1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከለከለ

እሑድ፣ የካቲት 10 2011

በአማራ ክልል ከጎንደር እስከ መተማ በተዘረጋው አውራ ጎዳና ሰዎች እንደሚታፈኑ እና መኪናዎችም በጥይት እንደሚመቱ አንድ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናገሩ። «የዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል» በተባለበት በዚህ መንገድ በአምስት ኪሎ ሜትር ክልል በግልም ይሁን በቡድን የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ከዛሬ ጀምሮ ተከልክሏል ተብሏል።

Äthiopien Brigadegeneral Asamnew Tsige
ምስል DW/A. Mekonnen

ብርጋዴየር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ስለመሳሪያ ክልከላ

This browser does not support the audio element.

የአማራ ክልል የሰላም ግንባታ እና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ብርጋዴየር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ለDW እንደተናገሩት የጦር መሳሪያ ክልከላ «ውሳኔው የተላለፈው የኅብረተሰቡን ጤንነት እና ደኅነት ከመጠበቅ አንጻር ነው።» ኃላፊው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጎንደር መተማ መስመር ላይ ይስተዋላሉ ያሉ ወንጀሎችን ዘርዝረዋል። 

«ይሄ መስመር ሕገ ወጥ የሆኑ ሰዎች በተለያየ መንገድ የተደራጁ ሰዎች መኪና እያስቆሙ የሚገሉበት፣ የሚዘርፉበት፣ ማጅራት የሚመቱበት የተለያየ ወንጀል የሚፈጽመበት ነው። መኪናዎች በጥይት ይመታሉ፣ ሰዎች ይታፈናሉ፣ ዘልለው በዚያ ቀጠና ውስጥ ይገባሉ። ስለዚህ የዜጎች ሕይወት በዚያ ቀጠና ውስጥ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ በመነሳት ይህን ዓለም አቀፍ መስመር ለተጠቃሚዎችም ወይም ደግሞ ለተፈላጊው ዓላማ ክፍት ማድረግ አለብን። የመንግስት አንዱ ኃላፊነት እና ግዳጅም ይኼ ነው። ስለዚህ እነዚህ ጥፋተኞች በዚያ እና በዚህ በመንገዱ እየተጠቀሙበት ስላለ አንደኛ መንገዱን አደጋን የማያስከትል ማድረግ ነው፣ ሁለተኛ እዚያ አካባቢ ጥቃት እንዳይደርስ እና እንዲህ አይነት ግለሰቦች ደግሞ ታጥቀው ከተገኙ ደግሞ ለዚያ ዓላማ መሆኑ ታውቆ መንግስት አስፈላጊውን ክትትል አድርጎ እርምጃ ይወስዳል» ሲሉ ለDW ገልጸዋል።  

ምስል AP

«ተመሳሳይ እና ተያያዥ ችግሮች» ከጎንደር በድንጋይ ትክል እስከ ሁመራ ድረስ ባለው መስመርም እንደሚስተዋል የተናገሩት ብርጋዴየር ጄነራል አሳምነው በዚያ መንገድም በአምስት ኪሎ ሜትር ክልል የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከልክሏል ብለዋል። «ወንጀል ፈጽመው ጎንደርን ከተማን እንደ መደበቂያ፣ እንደ ምሽግ የሚጠቀሙ ኃይሎች አሉ ያሉት» ኃላፊው ይህን ለመከላከል በከተማይቱ ከሕጋዊ እና የመንግሥት ታጣቂዎች ውጪ የጦር መሣሪያ ታጥቆ መንቀሳቀስ እንደተከለከለ አስረድተዋል። ሆኖም በከተማይቱም ሆነ በአውራ ጎዳናዎቹ ላይ የሰዓት እላፊ አልታወጀም ብለዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው ክልከላ ከሳምንታት እስከ ወር ሊቆይ እንደሚችል የገለጹት ብርጋዴየር ጄነራል አሳምነው ሆኖም በረጅም ጊዜ ለውጥ ካልመጣ የክልሉ አመራር ለሁኔታው የሚመጥን ውሳኔ ወደፊት እንደሚወስን አብራርተዋል። ክልከላውን ጥሶ በተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ በጸጥታ ኃይሎች የሚወሰደው እርምጃም «ሕግን የተከተለ» ይሆናል ብለዋል።

ከብርጋዴየር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ጋር የተደረገውን አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ      

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW