በአማራ ክልል የሚደረገው የዘፈቀደ እሥር እንዲቆም ተጠየቀ
ሰኞ፣ መስከረም 27 2017በአማራ ክልል የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችን እና መርሆችን ያልተከተሉ እስሮች በአፋጣኝ ሊቆሙ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ።
ኮሚሽኑ በትጥቅ ግጭት እና "በጸጥታ መደፍረስ ወቅትም ቢሆን ሲቪል ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያበቃ በቂ ሕጋዊ ምክንያት መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ብሏል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እና የፋኖ ኃይሎችን ግጭት በሰላም ለመፍታት የአመቻችነት ሚና ይዞ የተቋቋመው የአማራ ክልል የሰላም ምክር ቤት በበኩሉ "ለሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች የሚያዋጣው ንግግር እና ድርድር ነው" ብላል። በክልሉ የሚካሄደው "ጦርነት በቀጠለ ቁጥር ይዞት እየመጣ ያለው ቀውስ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው" ሲሉም የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
የኢሰመኮ መግለጫ ዝርዝር ይዘት
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል ከመስከረም አጋማሽ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ "በአዲስ መልክ" ሲል በገለፀው ሁኔታ ጎንደር እና ባሕር ዳር ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የበርካታ ሰዎች እሥር እየተፈፀመ መሆኑን ገልጿል። የመብት ተቋሙ ድርጊቱ ላይ ክትትል ማድረጉን እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
ብሔራዊው የመብቶች ጥበቃ ተቋም ትናንት እሑድ ባወጣው መግለጫ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላትን ጨምሮ "በርካታ ሰዎች ወደ ጊዜያዊ ማቆያዎች እየተወሰዱ" እንደሆነም ተገልጿል።
እየተደረገ ያለው እሥር "በሕግ አግባብ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ያልተፈጸመ፣ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ያልቀረቡበት እንዲሁም ከመካከላቸው ቋሚ የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች መኖራቸውንም ኢሰመኮ ይፋ አድርጓል።
መስከረም 17 ቀን በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው አድቬንቲስት ትምህርት ቤት እና በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች ማንነታችው ባልታወቁ ሰዎች የቦንብ ፍንዳታዎች መፈፀመቸውንና ጉዳዩን በመከታተል ላይ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የሚፈጸሙት እስሮች "በፍርድ ቤት የተሰጠ የመያዣና የብርበራ ትእዛዝመኖሩን፣ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በመደበኛ ማቆያ ቦታዎች ብቻ እና መብቶቻቸውን ባከበረ ሁኔታ መያዛቸውን እንዲሁም በተያዙ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ማረጋገጥ ይገባል" ስለማለታቸው በመግልጫው ተጠቅሷል።
ማንኛውም አካል "በሲቪል ሰዎች እና በሲቪል ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከማድረስ እንዲሁም የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከሚያውክ ተግባር ሊቆጠብ እንደሚገባም" በመግለጫው አሳስቧል። በኢሰመኮ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር አለሙ ምህረቱን በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀናቸዋል።
"መጀመርያ ለመያዝ የሚያበቃ ሕጋዊ ምክንያት መኖሩ እንዲረጋገጥ፣ ከተያዙ በኋላም ደግሞ በአስቸኳይ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እና የሚያዙበት ቦታም በመደበኛ ማቆያ ቦታዎች ላይ እንዲያዙ ነው ጥሪ ያቀረብነው"።
የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል እና የአመነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪዎች
ግጭቱን በሰላም ለመፍታት በሚል ለአመቻችነት ሚና የተቋቋመው የአማራ ክልል የሰላም ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያቸው ተሻለ በክልሉ ለተጋረጠው ችግር መፍትሔው አሁንም ድርድር ነው ሲሉ እሥሩ ተገቢ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
"ለሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የሚያዋጣው ንግግር፣ ድርድር ነው። ምክንያቱም ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ይዞት እየመጣ ያለው ማህበራዊ ቀውስ ከቀን ወደ ቀን ነው እየጨመረ እየሄደ ያለው። ብዙ የሀብት ውድመት እየተከሰተ ያለበት ክልል ነው እየሆነ ያለው"።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅት በአማራ ክልል እየተፈፀመ ነው ያለው "የዘፈቀደ የጅምላ እሥር" በአስቸካይ እንዲቆም ባለፈው ሳምንት ጠይቋል። ድርጅቱ የፀጥታ ኃይሎች በዘመቻ መልክ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እያሠሩ መሆኑና ጠቅሶ ድርጊቱ "መንግሥት ለሕግ የበላይነት ደንታ ቢስ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው"። ማለቱ ይታወሳል።
የክልሉ መንግሥት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባለፈው ሳምንት በጋራ በሰጡት መግለጫ ግን እርምጃው ሕግ የማስከበር ተግባር ነው ብለው ነበር።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ