1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የታወጀው የ10 ወራት የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ቆይታ ተጠናቆ ይሆን?

ረቡዕ፣ ግንቦት 28 2016

በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ የተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ ም ለስድስት ወራት የደነገገውና ጥር 2016 ለተጨማሪ 4 ወራት ያራዘመው የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ዛሬ ተጠናቅቋል፡፡ ዛሬ በ10ኛ ወሩ የተጠናቀቀው አዋጅ ለሌላ ዙር ስለመቀጠሉ ከመንግስት የተባለ ነገር የለም፣ ባለፉት 10 ወራት አዋጁ ምን አስገኘ ?

Äthiopien Bahirdar Covid19
ምስል DW/A. Mekonnen

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜው ቢያበቃም ስለመነሳት መቀጠሉ የተባለ ነገር የለም

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል የታወጀው የ10 ወራት የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ቆይታ ተጠናቆ ይሆን?

በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ የተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ ም ለስድስት ወራት የደነገገውና ጥር 2016 ለተጨማሪ 4 ወራት ያራዘመው የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ዛሬ ተጠናቅቋል፡፡ ዛሬ በ10ኛ ወሩ የተጠናቀቀው አዋጅ ለሌላ ዙር ስለመቀጠሉ ከመንግስት የተባለ ነገር የለም፣ ባለፉት 10 ወራት አዋጁ ምን አስገኘ? ስንል በአማራ ክልል የሚገኙ የአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች አስተያየት ጠይቀናል፡፡

እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት አዋጁ በክልሉ ተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ወደ ተሻለ ሁኔታ ያመጣል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም ጉዳቱ ያመዝናል ይላሉ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ፣

“ይሄ ነው የሚባል ነገር አስገኝቷል ብየ ያየሁትም የሰማሁትም ነገር ስለሌለኝ “እንደዚህ ነው”  የምለው ነገር የለኝም፣ በእጅጉ ጉዳቱ ያመዝናል፣ ብዙ እኮነው ህዝቡ የተጎሳቆለ፣ ከአካባቢያችን ጀምሮ ስቃይ ነው፣ ኑሮው ሰቀቀን ነው፣ ህዝቡ ምን ጥቅም አገኘ ይባላል? ትርፉ ምንድ ነው፣ ሰቀቀን፣ መከራ፣ ሞት፣ እንግልት ነው ያየነው፡፡” ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና አንድምታው

በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሀ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፣ አዋጁ የሞተር ብስክሌቶችን ለ10 ወራት እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጉ፣ በተለይ በአካባቢው በግብርና ስራ የተሰማሩ ባለሀብቶች የግብርና ስራቸውን በአግባቡ ሄደው እንዳይከታተሉ ማድረጉን ጠቅሰው በማሕበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ጉዳት አስከትሏል ነው ያሉት፡፡

“አዋጁ ጥቅሙ ህግን ለማስከበር ነው፣ ህጉ በተገቢው ተከብሯል ወይ? የሚለው ነገር ያጠያይቃል፣ ዞሮ ዞሮ ጉዳቱ ነው እያመዘነ ያለው፣ በኢኮኖሚው ብትለው፣ በሰላሙ ብትለው፣ በተለይ ሰላማዊ ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ነው ያደረገ፣ በቴክኖሎጂው ብትል በሰላሙ ብትል ከጤና አኳያ ሌሊት እናቶች ወልደው መሄድ እንኳ አልቻሉም፣ ስለዚህ አስቸኳ አዋጁ ለእኔ ብዙም ጥቅሙ አልታየኝም፡፡” ሲሉ ገልጠዋል፡፡

የምሽት እንቅስቃሴዎች በተለይ በዝቅተኛ ንግድ የተሰማሩ ወገኖችን ጎድቷል የሚሉት አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ፣ የኢንተርኔት አለመኖርም የቴክኖሎጂ ግብይቶችንና የመረጃ ማግኘት እድሉን ዘግቷል ሲሉ ነው ለዶይቼ ቬሌ የተናገሩት፡፡ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የምሽት እንቅስቃሴዎች በተለይ በዝቅተኛ ንግድ የተሰማሩ ወገኖችን ጎድቷል የሚሉት አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ፣ የኢንተርኔት አለመኖርም የቴክኖሎጂ ግብይቶችንና የመረጃ ማግኘት እድሉን ዘግቷል ሲሉ ነው ለዶይቼ ቬሌ የተናገሩት፡፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ አንድ የህክምና ባለሙያ በአዋጁ ምክንያት ወላዶችና ሌሎች ታማሚዎች ሌሊት ወደ ህክምና መምጣት ባለመቻላቸው ብዙ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡

የታሰሩ ተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብት ይዞታ

“አብዛኛዎቹ ታማሚዎች ሌሊት አይመጡም፣ ሆስፒታል በማድርበት ሰዓት ከምሽቱ 1 ሰዓት በኋላ አይመጡም፣ ከነጋ በኋላ በጣም ከደከሙ ነው የሚመጡት፣ ምክንቱም በአዋጁ ምክንያት ሌሊት መምጣት ስለማይችሉ ነው፡፡ እናቶች ቤት ነው የሚወልዱት፣ ከመጡ ደግሞ በእንጨት አልጋ ሰው ተሸክሟቸው ነው፣ ህክምና ሳይደርሱ የሚሞቱም ብዙ አሉ፣ ከጤናው አንፃር፣ ከመድኃኒት እትረት አንፃር፣  ከብዙ ነገር አንፃር ችላ የተባለ ነው የሚመስለው፡፡”

በምዕራብ ጎጃም ዞን የደንበጫ ከተማ ነዋሪ አዋጁ ብዙም ያመጣው ለውጥ እንደሌለ አመልክተው ችግሮች በውይትና በድርድር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

“የአዋጁ ጠቀሜታ ለእኔ ምናልባት መንግስት አሁን ካለው የባሰ ችግር እንዳይመጣ አስቦ ይሆናል፣ ከዚህ የተሻለ ግን ወደ ድርድር፣ ወደ ውይይት የሚመጣበት አጋጣሚ ቢኖር ነገሮች በሰከነ ሁኔታ ቢታዩ ጠቃሚ ነው፣ አዋጁ እንደገና የሚራዘም ከሆነ ደግሞ ነገሮች የባሰ እየከፉ ነው የሚሄዱት”

የደቡብ ጎንደር አስተያየት ሰጪም ለውይትና ድርድር ቅድሚ ይሰጥ ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ፋይዳ

በሰሜን ጎጃም ዞን የጎነጂ ቆለላ ነዋሪም ሁለቱ ኃይሎች ከጠብመንጃ አፈሙዝ ልቅ ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ መክረዋል፡፡

በሰሜን ጎጃም ዞን የጎነጂ ቆለላ ነዋሪም ሁለቱ ኃይሎች ከጠብመንጃ አፈሙዝ ልቅ ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ መክረዋልምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አክለውም፣ “ሁለቱም ኃይሎች (መንግስትና ፋኖ) እንደ ኢትዮጵያ ካሰቡ፣ ወደ ሰላማዊ ድርድር መምጣት አለባቸው፣ መንግስትም ይህንን ነው መግፋትና ማጠናከር ያለበት፣ ጫካ  ያለው ኃይልም የህብረተሰቡን ችግር አይቶ ወደ ጠረጴዛ ውይይት መምጣት አለበት፣ ብሔራዊ ምክክሩ ወደ ተግባር የሚለወጥ ከሆነ፣ በጣም ትክክለኛ መንገድ ነው፣ ሁለቱም አካላት ለሰላም ሲሉ ወደዚህ ቢመጡ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአማራ ክልል ከተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ በክልሉ ሐምሌ 2015 ዓ ም ለ6 ወራት የታወጀውና ጥር 2016 ዓ ም ላይ እንደገና ለ4 ወራት የተራዘመው   የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ጊዜው ዛሬ ተጠናቅቋል፤ አዋጁ ለሌላ ዙር ስለመቀጠሉም ሆነ ስለማብቃቱ እስከ ዛሬ ቀን 7 ሰዓት ድረስ የተባለ ነገር የለም፡፡

በአማራ ክልል የነበረውን የልዩ ኃይል አደረጃጀት መፍረስ ተከትሎ በክልሉ የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ መፍትሔ ሳያገኝለት  ሞትን፣የአካል ጉዳትንና መፈናቀልን አስከትሎ እነሆ አንድ አመት እየሆነው ነው፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW