1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአማራ ክልል ግጭቶች ያስከትሉት ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ

ዓርብ፣ ነሐሴ 12 2015

በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት አለመረጋጋት በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አሳውቋል። አንድ የፖለቲካዊ ምጣኔ ሃብት በክልሉ አምራች ኢንደስትሪዎች በተለይም ሊያስገኙ ከሚችሉት የውጭ ምንዛሪ አኳያ በግጭቱ ሊፈጠር የሚችለው ተግዳሮትም ቀላል እንዳልሆነም ይናገራሉ።

ኮምቦልቻ ከተማ፤ ፎቶ ከማኅደር
የክልሉ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢንድሪስ አብዱ ለክልላዊው የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ጉዳት ማስተናገዳቸውም በርካቶችን ሥራ አልባ አድርጓል። ፎቶ ከማኅደር፤ ኮምቦልቻ ከተማ ምስል፦ Maria Gerth-Niculescu/DW

በአማራ ክልል ግጭቶች ያስከትሉት ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ

This browser does not support the audio element.

 

ሰሞኑን በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት አለመረጋጋት በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አሳውቋል። የክልሉ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ እየተነቃቃ ነበር ያለው ዘርፍ ያስገኝ ከነበረው የውጭ ምንዛሪ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ገቢ አኳያ የደረሰበት ውድመት ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል። አንድ የፖለቲካዊ ምጣኔ ሃብት ባለሙያ እንደሚሉት ምናልባትም አሁን በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት ሊያስከትል የሚችለው የምርት እጥረት፤ በዋጋ ግሽበት የተፈተነችውን አገር ይበልጡንም ሊያስቸግር የሚችል ነው።

የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን አሁን በአማራ ክልል የሚስተዋለው ወቅታዊ አለመረጋጋት ያስከተለውን ዳፋ ከማንሳት አስቀድመው መንስኤ ያሉት ገፊ ምክንያት ያነሳሉ።  «ኅብረተሰቡ አስቀድሞ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ይፈጸምብኛል በሚል ጥያቄ ሲጠይቅ ቆይቷል።በቅርቡ ደግሞ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ትጥቅ አስፈታለሁ ማለቱ እና ከማዳበሪያ እጥረት ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ የተማረረበት ጉዳይ በዚህ ላይ ገፊ ምክንያቶቹ ይመስላሉ። ይህ ደግሞ በብሔራዊ ኢኮኖሚው ላይ ጫና ይፈጥራል።» ነው የ ሚሉት።

ሰላምና ጸጥታ እስከሌለ ድረስ ስለኢኮኖሚ ዕድገት ማሰብ ዘበት ነው የሚሉት ዶቼ ቬለ አስተያየት የጠየቃቸው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ፤ «ለፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ ፖለቲካዊ እልባት መስጠት ከችግሮቹ ለመውጣት ብቸኛው መንገድ ነው» ብለዋል። ፎቶ ከማኅደር፤ ላሊበላ  ምስል፦ Solan Kolli/AFP/Getty Images

ባለሙያው አክለውም በክልሉ አምራች ኢንደስትሪዎች በተለይም ሊያስገኙ ከሚችሉት የውጭ ምንዛሪ አኳያ በግጭቱ ሊፈጠር የሚችለው ተግዳሮትም ቀላል እንዳልሆነም ይናገራሉ። «አገሪቷ ወደ ውጭ ምርት በመላክ ወደ ሦስት ቢሊየን ዶላር ታገኛለች። ምርት ከውጪ ለማስገባት ደግሞ 18 ቢሊየን ዶላር ገደማ ነው የሚያስፈልጋት። 500 በመቶ ደገማ አሉታዊ ልዩነት ያለው ማለት ነው። ግጭቱ ይህነ ክፍተት የበለጠ ያሰፋዋል።»ም ባይ ናቸው።

ሰላምና ጸጥታ እስከሌለ ድረስ ስለኢኮኖሚ ዕድገት ማሰብ ዘበት ነው የሚሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ፤ ለፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ ፖለቲካዊ እልባት መስጠት ከችግሮቹ ለመውጣት ብቸኛው መንገድ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል ተባብሶ የቀጠለው ግጭት በአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ አምራች ኢንደስትሪ ዘርፍ የ2.5 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማስከተሉን የአማራ ክልል ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል። የክልሉ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢንድሪስ አብዱ ለክልላዊው የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ጉዳት ማስተናገዳቸውም በርካቶችን ሥራ አልባ አድርጓል። እንደ ክልሉ ኢንቨስትመንት እና ኢንደስትሪ ቢሮው መረጃ በወቅታዊው ጦርነት ሳቢያ በአንድ ፕሮጀክት ላይ ብቻ በደረሰ ውድመት እስከ ሦስት ሺህ ዜጎች ከሥራቸው ተፈናቅለዋል።

ሰሞኑን በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት አለመረጋጋት በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አሳውቋል። ፎቶ ከማኅደር፤ ጎንደር ከተማ ምስል፦ Nebiyu Sirak/DW

በክልሉ ከሚገኙ ከ38 በላይ አምራች ኢንደስትሪዎች በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ኢንቨስትመንቶች ከተሰማሩት በተገባደደው የበጀት ዓመት 128 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱም ተነግሯል። በአማራ ክልል በተለይም የሁለት ዓመታቱን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት የገታው የፕሪቶሪያው ስምምነት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ከተፈረመ ወዲህ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በፍጥነት ማደጉና በ2015 የበጀት ዓመት ብቻ ከ4 ሺህ 700 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ጥያቄ ከአገር ውስጥ እና የውጪ ባለሃብቶች ቀርቦ እንደነበርም ተጠቁሟል።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW