በአማራ ክልል የሚደረገዉ ግጭት በጤና ባለሙያዎች ስራ ላይ ያደረሰዉ ጫና
ዓርብ፣ ሚያዝያ 3 2017
የአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች በክልሉ በሚደረገዉ ግጭት ጉዳት የደረሰባቸዉንም ሆነ ማህበረሰቡን የማገልገል ተግባር እየተወጣን ቢሆንም አገልግሎታችንን በተገቢዉ መንገድ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በመንግስትና በፋኖ ታጣቂ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘዉ ጦርነት ፈተና እንደሆነባቸዉ የጤና ባለሙያወች ይናገራሉ።
«ሌሊት አሁን ሰዉ ቢታመም ህክምና መድረስ አይችልም ኮማንድ ፖስት አለ ተሽከርካሪ ሌሊት አይንቀሳቀስም ወይ በግርህ ነዉ ባጃጂም አይቻልም እና በጣም ትልቅ ተፅኖ ነዉ ያለዉ ለባለሙያዉ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡም አሁን ከጤና ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር ነዉ ያለዉ ግጭትም ሲኖር የሚቆስል አካል ይመጣል ከሁለቱም እንደዚህ ያለ ነገር በጣም በስጋት ነዉ የምንሰራዉ »
የጤና ባለሙያዎች የሙያ ክፍያ በተገቢዉ ጊዜ ያለመከፈል
በክልሉ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ተመሳሳይ የሆነ ክፍያ ለአገልግሎታቸዉ ያለመከፈልና የትርፍ ጊዜ ክፍያ ወቅቱን ጠብቆ ያለመክፈል ተጨማሪ የባለሙያዎቹ ችግር ሆኖም ተነስቷል
«በዚህ በተፈጠረዉ ችግር ደመወዝ የማይከፈላቸዉ ብዙ ገጠር ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች አያለሁ የነበረዉ ጭማሪ አልተከፈለንም የሚሉ የጤና ባለሙያዎች አሉ»
ህይወታቸዉን ለአደጋ አጋልጠዉ ሙያዊ ግዴታቸዉን በመወጣት ማህበረሰቡን እያገለገሉ ያሉ የጤና ባለሙያዎች በፈተና ዉስጥ የሌሎችን ህይወት የመታደግ ተግባር እየተወጣን ነዉ ይላሉ
<ይህንን ተጋፍጦ የሚመጣዉን ለመቀበል እቤትም ሆነህ እኮ ትሞታለህ ዙሮዙሮ ተቋም ላይ መንግስት በሰጠዉ የስራ ክፍል ህዝብን ለማገልገል አንፃር ህዝብን እያገለገልን ነዉ ምንም ባልተቆራረጠ መልኩ ስራዉ ይሰራል እንደ አማራ ክልል ያለዉ ችግር ነዉ እኛም ጋር ያለዉ>
የመድኅኒቶች መዘረፍ
ሁለት አመት ሊሞላዉ ጥቂት ጊዚያት የሚቀሩት የአማራ ክልል ግጭት ዉስጥ መድኃኒቶች በመንገድ ላይ መዘረፍ የበጀት እጥረትና ትራንስፖርት አለመኖር ለጤና ባለሙያዉ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ፈተና መሆኑ ይገለፃል የአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ሻምበል ፈንታየ በበኩላቸዉ ማህበሩ በክልሉ እየተካሄደ በሚገኘዉ ጦርነት ምክንያት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ አባላቱን መደገፍ ባይችልም በአባላቱ ላይ የሚደርስ እስራትና መንገላታት ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ
<የሚደርስባቸዉም ጉዳት ደግሞ ባስቸኳይ መቆም አለበት ምክንያቱም ባለሙያው ገለልተኛ ሆኖ የሚሰራ አካል ነዉ ለተጎዳ ሰዉ ሁሉ ማገልገል ግዴታዉ ነዉ በባለሙያ ላይ የሚደርስ እስራት ሌሎች መንገላታት ካለ ባስየኳይ መቆም አለበት>
በተለይም የትርፍ ጊዜ ክፍያና ሌሎች የመብት ጥያቄን በሚያነሱ የጤና ባለሙያዎች ላይ የሚደርስ ማዋከብና እስራትን በተመለከተ ለክልሉ አመራር የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነዉ የሚሉት አቶ ሻምበል ችግሮቹን በአግባቡ ለመፍታት እየሰራን ነዉ ይላሉ።«ለጤና ባለሙያዉ እኛ ተወካይ እንደመሆናችን ጥብቅና እንደመቆማችን መጠን ችግሮች በአግባቡ ይፈቱ ዘንድ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ሁሉ እየተገናኘን እየተወያየን ነዉ ችግሮች እንዲፈቱ እናም ከባለፈዉ ከጂምሩ አሁን በተወሰነ መልኩ እየተሻለ የመጣበት ሁኔታ አለ»
የጤና ባለሙያዎች ላይ የሚደርስ ማዋከብና እስራት
በአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች ስራቸዉን በነፃነት እንዲሰሩ ለማስቻልና መድኃኒቶች በተገቢዉ መንገድ ለማህበረሰቡ እንዲደርሱ የጦርነት ተሳታፊ አካላትን የማግባባት ስራ በመስራት ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ባይቻልም መሻሻል እንዳለ የአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሻምበል ፈንታየ ተናግረዋል።
<ሙሉ በሙሉ ተቀረፈ ባይባልም የተወሰነ መሻሻል አለ በተለይም መድኃቶች ከመዘረፍ ከመቃጠል በአግባቡ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ ከማድረግ አንፃር እኛም በተለያየ የግንኙነት መንገድ ለሁሉም እንዲደርስ በግጭቱም በተቃራኒ ወገን ባለዉ ሁኔታም ላሉትም እንዲደርስ ጥረት አድርገናል
ኢሳያስ ገላዉ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ