በአማራ ክልል የዘፈቀደ እሥር መቀጠሉን ኢሰመኮ ገለፀ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 30 2017
በአማራ ክልል የዘፈቀደ እሥር መቀጠሉን ኢሰመኮ ገለፀ
በአማራ ክልል ለአሥር ወራት ተደንግጎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግንቦት 2016 ዓ.ም ያበቃ ቢሆንም የዘፈቀደ እሥር መቀጠሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገለፀ።
ይህንን ያሉት ጋምቢያ ውስጥ እየተከናወነ ባለው የአፍሪካ ሰብአዊ እና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን ጉባኤ ላይ አጭር ማብራሪያ የሰጡት የኮሚሽኑ የሲቪል ፖለቲካ እና ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር አብዲ ጅብሪል ናቸው።
ሰሞኑን ለአንድ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ የሰጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በፊናቸው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ "በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተሟላ ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሯል" ብለዋል።
የሰሞኑን መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ሕብረት ቁልፍ ከሚባሉ ተቋማት አንዱ የሆነው የአፍሪካ የሰብአዊ እና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን 83ኛው ጉባኤ ላይ የተካፈሉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሲቪል ፖለቲካና ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር አብዲ ጅብሪል፣ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ. ም በአማራ ክልል ተደንግጎ እና ለአራት ወራት ተራዝሞ ከአሥር ወራት ተፈጻሚነት በኋላ ግንቦት 2016 ዓ .ም ያበቃው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜው ቢጠናቀቅም፣ በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች የትጥቅ ውጊያ በቀጠለበት በዚህ የኢትዮጵያ ክልፍ የዘፈቀደ እሥር ስለመቀጠሉ አብራርተዋል።
"የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢያበቃም የዘፈቀደ እሥራት ቀጥሏል። የማቆያ ቦታዎች የተጨናነቁ፣ በቂ ብርሃን የሌላቸው እና ንፁሕ መገልገያዎችም የላቸውም"።
በሀገሪቱ በዋናነት በግጭት በሚፈተኑት አካባቢዎች "ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው" ያሉት የብሔራዊው የመብቶች ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ፣ የሚያዙ ሰዎች ማቆያ ሥፍራዎች የተጨናነቁ መሆኑንም አመልክተዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በአማራ ክልል ይካሄዳል ያሉት «የዘፈቀደ የጅምላ እሥር»
"ግጭቶችን ለመከላከል ውጤታማ እርምጃዎች አለመኖር እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ለሀገር ውስጥ መፈናቀል መግፍኤ ሆነዋል"
ስለ ኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ
ሰሞኑን NBC ለተባለ የሀገር ውስጥ የመገናኛ አውታር በሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ማብራሪያ የሰጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ "አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ወደተሟላ የሠላም ሁኔታ እየገባች ነው" ብለዋል።
"በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተሟላ ሠላማዊ ሁኔታ ተፈጥሯል"
"የእገታ እና የመዝረፍ ሁኔታዎች እየቀነሱ ቢመጡም አሁንም አሉ" ያሉት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ፣ በሰላምና ፀጥታ ረገድ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አሁን ይገኙበታል ያሉትን የመንግሥት ግምገማ ገልፀዋል።
በአማራ ክልል የሚደረገው የዘፈቀደ እሥር እንዲቆም ተጠየቀ
"በተለይም ካለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ከነበረው ሁኔታ በእጅጉ የተለየ ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሯል በኦሮሚያ፤ በአማራም በድርድርም ይሁን ሕግ በማስከበር አሁን በአብዛኞቹ አካባቢዎች ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሯል"። የሚል የመንግሥት ግምገማ መኖሩን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ከባድ የመብት ጥሰት የፈፀሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የጀመረችውን የሽግግር ፍትሕ ሂደት በአወንታ የጠቀሱት የኢሰመኮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ በኦሮሚያ ክልል የተደጉ የሰላም ስምምነቶች (በመንግሥት እና በታጣቂዎች) እሥረኞች እንዲፈቱ ማድረጉን በጋምቢያው ጉባኤ ላይ በበጎ ጠቅሰዋል። እንዲያም ሆኖ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ትግበራ ላይ አሁንም ፈተናዎች መኖራቸውን በዚሁ አህጉራዊ ጉባኤ ላይ አብራርተዋል።
መንግሥት ለፆታዊና ወሲባዊ ጉዳት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ማቆያ ማዕከላትን ተደራሽ እንዲያደርግ በግጭት ምክንያት በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ የትምህርትና የጤና ማዕከላትም እንዲገነቡ ጠይቋል።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ