በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 24 2014
ሰሞኑን እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን የየከተሞቹ አስተዳደሮች አስታውቀዋል፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምላፊ ኮማንደር አሳምን ሙላት ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት ከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ውሳኔው መተላለፉን አመልክተዋል፡፡ ደብረ ብርሐን፣ ሰቆጣና ኮምቦልቻ ከተሞችም የሰዓት እላፊ ገደብ መጣላቸውን ዛሬ አስታውቀዋል።
የፀጥታ ኃይሉ የተሻለ ሥራ እንዲሰራ ለማስቻል “ ነጋዴዎች ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ፣ ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎች (ባጃጆች) በከተማው ውስጥ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 1 ሰዓት ብቻ ይንቀሳቀሳሉ፣ ታክሲዎችና ሌሎች ከተፈቀደላቸውና አምቡላንስች ዉጪ ከጠዋት 12 ሰዓት እስከ ምሽት 2 ሰዓት፣ መጠጥ ቤቶችና ምግብ ቤቶች አገልግሎት የሚሰጡ እስከ ምሽት 1 ሰዓት ብቻ ይሆናል” ብለዋል፡፡
ባለሆቴሎችም በምኝታ ቤቶቻቸው የሚያድሩ እንግዶችን መታወቂያ ተቀብሎ ፎቶ ኮፒ እንዲያደርግና ለሚመለከተው አካል ማቅረብ እንዳለበትም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የሰሜን ጎንደር ዞን የሥራ ኃላፊም በዞኑ ባሉ ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል ብለዋል፡፡
“ከምሽት አንድ ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ማንኛውም ሰው እንዳይንቀሳቀስ፣ ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎች (ባጃጆች) በሁሉም የዞኑ ከተሞች ውስጥ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ብቻ ይንቀሳቀሳሉ፣ በዳባትና በደባርቅ የሚገኙ ተፈናቃዮች ከመጠለያ ጣቢያ መግባትም መውጣትም እንዳይችሉ ውሳኔ ተላልፏል” ነው ያሉት፡፡ መታወቂያ ሳይዝ የሚንቀሳቀስ ግለሰብ ከተገኘም ተጠያቂ እንደሚሆን ነው ኃላፊው አመልክተዋል፡፡
የህወሓት ኃይል ባለፈው ሳምንት ወደ ዞኑ ለመግባት ሙከራ አድርገው በመከላከያ ተመትተው ተመልሰዋልም ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የወልዲያ፣ በደቡብ ወሎ ዞን የሐይቅና የተሁለደሬ ከተማ አስተዳደሮች፣ የወልቃይት፣ ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ተመሳሳይ የሰዓት እላፊ ገደቦችን በከተሞቻቸው ላይ ጥለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና በተባባሪዎቹና በህወሓት መካከል የሚደረገው ጦርነት ወደ ወልዲያ እየተጠጋ እንደሆነ ከአካባበው ፈናቅለው ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚሸሹ ሰዎች እተናገሩ ነው፡፡ ሁኔታውን በተመለከተ ከሰሜን ወሎ አስተዳደር ተጨማሪ አስተያየት ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ስልክ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ መስራት ባለመቻሉ አልተሳካልኝም፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ