1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 2.5 ሚሊዮን ማሻቀቡ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 2016

መንግስት አጠቃላይ በአማራ ክልል በችግር ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በየወሩ ከ2 .2ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደርግም የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብልምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል በድርቅና በፀጥታ ችግር የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 2.5 ሚሊዮን ማሻቀቡ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል በድርቅና በፀጥታ ችግር የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 2.5 ሚሊዮን ማሻቀቡ
በአማራ ክልል በድርቅና በተለያዩ የፀጥታ ችግሮች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 2 ሚሊዮን 500 ሺህ ማደጉን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ፣ መንግስት ለእነዚህ ወገኖች በየወሩ 2 ቢሊዮን 2 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደርግም ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል እንደሚሉት የአማራ ክልል በ2016 ዓ.ም  ሦስት ዋና ዋና ችግሮች አጋጥመውታል፡፡
“... አንደኛው በክልሉ ያለው ግጭት ነው፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ በመገደቡ ምክንት ግብዓትና የምግብ እህል በወቅቱ እየቀረበ አይደለም፣ የቀን ሰራተኛው ሰርቶ እየበላ አይደለም፣ አርሶ አደሩ የምርት ስራውን በተሟላ መንገድ እየሰራ አይደለም፣” ብለዋል፡፡


ሁለተኛው እንደችግር የሚወሰደው ደግሞ እንደ ኮሚሽነሩ፣ የዝናብ እጥረቱን ተከትሎ በክልሉ ያጋጠመው ድርቅ ነው፡፡
“ ሶስተኛው እንደ ችግር የሚወሰደው በተለያዩ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች ክልሉ በርካታ በርካታ ተፈናቃዮችን መቀበሉ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት በአማራ ክልል የተከሰተው ድርቅ ሰፊ ቦታ የሸፈነ ሲሆን 1 ሚሊዮን 850 ሺህ ያህል ወገኖችን የእርዳታ እህል ጠባቂ አድርጓቸዋል ብለዋል ኮሚሽነር ተስፋው፡፡
ኮሚሽነር ተስፋው ትናንት በሰጡት መግለጫ በዚህ ዓመት የተከሰተው ድርቅ በአማራ ክልል በዘጠን ዞኖች፣በ43 ወረዳዎች፣ በ429 ቀበሌዎች የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን 846 ሺህ 955 ሰዎች የድርቁ ቀጥተኛ ተጠቂ ሆነዋል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል በደባርቅ ከሚገኙ ተፈናቃዮች በከፊልምስል Debark Woreda Food Security/Disaster prevention Office


በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ደግሞ 622 ሺህ ወገኖች ከቀያቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመጠለያና ከማህበረሰቡ ጋር እንደሚኖሩ ነው ያመለከቱት፡፡
በራያ አላማጣና አካባቢው በቅርቡ በተቀሰቀሰው ግጭት ደግሞ  “ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ” ያሏቸው ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ ተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች “ተበትነዋል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
መንግስት አጠቃላይ በችግር ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በየወሩ ከ2 ቢሊዮን  2 መቶ ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
ዲያቆን ተስፋው ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች በርካቶች ተፈናቅለው የነበሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡
የአማራና የኦሮሞ ክልሎች መንግስታት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በደረሱት ስምምነት መሰረት እስከ አሁን  1ሺህ 407 ተፈናቃዮች ወደ ኦሮሚያ ክልል መመለሳቸውንና ተፈናቃዮቹን የመመለስ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW