1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትአፍሪቃ

በአማራ ክልል የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ የሚያስፈትኑ 470 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው

ዓለምነው መኮንን
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 30 2017

በአማራ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ከስራ ውጪ በመሆን በተማሪዎች የመማር ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲፈጠር ቆይቷል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአማራ ክልል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ደግሞ በድጋሜ በተማሪዎችና በትምህርት ቤቶች ላይ ጫናው መቀጠሉን መርጃዎች ያሳያሉ፡፡

Äthiopien Bahir Dar 2025 |  Bildungsabteilung der Stadtverwaltung
ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በክልሉ ሰላማዊ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ለማስፈተን ዝግጅት ማድረጋቸው

This browser does not support the audio element.

 

በአማራ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ከስራ ውጪ በመሆን በተማሪዎች የመማር ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲፈጠር ቆይቷል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአማራ ክልል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ደግሞ በድጋሜ በተማሪዎችና በትምህርት ቤቶች ላይ ጫናው መቀጠሉን መርጃዎች ያሳያሉ፡፡

በዚህ ዓመት በሚሰጠው 12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በክልሉ ሠላም ባለባቸው 470 ትምህርት ቤቶች 99ሺህ 880 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ እየሩስ መንግሥቱ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአማራ ክልል በአጠቃላይ 685 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡

“ሥራ ላይ ያልነበሩ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ዘንድሮም ተማሪዎቻችውን አያስፈትኑም” ት/ቢሮ

በአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት ያልጀመሩና ተማሪዎቻቸውን የማያስፈትኑ በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙም ምክትል ኃላፊዋ አመልክተዋል፡፡

ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ፈተናውን መውሰድ እንደማይችል የገለፀልን አንድ በሰሜን ጎጃም ዞን የሚገኝ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሠላም እስኪመጣ አማራጭ ያለውን ሥራ እየሰራ እንደሆነ ነግሮናል፡፡

“... ወጥተን ገጠር ቁጭ ብለናል፣ ምን እናደርጋለን፣ ከቤተሰብ ጋር ሆነን ልማት ነገር እናለማለን፣ በመስኖ ልማት ለጊዜው ሽንኩርት እያለማሁ ነው፣ ትምህርቱማ በዚህ ሰዓት የለም፡፡” ነው ያለው፡፡

ጦርነት በተማሪዎች እና ትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚጥለው ጠባሳ

“የመፈተን እድሉ ያላቸው ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሰራ ነው” ባለድርሻ አካላት

ፈተናውን ለመስጥት ከሚዝጋጁ ትምህርት ቤቶች መካከል ሰቆጣ ከተማ በሚገኘው ዋግ ስዩም አድማስ ወሰን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት መንግሥቱ አረጋ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተቃራኒ ሽፍት ሳይቀር ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ነው፣ የተሻለ ዝግጅት ያላቸው ተማሪዎችም ሌሎችን እያገዙ እንደሆነ መምህሩ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሞዴል ፈተና እስካሁን ባለመላኩ ሞዴል ፈተና ለመስጠት አለመቻላቸውንም መምህር መንግሥትቱ ጠቁመው፣ ሞዴል ፈተናው ካልመጣ ትምህርት ቤቱ ራሱ አዘጋጅቶ የሚፈትን እንደሚችልም ገልጠዋል፡፡

የመምህራን እገታ በሰሜን ጎጃም

አንድ የትምህርት ቢሮ  የሥራ ኃላፊ ግን የሞዴል ፈተና በቅርቡ ወደ የትምህርት ቤቶች እንደሚላክ አመልክተዋል፡፡

የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ነጋልኝ ተገኝ ወቅታዊው የክልሉ የሠላም ሁኔታው በዞኑ ትምህርት ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ጠቁመው፣ ሆኖም ለአገራዊ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እየተሰራ መሆኑን ገልጠዋል፡፡

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉዓለም አቤ በበኩላቸው፣ በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የተሻለ ዝግጅት እንዲያደርጉ ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጭምር በመተባብር ለተማሪዎች የክለሳና የማጠናከሪያ ትምህረት እየተሰጠ መሆኑን ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡

በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የተሻለ ዝግጅት እንዲያደርጉ ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጭምር በመተባብር ለተማሪዎች የክለሳና የማጠናከሪያ ትምህረት እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ሆነዋል

የዋግ ስዩም አድማስ ወሰን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ብርቱካን ንጉሱና ሩሔ ኃይሉ ያላቸውን ዝግጅት ጠይቀናቸው፣ “ መምህራን በተቻላቸው መጠን ተማሪዎችን ለማገዝ ጥረት እያደረጉ ነው፣ ከዚህ በፊት የነበሩ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ጥያቄዎችን ያሰሩናል፣ የማጠናከሪያ ትምህርትም ይሰጡናል” ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ቀናት በባሕር ዳር ከተማ ከተለያዩ ዞኖች የተውከሉ የትምህርት ባለድርሻ አካላት የተማሪዎችን ውጤት እንዴት ማሻሻል እንደሚገባ፣ እንዲሁም በቀጣዩ ዓመት ትምህርት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶችንና ተማሪዎችን  ሥራ ለማስጀመር መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በአማራ ክልል መማር ያልቻሉ ልጃገረዶች እያገቡ ነዉ

በክልሉ ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የተፈታኞች ቁጥር እየቀነሰ ስለመሆኑ

የአማራ ክልል ቀደም ባሉት ዓመታት በየዓመቱ ከ150 ሺህ እስከ 180ሺህ ተማሪዎችን የማስፈተን አቅም ነበረው፡፡

ባለፈው ዓመት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ 200ሺህ ተማሪዎችን ለማስፈተን አቅዶ የነበረ ቢሆንም ለፈተና የተመዘገቡት 96ሺህ ያክሉ እንደነበሩ በወቅቱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አሳውቋል፡፡ በአማራ ክልል ለ12ኛ ክፍል መለቀቂያ አገር አቀፍ ፈተና ከተመዘገቡት 96ሺህ ተማሪዎች መካከል ከ9ሺህ በላይ የሚሆኑት ለፈተና እንዳልተቀመጡ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡

በአማራ ክልል ወደ 4 ሚሊዮን ታዳጊዎች ት/ቤት አይሄዱም ተባለ

ካለው የፀጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል አጠቃላይ ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ከነበረባችው 7 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል የተመዘገቡት ከግማሸ በታች እንደሆኑ የክልሉ ትምህርት ቢሮ በተለያየ ጊዜ ገልጧል፣ በቅርቡ ባሕርዳር ከተማ ተደርጎ በነበርእው “ትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ማሻሻያ ህዝባዊ ንቅናቄ” ላይ እንደተገለፀው ደግሞ በአማራ ክልል 3ሺህ 700 ትምህርት ቤቶች ከስራ ውጪ ናቸው፡፡

 

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW