1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችአፍሪቃ

በአማራ ክልል የሚካሄደው ውጊያ ወጣቶች ላይ ያስከተለው ተጽዕኖ

ኢሳያስ ገላው
ረቡዕ፣ የካቲት 25 2018

በአማራ ክልል በመንግሥትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘዉ ጦርነት ወጣቶች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት አድርሶብናል አሉ። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ወጣቶች ጦርነቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን እንዳንሠራ አግዶናል፤ በተለይም መፈራራትና ጥርጣሬ እንዲያድርብን አድርጎናልም ብለዋል።

የአማራ ክልል ውጊያ
በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመት በመንግሥትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት በክልሉ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የክልሉ ወጣቶች ገልጸዋል። (ፎቶ ከማኅደር) ምስል፦ AP/picture alliance

በአማራ ክልል የሚካሄደው ውጊያ ተጽዕኖ

This browser does not support the audio element.

 

ኢትዮጵያ አማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመት በመንግሥትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት በክልሉ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ይነገራል። በተለይም ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች ተዳርገናል የሚሉ ወጣቶች ከቦታ ቦታ እንደልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት የተገደበ መሆኑ እና የእርስ በእርስ ግንኙነታችን በጥርጣሬ የተሞላ በመሆኑ ከፍተኛ ስነልቦናዊ ጫና እያሳደረብን ይገኛል ይላሉ። ዶቼቨሌ ያነጋገረው የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ ወጣትም ከደብረ ታቦር ባሕር ዳር እንኳን ተንቀሳቅሶ ለመሥራት መቸገሩን ይገልፃል።  

‹‹እኔ አንድ ሥራ ፈላጊ ወጣት ነኝ። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለምሳሌ ከደብረ ታቦር ባሕር ዳር መሄድ አልችልም። እና ይሄ ትልቅ ተፅዕኖ ነው። ደብረ ታቦር ትንሽ ከተማ ነው። እንደ እኔ የሚመስሉ ወጣቶች አሉ። የሥራ እድል መፍጠር አልተቻለም።»  

ከሰሜኑ ጦርነት በፊት በንግድ ሥራ ተሰማርቶ እንደ ነበር እና በጦርነቱ ሁሉም ነገር እንዳጣ የገለፀልን የሰሜን ወሎ ወጣትም አሁን አካባቢው በግጭት ውስጥ ያለ በመሆኑ ለመሥራት መቸገሩን እና በቀጣይ ስደትን ምርጫ ለማድረግ እያጤነ መሆኑን ይናገራል።  

«እንደዚያ ሆኜ በመከራ ያን ሁሉ ተዘርፈን አብቅተን፣ ባዶ ሆነን እንደገና አንሰራርተን ሱቅ ጀምርን አስቸጋሪ ነው። አሁን የሚሠራበት ሰዓት አይደለም። ጦርነት ነው ያለው የሆነ ነገር ብታደርግ ወይ ፋኖ ነው፣ ወይ መከላከያ ነው የሆነ ነገር ስለሚባል ከባድ ነው። ወደ የትም ተንቀሳቅሰህ ልትሠራ ትችላለህ፤ ግን ተንቀሳቅሶ መስራት አይቻልም። አማራጩ ወደ ውጭ መሄድ ነው። ወደ ሳውዲ ነዋ ወዴት ይኬዳል።»

 በአማራ ክልል የሚካሄዱ ጦርነቶች ከተማን ማዕከል ያደረጉ ባይሆኑም እንኳን ለወጣቱ ከፍተኛ የሥራ እድል ይፈጥሩ የነበሩ ዘርፎች በጦርነት ምክንያት የቀደመ ሥራቸው ላይ ባለመገኘታቸው በከተማ የሚኖሩ ወጣቶች በሥራ እጦት ምክንያት ለሱስ እየተጋለጡ መሆናቸውን ነው የደሴ ከተማ ነዋሪው ወጣት የሚናገረው።  

«ሥራ ስለሌለ ጫት ይዘው ቪዲዮ ቤት ቁጭ ነው የሚሉት ሀሺሹ፣ ጋንጃው ወደዛ ነው ያዘነበሉት።»  

«ሥራ ስለሌለ ጫት ይዘው ቪዲዮ ቤት ቁጭ ነው የሚሉት« የደሴ ከተማው ወጣት አስተያየት።(ፎቶ ከማኅደር)ምስል፦ Esayas Gellaw/DW

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን መርኀቤቴ ወረዳ ነዋሪው ወጣትም አሁን በክልሉ ያለው ግጭት ለተጨማሪ ስቃይ እና እንግልት እንደዳረጋቸው ይገልፃል።  

«የአማራ ክልል ወጣት እንግዲህ አሁን ባለበት ሁኔታ ብዙ የመሰቃየት የመፈነካከት የመንከራተት ግዴታ አለ፤ ያው በቃ ከሥራ መፈናቀልን ያለአግባብ መንከራተትን ይህ ነገር ወደተሻለ ነገር መጥቶ በሰላም በፍቅር እንኑር ብየ ነው የማስበው።»  

ወጣቶች የማኅበረሰብ ተጠባቂ አካል ናቸው የሚሉት በወሎ ዩኒቨርስቲ የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሀየሎም አባዲ ጦርነት የማኅበራዊ ትስስርን፣ አንድነትን የሚያናጋ በመሆኑ በእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ውድመት ሊያስከትል ስለሚችል ወጣቶች በቀጥታ በኢኮኖሚ ተጎጂ ይሆናሉ ይላሉ።  

«ወጣቱም ልክ እንደሌላው የራሱ የሚተዳደርበት ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ይኖረዋል። በጦርነት ጊዜ ያን የሚያጣበት ሂደት ይኖራል ወጣቱ፤  የኢኮኖሚ ድህነት እንዲሰደድ ሊያደርገው ይችላል። ተስፋ ቆርጦ ቤቱ እንዲቀመጥም ሊያደርገው ይችላል። አለያም ወደ ሌላ አማራጭ ያዋጣኛል ይህንን ችግር ሊቀርፍልኝ ይችላል ብሎ ወዳሰበው አካል ተቀላቅሎ ግጭት ውስጥ የሚገባት እድል ሊኖር ይችላል። የመተዳደሪያ ምንጭ ማጣቱ በተለያየ መንገድ ተጽዕኖ አለው ወጣቱ ላይ ማለት ነው።» 

የወጣቶች የማኅበራዊ ግንኙነት መላላት እና የኢኮኖሚ አቅማቸው መዳከም ወጣቶችን ወደ ግጭት ሊያስገባቸውና ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል ይላሉ የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁሩ። 

«በአብዛኛው ወደ ግጭት የሚገባው ኃይል ወጣቱ ነው ተሳታፊ የሚሆነው። በዚህ መሃል የሚሞተው፣የሚቆስለው የሚሰደደውም ወጣቱ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞም ጦርነት ውስጥ የሚገባው የሚሳተፈው በየትኛውም ወገን ያለው ኃይል ወጣቱ ይሆናል። ስለዚህ ለአካል ጉዳት ሞት የሚጋለጥበት ሂደት ይኖራል ማለት ነው።» 

ኢሳያስ ገላው

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW