በአማራ ክልል የደም ባንኮች አሳሳቢ የደም እጥረት
ሐሙስ፣ የካቲት 20 2017
1.5 ሚልየን ለሚሆኑ የህብሰተሰብ ክፍሎችና 5 ወረዳዎች አገልግሎት የሚሰጠዉ የቅዱስ ላሊበላ አጠቃላይ ሆስፒታል በህክምና ወቅት የሚያስፈልግ ደም በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ እናቶችና ህፃናት ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን የቅዱስ ላሊበላ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ አቤኔዘር ፈንቴ ይገልፃሉ «በጦርነት ብዙ ችግር ያሳለፍን አካባቢ ነን ሰዉሰራሽ አደጋዎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሚከሰትበት በአካባቢያችን ከዚህ ከወቅታዊ ድርቅ የወረርሽኝ አኳያ እናቶች ወላዶች በጣም ብዙ ደም የሚያስፈልጋቸዉ ሰዉ ከመኖራቸዉ አኳያ ህይወታቸው እያጡብን ነዉ ጨቅላ ህፃናት ደም የሚያስፈልጋቸው መለስተኛ ህፃናት ጭምር ብዙ ችግሮች እየደረሰባቸዉ ነዉ»
በደም እጥረት ምክንያት ለህሙማን አስፈላጊዉን ህክምና ለመስጠት ተቸግረናል ሲሉ የተናገሩት የቆቦ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ሲስተር ከበቡሽ በሆስፒታላችን ልምድ ያላቸዉ ሀኪሞች ቢኖሩም የደም እጥረቱ አገልግሎት እንዲሰጡ አላስቻላቸዉም ይላሉ
«እረ በጣም እጥረት አለ ከትናት ወዲያም ደም አጥተን ወደ ወልድያ ሪፈር ብለናል ቀዶ ህክምናም ነበረን ሰርዘናል በደም እጥረት ምክንያት ማለት ነዉ የደም እጥረቱ በጣም አለ አሁን ማህበረሰቡም ደምን ፖለቲካ አድርጎታል»
ሆስፒታሎች በቂ ደም እያገኙ አይደሉም
አሁን ለአስቸኳይ ህክምና ብቻ የሚሆን ደም እንዳላቸዉ የሚገልፁት የወልድያ ደም ባንክ አገልግሎት ስራአስኪያጅ አቶ ጋሹ ደርበዉ የ20 ቀናት ብቻ የሚቆይ ደም ነዉ ያለን ይላሉ ሆስፒታሎች ለህሙማን አገልግሎት ለመስጠት በርካታ የደም ጥያቄ ቢኖራቸዉም መስጠት ጥቂቱን ነዉ ይላሉ
« አሁን እኛ ለአስቸኳይ ህክምና ጊዜ ብቻ የሚሆን ነዉ የምንሰበስበዉ በቂ አይደለም አሁን በቀጠሮ የሚሰራላቸዉን እያዘገየን ነዉ ያለነዉ ደም ሲኖር ብቻ ነዉ የሚሰራላቸዉ ከተማ ላይ አሁን ሰዉ እየለገሰ አይደለም ሆስፒታሎች አሁን ደም ይጠይቁናል 80 ቢጠይቅ አንድ ሆስፒታል የምንሰጠዉ 20 ወይም ከዚያ ያነሰ ነዉ የምንሰጠዉ ከሌለን ደግሞ ሪፈር ነዉ የሚሉት ሪፈር ሲባሉ ደም ከፈሰሰ መንገድ ላይ ሊሞቱ ይችላሉ»
በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል የተለያዮ አካባቢዎች በፋኖና በመንግስት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘዉ ጦርነት ደም በተገቢዉ መንገድ ለመሰብሰብ እንቅፋት እንደሆነ የሚናገሩት የሰቆጣ ደም ባንክ አገልግሎት ስራአስኪያጅ አቶ ክብረት በስራችን ላይ ተፅኖ እየፈጠረብን ነዉ ይላሉ
«የሰላሙ ሁኔታ ምንም ጥያቄ የለዉም ሰዉ አስተሳሰብ ወደ ሌላ አመለካከት ነዉ ደም ስንሰበስብ እና አካባቢው ላሊበላ መስመር ስለሆነ ፋኖ አጎራባች ላይ ያለበት ነዉ ደሙን ለማን ነዉ የምትሰጡት እንዴት ነዉ የምሰበስቡ የሚሉ አንዳንድ ግለሰቦች ለደም ማሰባሰቡ እንቅፋት የሚሆኑ አሉ»
ደም በበቂ ሁኔታ ላለመሰብሰብ ለጋሽ የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎት ማጣት ተጠቃሽ ምክንያት ቢሆንም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ደም ለመሰብሰብ ግን የሰላሙ ሁኔታ እንዳላስቻላቸዉ የወልድያ ደም ባንክ አገልግሎት ኃላፊ ይናገራሉ
«በሰላም ወቅት ላይ እስከ አላማጣ ድረስ እየሄድን እንሰራ ነበር አሁን ሮቢት: ጎብየ: ቆቦ: ቆቦ ሆስፒታል ብቻ ነዉ ስታፉ የሚለግስ እንጂ የሄ ሁሉ ተቋርጧል አሁን በሀብሩ ወረዳ ከተማዉ ላይ ብዙ አልተሰራም ሆስፒታል ላይ ብቻ ነዉ ወርጌሳ ጊራና አቁሟል ግዳን ወረዳም አልሄድንም አሁን ቅርባችን ላይ ሳንቃ ሲሪንቃ ወልድያ ላይ እምቢ ብለዉን እስካሁን አልተለገሰም»
በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች መሪ ስራ አስፈፃሚ ተወካይ የሆኑት ዶክተር መላሽ ገላዉ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ እንዲሰጡን ጠይቀን ፈቃደኛ ባይሆኑም ከቀናት በፊት ከአንድ የሀገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሀን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ በአማራ ክልል ባለዉ ከፍተኛ የደም እጥረት የህሙማን ህይወት እያለፈ መሆኑን ተናግረዉ ነበር።
ኢሳያስ ገላው
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር