ ተጥለቀለቁ
በአንዳንድ የብዙሐን መገናኛ ተቋማትና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች 19 ሰዎች እንደሞቱ የሚሰራጨው ዘገባ ግን ሀሰት መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ኃይሉ ግርማይ የሟቾች ቁጥር 12 መድረሱን ከቤተሰቦቻቸው መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም አደጋው የደረሰው ከዚህ በፊት መሻገሪያ የነበረው ድልድይ በጎርፍ በመወሰዱና ተጠግኖ አገልግሎት ባለመስጠቱ ነው የሚለውን ክስ አይቀበሉትም፣ ድልድዩ ኖረም አልኖረ ከድልድዩ እርቀው የሚኖሩ ሰዎች ጀልባን ለትራንስፖርት አገልግሎት ይጠቀምበታል ነው ያሉት፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ