በአማራ ክልል የቀጠለው ውግያ
ሰኞ፣ መስከረም 27 2017በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን አማኑኤል ከተማና በምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት ከተማና አካባቢው በፋኖ ታጣቂዎችና በመንግስት የመከላከያ ሰራዊት መካከል ከትናንት ጀምሮ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ውጊያ ሲካሄድባት የነበረችው የደንበጫ ከተማ የተኩስ ድምፅ ባይሰማም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ በከተማዋ ውስጥ እንንደማይታይ አንድ የአይን እማኝ ገልጠዋል፡፡
ከትናንት ጀምሮ እስከዛሬ ጠዋት ድረስ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት ከተማና በዙሪያው ጦርነቶች እንደነበሩና ዛሬ ረፋድ ላይ ተኩሱ በተወሰነ ደረጃ መቀነሱን አንድ ነዋሪ ቀን ቀትር ላይ ነግረውናል፡፡
“ከሁለት ሰዓት ጀምሮ ከባድ ውጊያ ነበር አሁን (ቀትር) በረድ ብሏል፡፡” ብለዋል፡፡ ትናንትና ወደ ገጠሩ አካባቢ ሙሉ ቀን ጦርነት እንደነበር የጠቀሱት አስተያየት ሰጪው፣ በተለይ “አቅላት” በሚባል አካባቢ ውጊያ እንደነበርና ዛሬ ደግሞ በከተማው ዙሪያ፣ በተለይም “ሻንጊ” በተባለ ቦታ ላይ ከባድ ውጊያ ቀትሎ ማርፈዱን ገልጠዋል፡፡ “ ነዋሪው ነፍስ ግቢ፣ ነፍስ ውጪ ላይ ነው፣ ሰው ተቸግሯል” ሲሉ ነው ያከሉት፡፡
ሌላ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው ጦርነቱ በሁለቱ ኃይሎች መካከል የተጀመረው ከመስከረም 21/2017 ጀምሮ መሆኑን አመልክተው፣ አሁንም በአራቱም አቅጣጫ ውጊያ መኖሩን ዛሬ ቀትር ላይ ተናግረዋል፡፡
ከመስከረም 21/2017 ዓ ም ጀምሮ በክር አቦ ፈረስ ውሀ ላይ ውጊያዎች እንደነበሩ ተናግረዋል። ዛሬ ደግሞ በከተማዋ ዙሪያ ጦርነቱ ቀጥሎ መዋሉን ገልጠዋል፡፡
በምስራቅ ጎጃም ዞን የአማኑኤል ከተማ ነዋሪም ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በከተማዋና አካባቢው ጦርነት መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡
ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በከተማዋና ዙሪያዋ ከባድ ውጊያ መቀስቀሱን አስረድተዋል፣ ትናንትናም ከከተማ ወጣ ብሎ ውጊያ እንደነበር እኚሁ አስተያየት ሰጪ አመልክተዋል፡፡
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአማራ ክልል በተለይም በጎጃም ቀጠናዎች በፋኖ ታጣቂዎችና በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መካከል ውጊያ ሲካሄድ ሰንብቷል። በተለይ ባለፈው አርብና ቅዳሜ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫና ጂጋ በተባሉ ከተሞች ከባድ ውጊያ እንደነበር ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡
አንድ የደንበጫ ከተማ ነዋሪ ዛሬ ለዶቼ ቬሌ እንዳሉት ዛሬ በከተማዋና አካባቢው የተኩስ ድምፅ ባይሰማም፣ በከተማዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ነው ያስረዱት፡፡ የመንግስት ኃይሎች በከተማዋ እንደሚታዩ አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡
አንድ የጂጋ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ በጅጋና “ሆድ አንሺ” በተባሉ አካባቢዎች ውጊያዎች እንደነበሩ አስታውሰው አሁን የተኩስ ድምፅ አይሰማም ብለዋል፣ በጂጋ ከተማ የፋኖ ታጣቂዎች እንደሚታዩም አብራርተዋል፡፡
በአማራ ክልል ከአንድ ዓመት በፊት በፋኖ ታጣቂዎችና በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መካከል የተነሳው ጦርነት ሰብአዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳትን አስከትሎ አሁንም መቋጫ ሳገኝ እንደቀጠለ መሆኑን ይታወቃል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ