1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የቀጠለው ቀውስ እና የንፁሃን ዜጎች ግድያ

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ ጥቅምት 29 2017

በአማራ ክልል ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ "አረጋውያንን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎችን ላይ ከሕግ ዉጭ" ግድያ እየተፈፀመ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ገለፀ። ኢሰመጉ ባወጣው መግለጫ "ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረገው እሥር" በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሌሎችም ክልሎች መፈፀማቸውንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤምስል Ethiopian Human Rights Council

በአማራ ክልል የቀጠለው ቀውስ እና የንፁሃን ዜጎች ግድያ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል የቀጠለው ቀውስ እና የንፁሃን ዜጎች ግድያ

በአማራ ክልል ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ "አረጋውያንን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎችን ላይ ከሕግ ዉጭ" ግድያ እየተፈፀመ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ገለፀ። ኢሰመጉ "በሕይወት የመኖር እና የአካል ደሀንነት መብቶች ይከበሩ" በሚል ባወጣው መግለጫ "ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረገው እሥር" በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሌሎችም ክልሎች መፈፀማቸውንም አስታውቋል። በአማራ ክልል ሰሞኑን በተለይ ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ አቅራቢያ በተፈፀመ ተከታታይ የድሮን ጥቃት በንፁሃን ላይ አስከፊ ጉዳት ስለመድረሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

"ብዙ ሰላማዊ ሰዎች እየሞቱ ነው" - ኢሰመጉ 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ. ም በአዊ ብሔረሰብ ዞን አዲስ ቅዳም ከተማ የመንግሥት ኃይሎች "የፋኖ ደጋፊ ናችሁ በሚል" በየቦታዉ ያገኟቸዉን አረጋውያንን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ከሕግ ዉጭ እንደገደሏቸው፣ በኦሮምያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን እዋሳኝ ድንበሮች ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት "ብዛት ያላቸው" ንፁሃን ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መድረሱን፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወልቂጤ ከተማ ከሰኔ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ብሔርን መሰረት በማድረግ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ እሥር መቀጠሉን ባወጣው መግለጫ ዘርዝሯል። እነዚህ ለማሳያ ተጠቀሱ እንጂ መሰል ድርጊቶች በሌሎች ቦታዎችም መፈፀማቸውን አመልክቷል። የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ ድርጅታቸው ስላወጣው መግለጫ "በታጣቂ ኃይሎች እና በመንግሥት ኃይሎች በሚኖር ግጭት ምክንያት ብዙ ሰላማዊ ሰዎች እየሞቱ ነው" 

ሰሞኑን አማራ ክልል ጎጃም አቸፈር ወረዳ የተፈፀመ ይፕድሮን ጥቃት 

በዚሁ ግጭት የከፋ ጥፋት እያደረሰ ባለበት አማራ ክልል ሰሞኑን ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ ውስጥ በተፈፀመ የሰው አልባ በራሪ ቁስ ወይም ድሮን በተሰነዘረ ጥቃት አስከፊ ጉዳት መድረሱን አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። "በድሮን ነው ጥቃት የፈፀመብን [መንግሥት]። ወደ ሦስት ጊዜ ነው የጣለብን። ከቤተ ክርስትያን ደርሶ የሚመለስ አርሶ አደር ተመቷል፣ ወጣቶች፣ ሕፃናቶች፣ ጤና ጣቢያ ላይ እንደዚሁ እናቶች ተመትተዋል" እኒሁ የዐይን እማኝ ጥቃቱ ንፁሃን ዜጎች ላይ፣ የሕዝብ ምገልገያ እና የሃይማኖት ተቋማት ላይ መድረሱን ጉዳቱ እጅግ የከፋ እንዲሆን ማድረጉን በተጎዳ ስሜት ውስጥ ሆነው ጠቁመዋል። "እናቴች መሣሪያ ይይዛሉ? ሕፃናት መሣሪያ ይይዛሉ?ሽማግሌዎች ኩታ ለብሰው ከቤተ ክርስትያን የሚመለሱ መሣሪያ ይይዛሉ? አይዙም" በማለት በንፁሃን ላይ የደረሰው ጥቃት ምክንያታዊ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። 

አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

ስለ ድርድር እና ሰላም መንግሥት የሚሰጣቸው ምላሾች 

በመላዉ ሀገሪቱ  ጅምላ የንፁሃን ግድያ፣ ሕገ ወጥ ጅምላ እሥር፣ ጾታዊ ጥቃት፣ መፈናቀል መቀጠሉ ተጠቅሶ መንግሥት ይህንን ለምን እንደማያስቆም ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የሀገር ሽማግሌዎች ልከን በእምብርክክ መመለሳቸውን እናንተም እኛም እናውቃለን" በማለት መልስ ሰጥተው ነበር። ደርሷል ስለተባለውየድሮን ጥቃት እና የዘፈቀደ እሥር ለመጠየቅ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ወደሆኑት ለገሠ ቱሉ የእጅ ስልክ ደጋግመን ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም። በኢትዮጵያ የግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አምስት ክልሎች የታጠቁ ሰዎች ባደረሱት ጥቃት "በርካታ ሰዎች" መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሳምንት በፊት አስታውቋል። 

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ምስል Britta Pedersen/dpa/picture alliance

የቀጠሉ የሰላም ጥሪዎች 

የኢሰመጉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ መንግሥት ችግሩን በሰላም ለመፍታት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገበል ብለዋል። "በተለይ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላት ባሉበት ቦታዎች - በአማራም ይሁን በኦሮሚያ ሰላማዊ የሆነ መንገድ ሊፈጠር፤ የንግግር መንገዶች መዘጋጀት አለባቸው። በጥይት፣ በመሣሪያ የሚመጣ ሰላም የለም፤ እስካሁንም አልታየም" ከግጭት ወደ ግጭት እየሄደ ያለው የኢትዮጵያ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ላይ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አማራ ክልል ውስጥ ቀጥሏል ያሉት የዘፈቀደ የእሥር፣ የንፁሃን ዜጎች የሕይወት መጥፋትና ቀውስ  እንዲቆም በመጠየቅ ላይ ናቸው።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW