1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችአፍሪቃ

በአማራ ክልል የግንባታ ሥራ መዳከምና የቀን ሠራተኛው ሮሮ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1 2017

አማራ ክልል ውስጥ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የግንባታ ዘርፉ በእጅጉ በመቀዛቀዙ በቀን ሥራና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ለችግር መዳረጋቸውን ተናገሩ። አንድ በቤት ግንባታና ሽያጭ የተሰማራ ድርጅት ባለሐብቶች አካባቢውን እየለቀቁ በመሄዳቸው የግንባታ ዘርፉ ተዳክሟል ይላሉ።

በጅምር የቆሙ የግንባታ ሥራዎች ባሕር ዳር
በጅምር የቆሙ የግንባታ ሥራዎች ባሕር ዳርምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የግንባታ ሥራ መዳከምና የቀን ሠራተኛው ሮሮ

This browser does not support the audio element.

 

የፀጥታው ችግር የፈጠረው የኑሮ ጫና

በአማራ ክልል ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩ የግንባታ ባለሙያዎችና የቀን ሠራተኞች ያለሥራ በመቀመጣቸው ኑሯቸውን በአግባቡ ሊመሩ እንዳልቻሉ እየገለፁ ነው። አንድ የግንባታ ባለሙያ ሥራ ካቆሙ አንድ ዓመት እንዳለፋቸውና በርሳቸውም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ላይ የኑሮ ጫና መፍጠሩን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

ምክንያት ያሉትንም ሲጠቅሱ «ባለሀብት የሚባል እየለቀቀ ወደ አዲስ አበባ ሄዷል፣ በእነዚህ ምክንያቶች የሚያሠራው ባለሀብት ባለመኖሩ ሥራ ባሕር ዳር ውስጥ የለም፣ እኔ ራሴ ሥራ ካቆምኩ አንድ ዓመት አልፎኛል» ብለዋል።

ሌላ በቀለም መቀባት ሥራ የተሰማሩ አንድ ባለሙያ በበኩላቸው ለግንባታ የሚውሉ ዕቃዎች አቅርቦት ችግር በእጅጉ መኖሩን ነግረውናል። በዚህም ምክንያት ባለሙያው ሥራ መሥራት ባለመቻሉ በኤኮኖሚ በጣም ተቸግሯል ነው ያሉት።

በፀጥታ ሥጋት ጥሬ ዕቃዎች እንደልብ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳርእንደማይገቡና የገቡትም ቢሆን ዋጋቸው በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ዕቃዎችን ግዝቶ የሚያሠራ ባለሀብት ባለመኖሩ ሥራ ሠርቶ ገቢ ለማግኘትና ቤተሰብ ለማስተዳደር ፈተና ሆኗል ሲሉም ገልጠዋል።

በግንባታ ዕቃ አቅርቦት የተጓተተው የግንባታ ዘርፍፎቶ ከማኅደርምስል፦ picture-alliance/blickwinkel/McPHOTO/BilderBox

በአንድ የሪል እስቴት ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት የሚሠሩ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ለግንብታ ሥራ መዳከም የተለያዩ ምክንያቶ እንዳሉ ነው ለዶይቼ ቬሌ ያስረዱት። 

የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር

እንደአስተያየት ስጪው፣ የጥሬ ዕቃዎች ለምሳሌ በብረትና በሲሚንቶ ዋጋ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሪ አለ። አብዛኛው ባለሀብት ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ አዲስ አበባ በመሄዱ የሚያሠራ አካል የለም። በዚያም ላይ ወደ ባሕርዳርና ወደ አማራ ክልል ቤት አስገንብቶ ለመኖር የሚመጣ ሰው ባለመኖሩ የግንባታው ዘርፍ በእጅጉ እንደተጎዳ ነው ያስረዱት።

ጉዳዩን በተመለከተ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለአማራ ክልል ከተማ ልማትና ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ብንደውልም ስልካቸውን ማንሳት አልቻሉም። አጭር የጽሑፍ መልዕክት ብንልክም መልስ አላገኘንም። የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በበኩላቸው ጉዳዩን የእርሳቸውን ቢሮ እንደማይመለከትና የሚመለከተው የፌደራሉን ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን መሆኑን ገልጸዋል። ለፌደራሉ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር የኮሙዩኒኬሽን ክፍል በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልኩ ሊንሳልን ባለመቻሉ አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW