1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ወደቀያቸው መመለስ የጀመሩት የአማራ ክልል የጻግብጅ እና አበርገሌ ወረዳ ተፈናቃዮች ስጋት

ኢሳያስ ገላው
ሰኞ፣ መስከረም 25 2019

በአማራ ክልል ዋግህምራ ብሄረሰብ ዞን አበርገሌ እና ፃግብጂ ወረዳዎች ከወራት በኋላ የመንግሥት መዋቅር በመመለሱ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ ቢጀምሩም፣ ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት፣ የሰው ሕይወት መጥፋት ያሳደረው ሀዘን እንዲሁም የረሃብና የደህንነት ስጋት እንደተቀነባቸው ነዋሪዎች ገለጹ።

በሰቆጣ ከተማ የሚገኙ የአበርገሌ እና ፃግብጅ ተፈናቃዮች
በሰቆጣ ከተማ የሚገኙ የአበርገሌ እና ፃግብጅ ተፈናቃዮችምስል፦ Private

በአማራ ክልል የጻግብጅ እና አበርገሌ ወረዳ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለስ ጀመሩ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልልየዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ስር በሚገኙ አበርገሌ እና ፃግብጂ ወረዳዎች ለወራት ተቋርጦ የነበረው የመንግሥት መዋቅር በመመለሱና አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ምክንያት በሰቆጣ ከተማ ተጠልለው የነበሩት ተፈናቃዮችወደ ቀያቸው መመለስ መጀመራቸው ተገለጸ። ከሚያዝያ 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዴን ወይም አገዉ ሸንጎ ታጣቂዎች ተይዘው የነበሩት የአበርገሌ እና ፃግብጂ ወረዳዎች ከወራት በኋላ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ውለዋል። በትብብር ኃይሉ አባላትና አዴን እንዲሁም በመንግሥት ኃይሎች መካከል በተካሄደ ግጭት ምክንያት ከ56 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከ5 የተለያዩ ወረዳዎች ቀያቸውን ጥለው በሰቆጣ ከተማ ተጠልለው ቆይተዋል። አሁን ላይ በአካባቢው የተወሰነ የሰላም አየር በመኖሩም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ መጀመራቸውን ይናገራሉ።"በዚህ አካባቢ በርግጥ አሁን ብቻ ሳይሆን ከዚህ  በፊት በጣም በተደጋጋሚ ጦርነት የሚጎዳበት አካባቢ ነው። ተማሪዎች  ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ትዳር አለም እየገቡ ለተለያዩ እንግልቶች የሚዳረጉበት አካባቢ ነው እና ቢያንስ አሁን ወረዳው ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጥተው ለጊዜውም ቢሆን ፎይ ብለናል።"ሲሉ ገልፀዋል።

ለመመለስ የትራንስፖርት ዋጋ መናር

 "አሁን እየገባን ነው አሁን ከተማው እየገባን ነው። እንኳን መጣችሁ እንኳን ደስ አለን ነው የሚሉ። በጣም ቦታው ሁላ ነጭ ነው ሰው የነበረበት ሁላ አይመስልም።" ብለዋል። አቶ ወዳጄ  በላይ እንደሚሉትም ከሰቆጣ ከተማ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው አበርገሌ ወረዳ ተፈናቃዮች ለመመለስ እስከ 1,000 ብር የትራንስፖርት ዋጋ በመጠየቃቸው ምክንያት በርካታ ተፈናቃዮች ረጅም መንገድ በእግር ለመጓዝ ተገድደዋል።

 "ትራንስፖርት አለ። አሁን ደግሞ ትራንስፖርት 1,000 ነው ከሰቆጣ እስከ አበርገሌ 65 ኪሎ ሜትር 1,000 ብር ነው። ስለዚህ አሁን መንግሥት ስንጠይቅ ደግሞ መኪና አብዛኛው ግዳጅ ስለሆነ የመኪና እጥረት ስላለ ተብሎ አሁን እየተጎላላ  የሚኖር ህዝብ አለ።"

ከአማራ ክልል ዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ስር በሚገኙ አበርገሌ እና ፃግብጂ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ለወራት ሰቆጣ ከተማ ተጠልለው ቆይተዋል።ምስል፦ Mebratu Mekonnen/Waghemra Communication

ከግጭቱ ጋር ተያይዞ በሰቆጣ ከተማ ዙሪያ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በነበረው ከፍተኛ ውጊያ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የሚናገሩት ነዋሪዎች በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትም ከፍተኛ ሀዘን ላይ እንደወደቁ ነው የአበርገሌ እና ፃግብጂ ወረዳ ነዋሪዎች የሚናገሩት። "አሁን ሳምንቱን ሙሉ ልቅሶ ልቅሶ ልቅሶ አይደለም የሰነበተው በየቀኑ በየቀኑ ሁለት ሰው አራትሳምንቱን ሙሉ ልቅሶ ነው የሰነበተው። እንዲያው ወጣቶች ወጣቶች በጣም የሚያስገርሙ ወጣቶች። ሳምንት ውስጥ ማለት ነው። 20 እና ከዛ በላይ የሆኑ ወጣቶች በልቅሶ ነው የሰነበተው።"በማለት ገልፀዋል።

"ሞተው ነው በጦርነቱ?" "በጦርነቱ አዎ። ከዛ በቃ ሳምንቱን ሙሉ ልቅሶ ነው የሰነበተው እንግዲህ። ልብስ ጥቁር ልብስ ለብሰን  ነው ያለሁት።" አካባቢው ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የማይቋረጥ የጦርነት ማዕከል በመሆኑ አሁንም ቢሆን የትጥቅ ግጭቱ እንደገና ሊቀስቀስ ይችላል የሚል ትልቅ ስጋት አለ ይላሉ።"በእኛ አካባቢ እንግዲህ በዋናነት የህወሓት ኃይሎች አሉ። ከእነሱ ጋር በተጨማሪ ያው አዴኖች አሉ። እነዚህ ሁለቱ ኃይሎች ናቸው እንግዲህ። ከ2013 ጀምሮ ያው አካባቢው የግጭት ቀጠና ሆኖ ያው የጦርነት ቀጠና እንዲሆን ሆኗል ማለት ነው እና፤ አሁን ለጊዜው ሰላም ነው። ያ ማለት ግን  ሁሉም ሰላም ፈላጊ ሆኖ ለሰላም እጁን ሰጥቶ የተረጋጋ ምህዳር እስከልፈጠርን ድረስ ከስጋት ነፃ ነን ማለት የምንችልበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም።"ሲሉ ገልፀዋል።

በሰቆጣ ከተማ የሚገኙ የአበርገሌ እና ፃግብጅ ተፈናቃዮች በዞኑ የከፋ የረሃብ አደጋ ይከሰታል የሚል ተጨማሪ ስጋት አላቸው።ምስል፦ Private

በተጨማሪም አካባቢው በተደጋጋሚ በተፈጥሮ ድርቅ የሚጠቃ በመሆኑ ዘንድሮ የታየው የአየር ንብረት መለዋወጥ እና ከጦርነት መደራረብ ጋር ተያይዞ በዞኑ የከፋ የረሃብ አደጋ እንዳይከሰት ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።"አዝመራ ደግሞ የለም። አዝመራ በጣም ድርቅ ነው። አበርገሌ ወረዳ ዝናብ የለም። በቃ ከዞን በዋግ ደረጃ ዝናብ እጥረት ነው የነበረው። አሁን ስደት እንዳይሆን ያው በየቦታዉ ጦርነቱ ስለሆነ አልሄዱም አሁን ከጦርነት ይልቅ ረሃቡን ነው የሚያስፈራው።"ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ  ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡን ለፃግብጂ እና አበርገሌ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ስልክ በመደወል እና መልእክት መላክም ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ማግኘት ባለመቻላችን አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልም።

ኢሳያስ ገላው
እሸቴ በቀለ
ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ ዘገባዎች ዐሳይ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW